የፖለቲካ የጋራ ጥምረት ምርጫው መደረግ የለበትም አለ
“የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት” አመራሮች መግለጫውን በሠጡበት ወቅት
በዕለቱ 52ቱ ፓርቲዎች ተገኝተዋል
ኢዛ (ዓርብ የካቲት ፲፫ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. February 21, 2020)፦ 74 የፖለቲካ ድርጅቶች የያዘው “የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት” ቀጣዩ አገራዊ ምርጫ 2012 መካሔድ የለበትም የሚል ውሳኔ ላይ መድረሱን አስታወቀ። ድምፅ የሠጡበት ዕለት 52ቱ ፓርቲዎች ተገኝተዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች ምክር ቤት አመራሮች ዛሬ በሠጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፤ ምርጫው ይካሔድ አይካሔድ በሚለው ነጥብ ላይ ውይይት ከተደረገ በኋላ የተሠጠው አብላጫው ድምፅ “ምርጫው አይካሔድ” የሚል መኾኑን አስታውቀዋል።
ምክር ቤቱ በጉዳዩ ላይ በሠጠው ድምፅ ስድስቱ ምርጫው መካሔድ አለበት ሲሉ፤ አምስት ደግሞ ድምፀ ተዓቅቦ ሲያድርጉ፤ 41 የፖለቲካ ፓርቲዎች ምርጫው መደረግ የለበትም ብለው በአብላጫ ድምፅ መወሰናቸው ታውቋል። ምክር ቤቱ ከዚህ ድምዳሜ የደረሰው የአገር ጉዳይ መቅደም አለበት በሚል ነው።
ይሁንና ይህ ውሳኔ ባለው የምርጫ ሕግ ብዙዎቹ ፓርቲዎች ወደምርጫ ለመግባት ያስፈልጋል የተባለውን መስፈርት ሊያሟሉ የማይችሉ በመኾኑ፤ ምርጫው እንዲራዘም በመሻታቸው ነው የሚል አስተያየት ይሠጣሉ። የጋራ ምክር ቤቱም ደግሞ ከዚህ ጋር የተገናኘ አይደለም ይላል።
መደረግ የለበትም የሚለው ውሳኔ ሲወሰን በቀጣይ ምን ይሁን ወይም ምን መደረግ አለበት የሚለው መሠረታዊ ጥያቄ ላይ በዝርዝር የቀረበ ነገር የለም። በዚህ የጋራ ምክር ቤት ውስጥ ብልጽግና፣ ኢዜማ፣ ኦነግና ሊሎች ከ70 በላይ ፓርቲዎች ያሉበት እንደኾነ ይታወቃል። (ኢዛ)



