የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው ጋዜጣዊ መግለጫውን በሠጡበት ወቅት

ሱዳን የህዳሴ ግድብ ይጠቅመኛል ብላ ታስባለች፤ ኢትዮጵያ ግድቡን በሐምሌ መሙላት እንደምትጀምር አስታውቃለች

ኢዛ (ረቡዕ የካቲት ፳፭ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. March 4, 2020)፦ የዓባይን ውኃ የመቆጣጠር ፍላጐት ያላት ግብጽ መኾኗንና በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ሱዳን ያላት አመለካከት ከግድቡ ተጠቃሚ እኾናለሁ የሚል መኾኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው ገለጹ፣ በዓባይ ውኃ መጠቀም የኢትዮጵያም መብት መኾኑንም አስገንዝበዋል።

ከህዳሴ ግድብና ከዓባይ ውኃ አጠቃቀም ጋር ተያይዞ ሰሞኑን የተፈጠረውን አለመግባባት አስመልክቶ አቶ ገዱና ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለሥልጣናት የካቲት 24 ቀን 2012 ዓ.ም. በሠጡት መግለጫ፤ ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሀብቷ የመጠቀም መብት ያላት መኾኗንና የጋራ ተጠቃሚነትንም ታሳቢ አድርጋ እንደምትንቀሳቀስ ገልጸዋል።

በአንፃሩ ግን ግብጽ በተለይ የዓባይን ውኃ የመቆጣጠት ፍላጐት ያላት መኾኑን አቶ ገዱ የገለጹ ሲሆን፤ ከዚህ የዓባይ ውኃ አጠቃቀምና በተለይም ከህዳሴው ግድብ አንፃር ሱዳን ተጠቃሚ መኾኗን እንደምታምን ያመላከተ ገለጻ አድርገዋል።

በሦስቱ አገራት የድርድር ሒደት ሱዳን ግድቡ ይጠቅመኛል የሚል ጠንካራ አቋም ያላት መኾኑን በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ያስታወሱት አቶ ገዱ፤ የዓባይን ውኃ የመቆጣጠር ፍላጐት ያላት ግብጽ ብቻ እንደኾነችም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በድርድር መርኅ ላይ ተመሥርታ ለታችኞቹ የተፋሰሱ አገሮች የበለጠ ተጨንቃ እየሠራችና ግድቡንም በዚሁ እሳቤ እየሠራች መኾኑን በመግለጽ፤ በውኃ አጠቃቀሙ ዙሪያ ኢትዮጵያ ሌሎችንም ታሳቢ አድርጋ የምትሠራ መኾኑን ጠቅሰዋል።

አሜሪካን ሰሞኑን ባወጣችውና ከግድቡ የውኃ አሞላል ጋር ተያይዞ ከሠጡት ማብራሪያ ውስጥ፤ አሜሪካ ሦስቱ አገራት ወደ ስምምነት እንዲደርሱ ግፊት በማድረግ በጐ ሚናዋን እንድትወጣና ከዚህ ያለፈ ሚና እንዳይኖራት የኢትዮጵያ ፍላጎት እንደኾነ ተጠቅሷል።

አሜሪካ የግድቡ ሙሌት ከስምምነቱ በፊት አይካሔድ ማለቷንና ኢትዮጵያ ይህንን እንደማትቀበል ማሳወቋ ግንኙነቱን አይሻክርም ወይ? ለሚለው ጥያቄ፤ አቶ ገዱ ይህ ይኾናል ብለው እንደማያምኑ ገልጸዋል።

“የኢትዮጵያና የአሜሪካን ግንኙነት በዚህ ደረጃ በአንድ ግድብ ላይ ባለ የሐሳብ ልዩነት ላይ ተመሥርቶ ይሻክራል ብለን አናስብም” ያሉት አቶ ገዱ፤ ተስፋ የሚያደርጉት ሦስቱ አገራት ስምምነት ላይ እንዲደርሱ በመደገፍ ሚናቸውን እንዲጫወቱ ነው።

ከዚህ ባለፈ ግን “እኛ ራሳችን ልንሠራ የሚገባውን ነገር ራሳችን እንድንሠራ ይተዉልናል የሚል እምነት ስላለኝ፤ እዚህ ላይ የሻከረ ግንኙነት ይኖራል ብዬ አልገምትም” በማለት፤ ሰሞኑን የተፈጠረው ነገር የአሜሪካንንና የኢትዮጵያን ግንኙነት ያሻክራል የሚለው ሐሳብ ላይ የማይስማሙ መኾናቸውን አመላክተዋል።

አሁን ባለው ደረጃ ግን ከግብጽ በኩል እየተነሳ ባለው ጉዳይ ያለው አንድ አማራጭ መነጋገርና መስማማት ብቻ መኾኑንም አቶ ገዱ ገልጸዋል። ነገር ግን በዚህ መግለጫቸው ላይ አስረግጠው የተናገሩት፤ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን የምትገነባው በተፈጥሮ ሀብቷ ላይ ግድብ የመገንባት ሙሉ መብት ስላላት ነው ብለዋል።

የራሷን የተፈጥሮ ሀብት ተጠቅማ ዜጐቿን ከድህነት ማላቀቅ መብቷ መኾኑን በማከልም፤ “ኾኖም ዓባይን የመሰለ የተፈጥሮ ሀብቷን ስታለማ፤ በዚህ ላይ ሕይወታቸውን የመሠረቱ የተፋሰሱ አገሮች ጉልህ ተፅዕኖ እንዳያሳድር በማሰብ ጭምር ነው።” ብለዋል።

ኢትዮጵያ በድርድሩ እንደምታምን ገልጸው፤ በዚህ ድርድር ግን የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቅ የሚገባ ቢኾንም፤ በአሜሪካ በኩል ስምምነቱ በቶሎ እንዲፈረም የመፈለግ አዝማሚያ እንዳለም ሳይጠቁሙ አላለፉም።

በድርድሩ ወቅት የዓለም ባንክና የአሜሪካ ሚናን በተመለከተ እነዚህ ወገኖች ከታዛቢነት አልፎ ሕግ የማርቀቅ ፍላጐት እንዳላቸው የጠቀሱት አቶ ገዱ፤ ለሁሉም መፍትሔ የሚኾነው ግን መደራደርና ስምምነት ላይ መድረስ ነው በማለት የመንግሥታቸውን አቋም ገልጸዋል።

ከዚህ ውጭ ግብጽ የምታሰማው ዛቻ ጥቅም የለሽ፤ እንዲሁም ለማንም የማይጠቅም መኾኑን ልትገነዘብ እንደሚትገባ በመግለጽ፤ አሁንም የድርድሩ መቀጠል አስፈላጊና ጠቃሚ መኾኑን አስረድተዋል።

በዚህ መግለጫ ጠንክሮ የወጣው ሌላው መልእክት፤ ኢትዮጵያ ግድቡን በስጦታ ወይም በሌላ ወገን ይሁንታ የማትገነባ መኾኑን ሁሉም ሊያውቀው የሚገባ መኾኑንና ግድቡ በሐምሌ ወር ውኃ መያዝ እንደሚጀምር ማረጋገጣቸው ነው።

የውኃ መስኖ ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በተቻለ መጠን ግንባታውን በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ እየተሠራ መኾኑንና በሐምሌ ግድቡ ውኃ መያዝ እንደሚጀምር አረጋግጠዋል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ