ቴዲ አፍሮና “ኢትዮጵያ ወደ ፍቅር”
“ኢትዮጵያ ወደ ፍቅር” የተሰኘው የቴዲ አፍሮ ኮንሰርት
ከመቶ ሺህ በላይ ታዳሚዎች ይጠበቃሉ
ኢዛ (ዓርብ የካቲት ፲፫ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. February 21, 2020)፦ ኢትዮጵያ ወደፍቅር የሚል መጠሪያ የተሠጠው የታዋቂው አቀንቃኝ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ኮንሰርት ነገ የካቲት 14 ቀን 2012 ዓ.ም በመስቀል አደባባይ ይደረጋል። ኮንሰረቱን ከመቶ ሺህ ሰዎች በላይ ይታደማሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ቴዲ አፍሮ ከበርካታ አድናቂዎቹ ጋር የሚገናኝበት መድረክ እንደሚኾን የሚጠበቀው ይህ ኮንሰርት፤ ከፍተኛ የጸጥታ ጥበቃ እንደሚደረግ ይጠበቃል።
“ኢትዮጵያ ወደፍቅር” የሚለው ኮንሰርት መጠሪያ የተሠጠው የአገሪቱን ሁኔታ ከግምት ያስገባ እንደኾነም ይታመናል።
አንዳንድ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በዚህ ኮንሰርት ምክንያት በአዲስ አበባ ስቴዲየም ይካሔድ የነበረ አንድ የኢትዮጵያ ፕሪሚር ሊግ የእግር ኳስ ጨዋታ መሰረዙን ነው።
በርካታ ታዳሚዎች በሚይዘው የመስቀል አደባባይ እንዲህ ያላ ኮንሰርት ቴዲ አፍሮ ሲያዘጋጅ ከዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ይዘጋጁ የነበሩ ኮንሰርቶቹ ሲሰረዝበት እንደነበር ይታወሳል። (ኢዛ)



