ከፌዴራልና ከአዲስ አበባ መስተዳድር የተሻሩት የሕወሓት አባላት በትግራይ ተሾሙ
ዶ/ር ሰለሞን ኪዳኔ፣ ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሔርና አስመላሽ ወልደሥላሴ (ከግራ ወደቀኝ)
ወ/ሮ ፈትለወርቅ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የፍትሕና መልካም አስተዳደር ኃላፊ ኾኑ
ኢዛ (ረቡዕ ጥር ፳ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. January 29, 2020)፦ በቅርቡ ከፌዴራል መንግሥትና ከአዲስ ከተማ አስተዳደር በከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊነታቸው የተነሱት ሁለት የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት የትግራይ ክልላዊ መንግሥት ሹመት ሠጣቸው።
በክልሉ ምክር ቤት ሹመታቸው የጸደቀላቸው በፌዴራል መንግሥት የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የነበሩት ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሔርና በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ዘርፍ ኃላፊ የነበሩት ዶክተር ሰለሞን ኪዳኔ ናቸው።
የክልሉ መንግሥት ወይዘሮ ፈትለወርቅ በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የፍትሕና መልካም አስተዳደር ኃላፊ ኾነው መሾማቸውን አስታውቋል።
ዶ/ር ሰለሞን ደግሞ በቢሮ ኃላፊ ማዕረግ የትግራይ ከተሞች ክትትል ኃላፊ ኾነው እንዲያገለግሉ ስለመሾማቸው ይኸው መረጃ ያመለክታል።
የክልሉ ምክር ቤት ለሌላው የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና ከለውጡ በፊት በነበረው የፌዴራል መንግሥት ቁልፍ የኃላፊነት ቦታ የነበራቸውን አቶ አስመላሽ ወልደሥላሴን የትግራይ ክልል በይነ መንግሥታት ጽሕፈት ቤት በሚል ለተጠቀሰ ጽ/ቤት ኃላፊ ኾነው ተሹመዋል ተብሏል።
ወይዘሮ ፈትለወርቅ ከሁለት ሳምንት በፊት በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ በተጻፈ ደብዳቤ ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትርነታቸው መነሳታቸው የሚታወስ ነው። አሁን በትግራይ ክልል ከተሠጣቸው ሹመት ባሻገር የሕወሓት ምክትል ሊቀመንበር ናቸው። (ኢዛ)



