ኤርትራ አዲስ ኤምባሲ በአዲስ አበባ ልትገነባ ነው
ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ
ኢሳይያስና ዶ/ር ዐቢይ የመሠረት ድንጋይ አኑረዋል
ኢዛ (ዓርብ ታኅሣሥ ፲፯ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. December 27, 2019)፦ ኤርትራ በአዲስ አበባ አዲስ የኤምባሲ ሕንፃ ለመገንባት ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የመሠረት ድንጋይ አስቀመጡ።
በአዲስ አበባ ስድስት ኪሎ አካባቢ ከአሜሪካን ኤምባሲ በቅርብ ርቀት ላይ ለሚገነባው የኤርትራ ኤምባሲ አዲስ ሕንፃ የመሠረት ድንጋይ የተጣለው ታኅሣሥ 16 ቀን 2012 ዓ.ም. ነው። ግንባታው የሚካሔድበት ቦታ ለኤርትራ በነፃ የተሠጠ ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድም “የመገንቢያ ቦታው ለኤርትራ ሕዝብና መንግሥት በስጦታ የተሠጠ ነው” ብለዋል።
ለሁለት ቀን ይፋዊ ጉብኝት አዲስ አበባ የመጡት ኢሳይያስ አፈወርቂ በሁለት ቀናት ያልታሰቡ ያሉዋቸውን ክስተቶች ያገኙባቸው አለመኾኑን ገልጸዋል። ከዚህ የመሠረት ድንጋይ ማስቀመጥ ፕሮግራም ቀደም ብሎ አቶ ኢሳይያስና ዶ/ር ዐቢይ የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክን ጨምሮ በተለያዩ ቦታዎች ጉብኝት አድርገዋል።
ኤርትራ የራሷን መንግሥት ስትመሠርት የመጀመሪያውን ኤምባሲዋን የከፈተችው አዲስ አበባ እንደነበር አይዘነጋም። በወቅቱ ስቴዲየም አካባቢ የነበረውን ሕንፃ በደርግ ወቅት አኢወማ ሲገለገልበት የነበረ ነው። በሁለቱ አገሮች መካከል የነበረው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ሲቋረጥ፤ ይህ ስቴድየም አካባቢ የነበረው የኤርትራ ኤምባሲ ተዘግቶ እንደገና የተከፈተው ባለፈው ዓመት እንደነበር አይዘነጋም። ኾኖም በአሁኑ ወቅት በዋናነት የሚገለገለው መገናኛ አካባቢ ባለው ኤምባሲ ነው። (ኢዛ)



