በናዝሬት የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ተቋርጧል
አዳማ / ናዝሬት
የሰዎች እንቅስቃሴዎች ተገድበዋል
ኢዛ (እሁድ መጋቢት ፳ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. March 29, 2020)፦ ሰሞኑን በአዳማ (ናዝሬት) የኮሮና ቫይረስ የተገኘበት ሰው መኖሩ ሪፖርት ከተደረገ በኋላ፤ በአዳማ እንቅስቃሴዎች እየተቀዛቀዙ መጥተው ዛሬ ሙሉ ለሙሉ የትራንስፖርትና ሌሎች እንቅስቃሴዎች ቆመዋል።
የከተማው አስተዳደር በተሽከርካሪ በመዞር ማንም ሰው ከቤቱ እንዳይወጣ ባስተላለፈው ትእዛዝ መሠረት ነዋሪው ከቤት እንዳይወጣ ተከልክሏል። በዚሁ መሠረት ከተማዋ እንቅስቃሴ አልባ ኾና አምሽታለች።
የኦሮሚያ ኮምዩኒኬሽን ቢሮም እንዳረጋገጠው በአዳማ ሦስት በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች መኖራቸውን ተከትሎ፤ በከተማዋ ውስጥ የትራንስፖርት አገልግሎት ከዛሬ ጀምሮ ተቋርጧል። ይህ ከተማዋን አቋርጦ የሚሔደው የትራንስፖርት አገልግሎት አይመለከትም ተብሏል። ባጃጅና ታክሲዎች ግን ሙሉ በሙሉ አገልግሎት እንዲያቋርጡ ተደርጓል። ይህ እቀባ ግን እስከ መቼ እንደኾነ ባይገለጽም፤ ይህ ውሳኔ ተግባራዊ እየኾነ ነው።
በተመሳሳይ መቱ እና አሰላ ከተሞች ውስጥ ትራንስፖርት አገልግሎቶች ቆመዋል። (ኢዛ)



