የሼህ ሙሐመድ አል-አሙዲ የቀኝ እጅ የሚባሉት ዶ/ር አረጋ ኃላፊነታቸውን ለቀቁ
ሼህ ሙሐመድ ሑሴን አል-አሙዲ (በግራ)፤ ዶ/ር አረጋ ይርዳው (በቀኝ)
ለሜድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ጊዜያዊ ሥራ አስፈጻሚ ተሰየመ
ከሥራ መልቀቃቸው ደባዎች በመደራረባቸው ነው ተብሏል
ኢዛ (ሰኞ ሚያዝያ ፲፱ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. April 27, 2020)፦ በኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ መዋለ ነዋይ በማፍሰስ የሚታወቀውንና በስሩ ወደ 27 የሚኾኑ ኩባንያዎች ያሉትን ሜድሮክ ኢትዮጵያን በመምራት የሚታወቁትና የሼህ መሐመድ አላሙዲን የቅርበ ወዳጅ ዶክተር አረጋ ይርዳው ኃላፊነታቸውን ለቀቁ።
ሜድሮክ ኢትዮጵያ በኢትዮጵያ በተለያዩ ኢንቨስትመንት መስኮች እንዲሰማራ ከጥንስሱ ጀምሮ ትልቁን ድርሻ እንደተጫወቱ የሚነገርላቸው ዶክተር አረጋ፤ ዛሬ ሚያዝያ 19 ቀን ይፋ በኾነው መረጃ፤ ከ20 ዓመታት በላይ የቆዩበትን የሜድሮክ ኢትዮጵያ ኃላፊነታቸውን በገዛ ፍቃዳቸው በመልቀቅ፤ አገሬን በሌላ ዘርፍ አገለግላለሁ ብለዋል።
ሜድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ የሚባለውን እና 27 የሚደርሱ ኩባንያዎችን በዋና ሥራ አስፈፃሚነት ሲመሩ የቆዩት ዶክተር አረጋ፤ ከኃላፊነታቸው ለመልቀቅ የተገደዱት በተለያዩ መልኮች እየደረሰባቸው ባለ ጫና መኾኑን አስታውቀዋል።
ይህንን አስመልክተው ለሜድሮክ ኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ባለቤትና ሊቀመንበር ሼህ ሙሐመድ ሑሴን አሊ አል-አሙዲን በደብዳቤ እንዳስታወቁትም፤ “በተለይ ላለፉት ሁለት ዓመታት ከየአቅጣጫው ከሚገጥሙን ፈተናዎች በተጨማሪ፤ በእጅ አዙር ጫና ራሳቸውን በጠቅላላ ሜድሮክ ላይ ግልጽ በኾነ መልኩ በሾሙ ግለሰቦች በሚፈጸሙ ክብራችንና ኃላፊነታችንን ዝቅ የሚያደርጉ ሁኔታዎች ሲከናወኑ ማየትን በትዕግሥት እኔና ማኔጅመንቱ አባሎቼ በትኩረት ተመልከተናል” በሚል ጠቅሰውታል። አያይዘውም እንዲህ ያለው ሁኔታ አስቸጋሪና ውጤቱም ችግር ይኖረዋል ያሉት ዶ/ር አረጋ፤ ኃላፊነታቸውን መልቀቅ ግድ እንደኾነባቸው ጠቁመዋል።
ጫና አሳድረውብናል ያሉዋቸውን ዋና ዋና ጉዳዮች በዝርዝር በደብዳቤያቸው ያያዙ ሲሆን፤ ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ብቻ በፕሬዝዳንትነት እየመሩ እንዲቀጥሉ ሁኔታዎች እንዲመቻቹ ለሼኩ በጻፉት ደብዳቤ ላይ ገልጸዋል። ዶ/ር አረጋ ዩኒቲን ነጥለው የጠቆሙትም በዩኒቨርሲቲው ውስጥ የባለቤትነት ድርሻ ስላላቸው ነው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የዶ/ር አረጋ ጥያቄ ተቀባይነት አግኝቶ በምትካቸው አቶ ጌታቸው ሃጐስ የሜድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ኩባንያ ጊዜያዊ ዋና ሥራ አስፈጻሚ በመኾን ተሹመዋል።
ለአቶ ጌታቸው ይህንን ሹመት የሠጡት የሜድሮክ ሊቀመንበር ሼህ ሙሐመድ አል-አሙዲ ናቸው።
ሜድሮክ ኢትዮጵያ በሜድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ውስጥ የሚተዳደሩትን ኩባንያዎች ጨምሮ በተለያዩ የኢንቨስትመንተ ሥራዎች ላይ ያሉ 80 ኩባንያዎች አሉት።
ሼህ ሙሐመድ አል-አሙዲ የዶክተር አረጋ ደብዳቤን ተከትለው በጥያቄያቸው መሠረት መልቀቂያውን ተቀብለው፤ “ከኃላፊነትዎ ተሰናብተዋል” በሚል ርዕስ ደብዳቤ ጽፈውላቸዋል። በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ መግባባት ስለመቻላቸው የጠቀሱት ሼህ ሙሐመድ ሥራ ለመሥራት እየፈሩ መኾኑን በመግለጽ ጭምር፤ ከዩኒቲ ኃላፊነታቸው ውጭ ሌላውን ኃላፊነት እና ንብረትና ሰነድ በሙሉ ለአቶ ጌታቸው ሃጐስ እንዲያስረክቡና ከሥራ እንደተሰናበቱ ገልጸውበታል።
ዶ/ር አረጋ ከኃላፊነታቸው ለመልቀቅ የጻፉትና ሼህ ሙሐመድ አላሙዱን የጻፉት ደብዳቤዎች የሚከተሉት ናቸው። (ኢዛ)







