የኢሕአዴግ መፍረስ በምርጫ ቦርድ ተወሰነ
የሕወሓትና የብልጽግና እሰጥ አገባ በኢሕአዴግ ዙሪያ
በሕወሓት የንብረት ክፍፍል ጥያቄ ላይ ውሳኔ ሠጥቷል
ኢዛ (ማክሰኞ ጥር ፳፮ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. February 4, 2020)፦ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) በይፋ መፍረሱን የሚያረጋግጥ ውሳኔ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ተወሰነ። ሕወሓት ኢሕአዴግ ስለፈረሰ የንብረት ልካፈል ጥያቄ በሊቀመንበሩ በዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል በተጻፈ ደብደቤ ማቅረቡ ታውቋል።
የኢትየጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኢሕአዴግን ሕጋዊ ሰውነት ማጣትን ውሳኔ መሥጠቱንና ይህንኑ ባሳወቀበት መግለጫ፤ ኢሕአዴግ በሊቀመንበሩ በኩል በላከው ደብዳቤ ግንባሩ መፍረሱን ያሳወቀ ሲሆን፣ ሕወሓትም በሊቀመንበሩ በኩል በተጻፈ ደብዳቤ ግንባሩ በመፍረሱ የንብረት ክፍፍልን አስመልክቶ ቦርዱ ውሳኔ እንዲሠጥበት ጥያቄ ማቅረቡን ቦርዱ አስታውቋል።
ቦርዱ ይህንን አስመልክቶ የሠጠውን ውሳኔና የንብረት ክፍፍሉን አስመልክቶ ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች አሳውቋል።
የምርጫ ቦርድ ውሳኔ ሙሉ ቃል የሚከተለው ነው።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ሕጋዊ ሰውነት ማጣትን በተመለከተ የሰጠው ውሳኔ
ኢሕአዴግ በሊቀመንበሩ በኩል ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በላከው ደብዳቤ ግንባሩ መፍረሱን ለቦርዱ ያሳወቀ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) በሊቀመንበሩ በኩል በተጻፈ ደብዳቤ ግንባሩ በመፍረሱ የንብረት ክፍፍልን አስመልክቶ ቦርዱ ውሳኔ እንዲሠጥበት ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
የግንባሩን መፍረስ የመወሰን ሥልጣን የቦርዱ በመኾኑ ግንባሩም ኾነ ሕወሓት ግንባሩ መፍረሱን መጥቀሳቸው የማይገባ ቢሆንም፤ ቦርዱ ሁለቱ ሊቃነመናብርት ያቀረቧቸውን የጽሑፍ ጥያቄዎች መሠረት በማድረግ ግንባሩ መፍረስ አለበት ወይ? ከፈረሰስ ውጤቱ ምን ይኾናል በሚል ቦርዱ መርምሮ ውሳኔ ሠጥቷል፡፡
በመኾኑም ቦርዱ የግንባሩ አባል ሦስት ፓርቲዎች ከግንባሩ ወጥተው አዲስ ውሕድ ፓርቲ መመሥረታቸውን የብልጽግና ፓርቲን አመሠራረት ከሚያሳየው መዝገብ ተረድቷል፡፡ በመኾኑም ግንባሩ በተግባር መፍረሱን ቦርዱ በሙሉ ድምፅ ወስኗል፡፡ የግንባሩን መፍረስ ተከትሎ ቦርዱ የኢሕአዴግን ንብረት አስመልክቶ ውሳኔ መሥጠት እንደሚያስፈልግም ተረድቷል፡፡
በመኾኑም የኢሕአዴግ አባል ድርጅት የነበሩት ሦስቱ ማለትም አዴፓ፣ ኦዴፓና ደኢሕዴን ብልጽግና የሚባል ፓርቲ መመሥረታቸው፤ በሌላ በኩል ደግሞ ሕወሓት ሕልውናውን ጠብቆ የቆየ ፓርቲ በመኾኑ፤ በሕጉ መሠረት በብልጽግናና በሕወሓት መካከል የኢሕአዴግን ንብረት ክፍፍል ማድረግ እንደሚገባ ቦርዱ ተገንዝቧል፡፡ በመኾኑም ቦርዱ የኢሕአዴግን ንብረት አስመልክቶ የሚከተሉትን ውሳኔዎች ወስኗል፡፡
1. ብልጽግናና ሕወሓት የኢሕአዴግ ንብረትና ሒሳብ የሚያጣራ አጣሪ በጋራ እንዲሰይሙ፣
2. በኢሕአዴግ ስም ያለ ማናቸውም እዳ ተጣርቶ እንዲከፈል፣
3. ከእዳ ክፍያ ቀሪ የኾነ ሀብት 3/4ተኛው ለብልጽግና ፓርቲ ( የሦስቱ የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች ውሕደት በመኾኑ) ¼ተኛ ደግሞ ለሕወሓት ድርሻ መኾኑ ታውቆ፤ በዚያ መሠረት ክፍፍል እንዲያጠናቅቁ፣
4. ከላይ የተጠቀሡትን ተግባራት በሕጉ መሠረት በ6 ወር ውስጥ ለቦርዱ እንዲያሳውቁ ተወስኗል፡፡ (ውሳኔው በጽሑፍ የሚደርሳቸው ይኾናል)
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ



