ጃክ ማ እና አሊባባ ግሩፕ የኮሮና ቫይረስን ሥርጭት በአፍሪካ ለመቀነስ እያደረጉ ያለው የመጀመሪያው ዙር እርዳታ

ጃክ ማ እና አሊባባ ግሩፕ የኮሮና ቫይረስን ሥርጭት በአፍሪካ ለመቀነስ እያደረጉ ያለው የመጀመሪያው ዙር እርዳታ

ለ54ቱ የአፍሪካ አገራት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከነገ ጀምሮ ያጓጉዛል

ኢዛ (እሁድ መጋቢት ፲፫ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. March 22, 2020)፦ በጃክ ማ እና አሊባባ ግሩፕ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ለአፍሪካ ለመሥጠት ቃል ከተገባው የተለያዩ የሕክምና መሣሪያዎች መካከል የመጀመሪያው ዙር አዲስ አበባ ገብቷል።

በመጀመሪያው ዙር ከገቡት ዕቃዎች ውስጥ የመመርመሪያ፣ የቫይረሱ ሥርጭት የመከላከያና የመቆጣጠሪያ የሕክምና መሣሪያዎች ይገኙበታል።

የሕክምና መሣሪያዎቹ አንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን የቫይረሱ መመርመሪያ ኪቶች፣ ስድስት ሚሊዮን የአፍ መሸፈኛ ጭምብሎችና 60 ሺህ ከቫይረሱ ጋር ንክኪ እንዳይኖር የሚከላከሉ ልብሶች መኾናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ የዕቃዎቹን መግባትና ድጋፍ ላደረገው ጃክ ማ ምስጋና ባቀረቡበት መልእክታቸው ገልጸዋል።

ከአሊባባና ከጃክ ማ የተገኙትን እነዚህን መሣሪያዎች ለመላው አፍሪካ ከነገ መጋቢት 14 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ የሚሠራጭ መኾኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።

እነዚህን መሣሪያዎች ለማግኘት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከጃክ ማ ጋር ባደረጉት ውይይት ቃል የተገባ መኾኑ ይታወሳል።

ከነገ ጀምሮ ወደ ተለያዩ የአፍሪካ አገራት የሚሠራጩት እነዚህን መሣሪያዎች የሚያጓጉዘው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ነው። አየር መንገዱ ዛሬ እንዳስታወቀው፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ጃክ ማ ፋውንዴሽን ለአፍሪካ አገራት የለገሠውን የሕክምና መገልገያ መሣሪያዎች ወደ አዲስ አበባ ማጓጓዙን ጥቅሶ፤ “የሕክምና መገልገያዎቹ ወደ 54ቱም የአፍሪካ አገራት በኢትዮጵያ አየር መንገድ ይጓጓዛሉ” ብሏል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ