ቤንሻንጉል ጉሙዝ አዲስ ፕሬዝዳንት ተሾመ
አቶ ጌታሁን አብዲሳ፣ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት
ክልሉ አፈ ጉባዔም ሹሟል
ኢዛ (ሐሙስ መጋቢት ፫ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. March 12, 2020)፦ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት ዛሬ ባካሔደው አስቸኳይ ጉባዔ በቀድሞው የክልሉ ፕሬዝዳንት ምትክ አዲስ ምክትል ፕሬዝዳንት ሾሟል።
ክልሉን በምክትል ፕሬዝዳንትነት እንዲያገለግሉ ምክር ቤት የሾማቸው፤ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ በመኾን ሲያገለግሉ የቆዩትን አቶ ጌታሁን አብዲሳን ነው።
አቶ ጌታሁን የክልሉ ምክትል ፕሬዝዳንት በመኾን የተሾሙት፤ የቀድሞው ፕሬዝዳንት አቶ አዲጎ አምሳያ ሥልጣናቸውን ለመልቀቅ ባስገቡት የመልቀቂያ ደብዳቤ መሠረት ሲሆን፤ ምክር ቤቱ ይህንን መልቀቂያ ከተቀበለ በኋላ አዲሱን ፕሬዝዳንት እንደሾመ ተገልጿል።
በዛሬው አስቸኳይ ጉባዔ አቶ ታደለ ተረፈን የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ አድርጎ የመረጠ ሲሆን፤ ክልሉን በተለያዩ የኃላፊነት መደቦች የሚመሩ አዳዲስ ሹመቶችም ተሠጥተዋል።
በዚህም መሠረት አቶ ነጂመዲን አልሃዲ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ተደርገው ሲሾሙ፤ አቶ ሉቅማን አብዱልቃድር ደግሞ የክልሉ ምክር ቤት የከተማ ልማት፣ ንግድ፣ ኢንዱስትሪ፣ ትራንስፖርትና የበጀት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ኾነው መሾማቸው ታውቋል። (ኢዛ)



