PM Abiy Ahmed parliamentary hearing

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ሲሠጡ፤ ጥር 24 ቀን 2012 ዓ.ም.

የታገቱት ተማሪዎችን በተመለከት ምላሽ ሠጥተዋል

ኢዛ (ሰኞ ጥር ፳፬ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. February 3, 2020)፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ዛሬ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ እንደሚሠጡ ከተገለጸበት ቀን ጀምሮ ወቅታዊውን የዶ/ር ዐቢይ አንደበት ለመስማት ብዙዎች ጓጉተው ነበር። ዛሬ ከጠዋቱ ጀምሮ ሁሉም ማብራሪያውን ለመስማት የሚያስችለውን የሥርጭት አማራጭ አስተካክሎ ሲጠብቅ ነበር ማለት ይቻላል። ይሁንና ብዙዎች እንደጠበቁት ወይም ረፋድ ላይ ሳይሆን ፕሮግራሙ ከሰዓት በኋላ ነበር የተካሔደው። የታገቱት ተማሪዎችን በተመለከት ምላሽ ሠጥተዋል።

ብዙዎች በጉጉት የጠበቁት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የዛሬ ውሎ ከሌላው ጊዜ በተለየ ሊጠበቅ የቻለው መልስና ማብራሪያ የሚሹ አገራዊ ጉዳዮች ከመበርከታቸው ጋር የተያያዘ ነው ማለት ይቻላል። ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የቀረቡ ጥያቄዎችም ከሞላ ጐደል ይህንን የሚያመላክቱ ናቸው።

በቅድሚያ ከቀረቡ ጥያቄዎች መካከል የዘር ፖለቲካ፣ የሃይማኖት ጉዳይ፣ የሕግና ሥርዓት እንዴት ይከበራል? በተለያዩ ክልሎች የለውጡን ሒደት የሚያውኩ የተለያዩ ሕገወጥ ተግባራት የሚፈጽሙ ከመበራከታቸው አንፃር የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በጥፋት ኃይሎች ላይ የሚወሰደው እርምጃ የችግሩን ያህል ነው ወይ? የደንቢ ዶሎ ተማሪዎች እገታ ጉዳይ ምንድነው?

የንብረት ሥርጭትና እገታ፣ ሕገወጥ ግንባታና የመሬት ወረራ መበራከትንም የተመለከተ ጥያቄ ቀርቧል። የመንግሥት አመራርና የጸጥታ ኃይል ችግሩን በመከላከል ረገድ ውጤታማ ሲኾን አይታይም የሚል ጥያቄም ነበር። እንዲህ ያሉ ሁኔታዎች ሕግ የማይከበር መኾኑን በመጥቀስ ቅስቀሳ ጭምር እየተደረገበት በመኾኑ እነዚህ ችግሮችን ለመፍታት ለምን አልተቻለም? ወደፊትስ ምን ታስቧል? የሚሉም ጥያቄዎች ነበሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በመጀመሪያው ዙር ለቀረቡት ጥያቄዎች መልስ ከመሥጠታቸው ቀደም ብሎ ግን ወደኋላ መለስ ብሎ ከለውጡ በፊት የነበረውን አገራዊ ሁኔታ ለማስታወስ በመፈለግና ይህንንም በማስገንዘብ የዕለቱን ማብራሪያ ለመጀመር ወድደዋል።

ከለውጡ በፊት ኢትዮጵያ እንደ አገር መቀጠል የማትችልበት ደረጃ ላይ እንደነበረች በማስታወስ፤ በሁሉም መስክ በፖለቲካው፣ በኢኮኖሚና በማኅበራዊ ጉዳዮች ወደ ፊት መጓዝ ብቻ ሳይሆን፤ ባለችበት መቆም የማትችልበት ደረጃ ደርሳ ነበር ብለዋል።

ለውጡን ስንጀምር አንዱ አዳጋች የነበረው ነገር ቀድሞ በነበረው መንግሥት የተወሳሰበ ጥልፍልፍ ትስስሮችና ያልተገቡ ኔትዎርኮች አገረ መንግሥቱ በግለሰቦችና ቡድኖች እጅ ይጣል እንደነበርም አስታውሰዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ ስቴት ካፕቸር አጋጥሞ ነበር። አንድ ነገር ታስቦና ታቅዶ የሚፈጸምበት ሁኔታ ሙሉ የመንግሥት ሥርዓትና ሲስተም ተገንዝቦ የሚሠራው አልነበረም።

ይህ ጥልፍልፍና በውል ያልተለየ ኔትዎርክ ላይ ላዩን ኃላፊዎች በማወቅ ብቻ ከሥር መሠረቱ ያንን ያልተገባ ኔትዎርክ በጣጥሶ ትክክለኛ ሥርዓት መገንባት ቀላል ሥራ አልነበረም ብቻ ሳይሆን፤ ሥልጣን ስንረከብ ያን ጥልፍልፍ ኔትዎርክ መገንዘብ በራሱ ውስንነት ነበረው። መገንዘብ ስንጀምርም ያ ኔትዎርክ በምን ሊፈታና ሊበጣጠስ እንደሚችልና ያንን ለመፈጸም የሚያስችል ቁልፍ በእጃችን አልነበረም በማለት በወቅቱ የነበረውን ፈተና አመላክተዋል። መንግሥትን በቁጥጥር ያዋለው ኢንፎርማል ኔትዎርክ ሥልጣን በተረከቡ ማግስት ብን ብሎ የጠፋ እንዳልነበረም ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሮች ይቀያየሩ እንጂ ስቴት ካፕቸር ያደረገው ያልተገባ ኔትዎርክ በጥቅም፣ በዘርም በዝምድና በጓደኝነት የተሳሰረው ኔትዎርክ ወዲያው አልተበተነም፤ አልታወቀም/ መፍቻ ቁልፉም አልተገኘም። ወዲያውም አልጠፋም። ሥራ በተጀመረበት ወቅት አንዳንድ ገመድ መለየትና መበጠስ ስንጀምር፤ መላ ኔትዎርኩ የቆመ ተበጣጥሶ ያለቀ የመሰለንም ስሕተት ነበርም ብለዋል። እስከታችኛው አስፈጻሚ አካል ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ የተደራጀ ሲፈልግ ማስኬድ፤ ሲያሻውም ማስቆም የሚያስችል የደረጃ ትስስር ነበረው።

ይህ ትስስር ምን መልክ እንዳለው በመረዳትና በማስቆም ዘላቂ እድገት ለማረጋገጥ መንግሥት በለውጡ ማግስት ሊከተል የፈለገው መንገድ መለየት ያለባቸውን ሥራዎች መለየት ነበርም በማለት በለውጡ ማግስት የገጠመውን ችግር በሰፊው አብራርተዋል።

ያልተገኘው ኔትዎርክ ያሳደረውን ተፅዕኖ ካስረዱ በኋላና ከለውጡ ወዲህ የተደረጉ ማሻሻያዎችን በማድረጉ ሥራ ላይ ኔትዎርኩ ለማደናቀፍ ባለመቻሉ ሕግጋት ስለመሻሻላቸውም ጠቅሰዋል።

እንዲህ ያሉ ሥራዎች ከተሠሩ በኋላ ተቋማትን ለመገንባት የተሔደበትን መንገድ በመጥቀስ፤ የተደረጉ ማሻሻያዎችን በጥበብና በትዕግስት ሲፈጸሙ እንደነበር አስታውሰዋል። ሌሎች በችግርና በተወሳሰበ ሁኔታ የተሠሩ መልካም ሥራዎችን በመግለጽ በቀጥታ ወደ ጥያቄዎች መልስ ገብተዋል። በዕለቱ ከቀረቡ ጥያቄዎች ከሠጡት ምላሽ ውስጥ የአንዳንዶቹን እናቀርባለን።

“እገታው” እና የጠቅላይ ሚኒስትሩ መልስ

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዛሬው የፓርላማ ውሏቸው ይጠየቃሉ ተብለው ሲጠበቁ ከነበሩት ጥያቄዎች ውስጥ አንዱ የደንበዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እገታ ጉዳይ ነው። የፓርላማ አባላቱም ይህንን ጥያቄ ያነሱ ሲሆን፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ምላሽ ሠጥተዋል።

ዶክተር ዐቢይ ለዚህ ጥያቄ ምላሻቸውን የጀመሩት ለእገታው ኃላፊነቱን እወስዳለሁ ያለ አካል ባለመገኘቱ ጉዳዩን ፈታኝ እንዳደረገው በመጠቆም ነው። ነገር ተማሪዎቹን ለማግኘት ግን መንግሥት ጥረቱን መቀጠሉን ተናግረዋል።

በዚሁ ጉዳይ በሠጡት ተጨማሪ ማብራሪያ “ቦኮሃራም ሰው ሲያግት ኃላፊነት እወስዳለሁ ብሎ ያውጃል፤ አልቃይዳ ሰው ሲያግት ኃላፊነቱን እወስዳለሁ ብሎ ያውጃል፤ በእኛ ጉዳይ እስካሁን ድረስ እገታውን ፈጽሜያለሁ ብሎ ኃላፊነት ለመውሰድ እራሱን የገለጸ ኃይል የለም።” ብለዋል።

እነዚህ ግለሰቦች መጀመሪያ ተይዘዋል፣ ከዚያ ተፈተዋል ከተባለ በኋላ አዳዲስ መረጃዎች መምጣት ሲጀምሩ መረጃውን ለማጥራት ሙከራ ስናደርግ ተማሪ ያልኾኑ ከተማሪዎች ጋር ስማቸው የተገለጠ ሰዎች ያሉበት መኾኑ፤ ተማሪ ኾነውም አንዳንዶቹ ከተባለው ስፍራ ውጭ መኖራቸውን የማያመላክት መረጃ በመኖሩ፣ መከላከያም አስሶ ምንም የለም በማለቱ፤ በመንግሥት በኩል በፍጥነት የታገቱ የለም የሚል ድምዳሜ ወደመውሰድ የሚያስችሉ ግፊቶች ነበሩ።

ነገር ግን በእኛ በኩል የነበረው ምላሽ እያንዳንዱ ዜጋ ወደ ሱዳን ተሰድዶም ይሁን ታግቶም ይሁን፣ ተደብቆም ይሁን አድራሻው እስኪታወቅ ወላጅ ስላለ፤ እናት ስላለች፤ አልታገቱም የሚል መልስ በፍጥነት መዘገቡ ተገቢ ነው ብለን አላመንም።

እስካሁን ድረስ መከላከያ በሚያደርገው ጠንካራ ኦፕሬሽን በአንድም ስፍራ የተጐዳ፣ የሞተ ሰው ሊገኝ አለመቻሉንም ጠቅሰዋል።

“መታገታቸውን እኔ አገትኩ የሚል ኃይል የለም፤ ተጐድተዋል እንዳይባል በሁሉም ቀበሌ፣ በሁሉም ወረዳ በተደረገ አሰሳ ተጐድቶ የተገኘ ሰው የለም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “ችግር አልደረሰባቸውም፣ አሉ እንዳይባል ቤተሰብ ጋር ያልደረሱ ልጆች አሉ” በማለት ገልጸዋል።

ሳይጐዱ እንደተጐዱ የሚነገር እንደተጠበቀ ኾኖ ግን፤ በውል የት እንዳሉ የማይታወቁ ሰዎች ደግሞ እንዳሉ በመጥቀስ እንዲህ ያሉ ነገሮች ሲያጋጥሙ መንግሥታት ያገተውን ኃይል ሲያውቁ ሰውን ለማዳን በገንዘብ ሁሉ ይደራደራሉ።

“ከአልቃይዳ ጋር በሚደረግ ትግል አሜሪካ የአልቃይዳውን መሪ ቢን ላዲንን ያሳየ ይህንን ያክል ሚሊዮን ዶላር ይከፈለዋል ትል ነበር። በግልጽ ራሱን ገልጾ አግቻለሁ ብሎ ኃላፊነት የሚወስድ ሲጠፋ ግን የግድ ማሰስ ይጠይቃል። ሲታሰስ ተጠቂው የዚያ ተማሪ ቤተሰብ ብቻ አይደለም። ተጠቂው አገር ነው። ተጠቂው የወለደች ወላድ በሙሉ ናች። በየትኛውም ደቂቃ ልጇ እዚህ አደጋ ውስጥ ሊገባ ይችላል። ተጠቂው ሰላም ወዳድ ሕዝብ ነው። እነዚህ ሁሉ ተባብረው ጥፋተኛውን መገሰፅና እታገልሃለሁ ማለት እንዳይችሉ፤ ጥፋተኛው ቢጠሩት የማይሰማ፣ ያለበትን የማይናገር በመኾኑ፤ ጉዳዩን ውስብስብ አድርጐታል። እንዳሻንም መናገር እንዳንችል አድርጐናልም ብለዋል። እንዳሻን በመናገራችንም የሰው ሕይወት አደጋ ላይ እንዳናስገባ ጥንቃቄ በማስፈለጉ፤ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር፣ በከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ከሁሉም የጸጥታ ተቋማት ተውጣጥቶ ከፍተኛ ሥራ ሲሠራ እንደነበር ያስታወሱበትን ምላሽ ሠጥተዋል።

አያይዘውም እነዚህ አካላት መላ ውጤታቸውን በደረሱበት ጊዜ እንደሚያሳውቁ ተስፋ አለኝ ብለዋል። ማረጋገጥ ያስፈልጋል ብለው የገለጹት ደግሞ፤ “እስከዚህች ደቂቃ ድረስ በእገታው ምክንያት የሞቱ አንድም ማረጋገጫ ያላገኘን መኾኑ፤ ሙሉ ለሙሉ በሚባለው ልክ አለመኾኑን የምናውቅ ቢሆንም፤ ሙሉ በሙሉ በእጃችንና በቁጥጥራችን ስር የዋለ ባለመኾኑ፤ መከላከያም የራሱን ሥራ እየሠራ በመኾኑ፤ የመረጃ ተቋማትም ሥራቸውን እየሠሩ፤ ኮሚቴው አስፈላጊ ኾኖ ሲገኝ የደረሰበትን በየጊዜው የሚያሳውቅ ይኾናል” ብለዋል።

በዚህ ጉዳይ ላይ ለምንድነው መንግሥት በየጊዜው መረጃ የማይሠጠው በሚለው ክስ ላይ ዶ/ር ዐቢይ፤ “በአንድ በኩል ትክክለኛ ክስ ነው፤ በሌላ በኩል ግን ኦፕሬሽኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። መንግሥት ባለው ኃይልና አቅም ልክ ባልተሟላ መረጃ ጠንከር ያለ መግለጫ በሚሠጥበት ጊዜ፤ ያልተደራጁ ግለሰቦች ያደረጉት እገታ ከኾነ፤ ራሳቸውን ለማዳን ታጋቾችን ሊጐዱ ይችላሉ፤ ሊገድሉ ይችላሉ።”
ጠ/ሚኒስትሩ አክለውም “የእኛ ዋና ፍላጐት ምንም ሰው ሳይሞት በሕይወት እንዲገኝ ስለኾነ፤ ከመናገር ይልቅ በሕይወት የማስገኘቱን የማሳለጡ ሥራ ቅድሚያ የተሠጠው እንደኾነ፤ ከቤተሰብ፣ ከሽማግሌዎች ጋር በተደረገው ውይይት እስካሁን በዚህ ረገድ ጥቃት ደርሶ ሕይወታቸው ያለፈ ሰው አንድም ሪፖርት ያልደረሰ መኾኑን፤ ምናልባት ችግሩ ግን ከሩቅ የመጣ አልሸባብ ወይም ሌላ ጠላት ሳይሆን እውስጥ በእኛ ስብእና ግንባታ ችግር የመጣ ስለኾነ፤ እንዲያው ጠላት በቀላሉ ማስወገድ አልተቻለም” የሚል ምላሽ ሠጥተዋል።

ቻይኖች “ከግንቡ አጥር ፊት” የሚል አባባል አላቸው፤ የቻይኖች ዋነኛው ተግዳሮት የነበረው ሁልጊዜም በጐረቤት አገሮች መወረር ነበር። በጐረቤት አገሮች የሚደርስባቸውን ጥቃት በሺሕ ኪሎ ሜትር የሚጠጋ ግንብ ገነቡ። ግንቡን ሲገነቡ ሰው ዘሎ ሊገባ እንደማይችል አረጋግጠው ከፍ አድርገው ነው። ነገር ግን ከግንቡ ግንባታ በኋላ የጠላት እግረኛ ኃይል እየገባ ጥቃት ፈጸመባቸው።

ቻይናዎች ያን የሚያክል ግንብ የገነቡት ሰላም ወዳድ ስለኾኑና በሰላም ለመኖር ካላቸው ጥማት ቢኾንም፤ ግንቡ በሰላም ሊያኖራቸው ባለመቻሉ፤ ባደረጉት የማጥራት ሥራ፤ ግንቡ ዙሪያ አልፎ አልፎ የተቀመጡ ቻይናውያን ጠባቂዎች በሚሠጣቸው ማባበያና ጉርሻ የጠላት እግረኛን ያሳልፉ እንደነበር ደረሱበት።

እናም ቻይናውያን “ግንብ ከመገንባት በፊት የሰውን አገር ወዳድነትና የጠላትነት ልክ መገንባት ነበረብን” አሉ ይባላል። በውስጥ ያለው አሾልኮና አስርጐ የማያስገባውን ኃይል መገንባት እስክንችል፤ የሚመሳሰል ጠላት ጠዋት “ደኅና አደርክ!?” ብሎ፤ ቀን ጥፋት የሚወስድ ጠላት መለየት፤ እንኳን ለጀማሪ የሪፎርም ኃይል፤ ለጠንካራ መንግሥታትም ቢኾን አዳጋች መኾኑን ከግምት ሊገባ ይገባዋል።

መንግሥታት በአገር ማፍረስ ሒደት ውስጥ ሦስት ፈተና ያጋጥማቸዋል። አንደኛው አርኣያ የሚኾኑ፣ የሚደመጡ፣ የሚመክሩ፣ የሚገስጹ ግለሰቦች ብቅ ሲሉ፤ እነዚያ ግለሰቦች እንዳይመጡ ምክራቸው ፍሬከርሲኪ ተደርጐ እንዲወሰድ ጠንካራ የኾነ የማጠልሸት ሥራ በመሥራት፤ ትልቆች፣ ሽማግሌዎችና መካሪዎች የሌሉበት አገር ማድረግ ነው።

ሁለተኛው የትምህርት ሥርዓትን ማፍረስ ነው። መምህራን ቢቆጡ የማይሰማ፣ መምህራንን የማያከብር ትውልድ መፍጠር ነው። ሦስተኛው ቤተሰብ የሚባለውን ተቋም ማፍረስ ነው። እናት ጐረምሳ ልጇን ስትቆነጥጥ፣ ስትገስፅ አልፎ አልፎም በፍልጥ እያገላበጠች ስትደበድብ፤ ጐረምሳው የሚደበደበው ባጠፋው ጥፋት የሚሠጠው ቅጣት ተገቢ ነው ብሎ በማመን እንጂ፤ እናቱን መከላከል የሚያስችል አቅም ስለሌለው አይደለም።

ያ ስብእና ሲጐል፣ ቤተሰብ ሲፈርስ፣ የትምህርት ሥርዓት ሲፈርስ፣ ታላላቆች ሲጠፉና እንክርዳድ ሲበዛ፤ የአገር የመፍረስ አደጋ ያጋጥማል። አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ እንክርዳዱን ለመንቀል ብለን አብረን ስንዴውን እንዳንነቅል የምናደርገው ጥረት፣ ጥንቃቄ፤ አልፎ አልፎ ሕዝቦች መስማት ከሚፈልጉት አንፃር የሚሰለች ወይም ፈጥኖ ለማወቅ ፍላጐትና ጉጉት እንዲያድርባቸው የሚያደርግ ኾኗል።

በሌላ መንገድ በአጭር ጊዜ ውስጥ ድል ለማምጣት፣ በአጭር ጊዜ አልተገቡም የምንላቸውን ሰዎች ለማጥፋት በምንወስዳቸው ኦፕሬሽኖችም ሕዝብ እንዳይጐዳ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል።

የረዘመም ቢሆን ጥፋተኛን ብቻ የለየ፣ አብሮ ሕዝብን የማያጠቃ መኾን ይኖርበታል። ይህንን ማድረግ ካልቻልን ዘላቂ ሰላም ማረጋገጥ አንችልም። ደም እየተቃባን ነው የምንቀጥለው። ጉልበት ያለው እያደማ፤ የሌለው እየደማ የሚቀጥል ይኾናል።

እንግዲህ አገሪቱ፣ ሁላችሁም እንደምትገነዘቡት አሁን ያለነው 2012 የሚባል ዓመተ ምሕረት ላይ ነው። ነገር ግን አንዳንድ የእኛ ፖለቲከኞች ያሉት 1966 የሚባል ክፉ ጊዜ ላይ ነው። አገሪቷ ያለችበት ዘመንና ፖለቲከኞቻችን ያሉበት ቦታ ሊገናኝ አልቻለም። ለምሳሌ በወለጋ ተነሣ ለተባለው ችግር ሁላችሁም እንደምታውቁት በተማሪዎች ብቻ ሳይሆን፤ በሥራ አመራሮች፣ በመንግሥት የታጠቁ ኃይሎችና በባለሀብቶች ላይ ከፍተኛ ጥቃት ደርሷል። የታጠቁ ኃይሎችን በሙሉ ካሉበት ኑ በሰላም እንታገል ብለን፣ የጋበዝንበትን፣ የሔድንበትን ርቀት መናገር አያስፈልግም ስለምታውቁት።

በወለጋ አካባቢ፤ በጉጂ እንኳን የሚባለው እንኳን ቀንሷል። ጉጂ አካባቢ በነበረኝ ጉዞና ውይይት፤ ሕዝቡ በተደራጀ መንገድ ያንን ዐይነት ችግር መቀነስ መቻሉን ገልጾልኛል። ነገር ግን በምዕራብ ወለጋ አሁንም ተጨማሪ ሥራዎች የሚጠይቁ ነገሮች አሉ። እንዲህ ያለውን ነገር እንዴት ይፈታል ተብሎ ለቀረበው ጥያቄም “ቢፈታ ለአገር የሚበጀው፣ መልካም የኾነው በሰላማዊ መንገድ ብቻ ነው። ወንድም ወንድሙን የሚገልበት ጊዜ እኛ አገር ማብቃት ስላለበት፤ በጣም መልካሙ መንገድ በሰላማዊ መንገድ፣ በድርድር፣ በንግግር ችግሩን መፍታት ነው።”
“የአገር መከላከያ ጥቃት ሰንዝሮ አሥር ሰው ቢገል የሚያኩራራ አይደለም። ወንድሞቹን ነው የገደለው። ወይም በዛ በኩል ያለው ሰው ተማሪ ቢያግት፣ ሰው ቢገድል፤ የሚያኩራራ አይደለም። የራሱን ወገኖች ነው እየጎዳ ያለው። መፍትሔው ሰላማዊ መንገድ ነው። ነገር ግን በአንድ አገር ሁለት የታጠቀና ሁለት መንግሥት መኖር አይችልም። በአንድ አገር ያውም ለዴሞክራሲ እጇን የከፈተች አገር፣ ለዴሞክራሲ ልቧን የከፈተች አገር ስትሆን፤ ሰው በሐሳብ፣ በንግግር፣ በውይይት ጉዳዩን ቢጨርስ መልካም ነው። ከዚያ ውጭ ያለመንገድ አያዋጣም። አሸናፊ አያስገኝም። በመሐል ብዙ ንጹኀን ዜጐች፣ ሴቶች ይጐዳሉ። ያ እንዳይኾን በከፍተኛ ትዕግስት ለረዥም ጊዜ በተለያየ መንገድ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል። አሁንም ጥረቱ ይቀጥላል። ነገር ግን ሁለት መንግሥት ያለው አገር እንዳይኾን፤ ሕጋዊ መንግሥት ሕጋዊ እርምጃ መውሰዱ የግድ ይኾናል።

እርምጃ ይብቃ፣ በሰላም እንነጋገር፣ በሰላም እንፍታ የሚል ወይም ደግሞ ያንን ማድረግ እችላለሁ የሚል ኃይል ካለ ግን፤ በከፍተኛ ደስታ መንግሥት ይቀበላል። አሁን ያለው ችግር መንግሥትን በሁለት መንገድ አጣብቂኝ በማስገባት፤ ደካማ ለማድረግ መሞከር ነው። አንደኛው “ሰላም ማስከበር አልቻላችሁም፣ እርምጃ አልወሰዳችሁም” የሚል ትልቅ ድምፅ፤ ያው ሰው ራሱ መልኩን ቀይሮ ዳግም “በምዕራብ ወለጋ ትልቅ ኦፕሬሽን አድርጋችሁ ሕዝብ ጐዳችሁ” የሚል ድምፅ በማሰማት፤ በሁለቱም ጫፍ መንግሥትን አጣብቂኝ ውስጥ ለማስገባት መሞከር ነው።

የተከበረው ምክር ቤት ከግምት እንዲያስገባ የምፈልገው ከአንደኛው የሕዝብ ወገን በፍጥነት እርምጃ ወስዳችሁ አካባቢውን ንጹኅ ማድረግ አለባችሁ የሚል ግፊትና፤ ወታደሮቻችሁን አውጡ አትንኩን የሚለው ኃይል ለጊዜው ነው እንጂ መንግሥትን እያጠቃ ያለው፤ በሒደት ሕዝብን ከሕዝብ የሚያጋጭ ውጤት ነው የሚያመጣው። በአማራና በኦሮሞ መካከል የሚፈጠር ቅራኔን ወደ ከፋ ጫፍ የሚወስድ ነው። ለጊዜው የብልጽግና ፓርቲ አስተዳደር የገጠመው ፈተና ሊመስል ይችላል፤ በኋላ ግን ሁለቱን ሕዝቦች በከፍተኛ ቅራኔ ውስጥ የሚያስገባ ስለኾነ፤ ይህንን ፖለቲካ ብለው የሚጫወቱ ኃይሎች በማስተዋልና በጥበብ፤ የሕዝቦችን ግጭት በቀነሰ መልኩ የሚሠሩበትን መንገድ ቢከተሉ በጣም ጥሩ ይኾናል።

ሰው በማንነቱ ይታገታል ለሚለው ሐሳብ፤ ተማሪ ማንነት የለውም። ደምቢዶሎ የሔደ ተማሪ በሙሉ፤ አገሬ፣ ቤተሰቦቼ ጋር ሔድኩ ብሎ የሚያምን ነው። ጅቡቲ አልሔደም፤ ኬንያ አልሔደም፤ ሱዳን አልሔደም። ውኃ ቢጠማው፤ ጐራ ብሎ እማዬ ውኃ አጠጪኝ ብሎ የሚጠጣበት አገር ውስጥ ነው የሔደው።

ይህንን ሰው ማጥቃት ይህንን ሰው የፖለቲካ መሣሪያ ማድረግ፤ ነውር፣ አሳፋሪና ፀያፍ ተግባር ነው። በዚህ መንገድ የሚሠራ ፖለቲካ ምናልባት 1966 ዓ.ም. ይኖር እንደኾን እንጂ፤ ከ2010 በኋላ መሠረት የለውም። ይሄንን በዚህ ጉዳይ ላይ የሚሳተፉ ኃይሎች በሙሉ መገንዘብ ይኖርባቸዋል። በተለወጠ አገር ውስጥ ያልተለወጠ ሐሳብ ይዞ መቸገር፤ የአገሪቱን እድገት ያስተጓጉል እንደኾነ እንጂ፤ ብዙ ጥቅም የለውም። አሸናፊ አያደርግም። ለምንድነው እንዲህ የሚያጋጥመው የሚል ሐሳብ ሲነሳ ግን፤ በተዘጋ የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ ያለ ፖለቲከኛና ታስሮ የቆየ ጥጃ አንድ ናቸው። ጥጃው ሲፈታ፤ ቧርቆ፣ ቧርቆ የሚደክም አይመስለውም። ለ40 ዓመታት ታስሮና ታፍኖ የነበረ ፖለቲከኛ፤ ተከፈተ ሲባል ድንበሩን አያውቀውም። እንደዚህ ዐይነት መቧረቆች ጊዜያዊ ናቸው። ጥጃውም ደክሞ እናቱ ጉያ መግባቱ አይቀርም፤ ፖለቲካውም ረግቦ ወደቦታው መግባቱ አይቀርም። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ