የኮሮና ቫይረስ ምልክት ያሳዩ ሁለት ሰዎች በለይቶ ማቆያ ገብተዋል
Ethiopian Arilines
በአራት ቀን ውስጥ 382 መንገደኞች ቫይረሱ ሪፖርት ከተደረገባቸው አገራት ኢትዮጵያ ገብተዋል
ኢዛ (ዓርብ የካቲት ፳፯ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. March 6, 2020)፦ የኮሮና ቫይረስ ተመሳሳይ ምልክት የታየባቸው ሁለት ሰዎች በለይቶ ማቆያ እንዲገቡ መደረጉ ተገለጸ። በአራት ቀን ውስጥ 382 መንገደኞች ቫይረሱ ሪፖርት ከተደረገባቸው አገራት ኢትዮጵያ መግባታቸው ታውቋል።
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እንዳስታወቀው፤ እነዚህ የኮረና ቫይረስ ምልክት የታየባቸው ሰዎች በማቆያ ክፍሉ ክትትል እየተደረገላቸው ይገኛል።
ይህም ከጥር 15 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ የኮሮና ቫይረስ ምልክት ታይቶባቸው በማቆያ ክፍል እንዲቆዩ የተደረጉትን 29 ያደረሰ ሲሆን፣ ከነዚህ ውስጥ 27ቱ በተለያየ ጊዜ ምርመራ ተደርጎላቸው ከቫይረሱ ነፃ መኾናቸውን ማረጋገጥ ስለመቻሉ መረጃው ያመለክታል።
ከየካቲት 24 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ 14 ሺህ 140 መንገደኞች በሙቀት መለኪያ እንዲያልፉ የተደረጉ ሲሆን፤ ከእነዚህ መንገደኞች 382ቱ ቫይረሱ ሪፖርት ከተደረገላቸው አገራት የመጡ ናቸው። ከእነዚህም ውስጥ 93ቱ ክትትል ሲደረግላቸው እንደነበርና በአሁኑ ሰዓት ክትትሉ መጠናቀቁን አስታውቋል።
ከዚህ በተጨማሪም በአሁኑ ሰዓት ለ910 ሰዎች የጤና ክትትል እየተደረገላቸው መኾኑን የገለጸው ኢንስቲትዩቱ፤ በተለየ መንገድ ስምንቱን በመለየት በተደረገ ምርመራ፤ ሁለቱን ሰዎች ክትትል እንዲደረግላቸው በለይቶ ማቆያ ገብተዋል።
በአሁኑ ወቅት የኮሮና ቫይረስ በአፍሪካ በሰባት አገሮች ውስጥ መከሰቱ ተረጋግጧል። (ኢዛ)



