Ethiopian Orthodox Epiphany

በየዓመቱ ጥር 11 ቀን በመላ አገሪቱ የሚከበረው በዓለ ጥምቀት

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተክርስቲያን ደስታዋን ገለጸች

ኢዛ (ሐሙስ ታኅሣሥ ፪ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. December 12, 2019)፦ ዛሬ ማለዳ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድን ለመቀበል ሽር ጉድ በሚባልበት ሰዓት፤ ኢትዮጵያውያንን የሚያስደስት ዜና ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተሰምቷል። “ሰበር ዜና” በሚል በተሠራጨ መረጃ፤ የጥምቀት በዓል የዓለም ቅርስ ኾኖ በዩኔስኮ መመዝገቡን የሚያበስር ነበር።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ ሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የጥምቀት በዓል አከባበር የማይዳሰስ ቅርስ ኾኖ እንዲመዘገብ ውሳኔ ያሳለፈው በኮሎምቢያ ቦጎታ በቅርስ ጥበቃ ጉዳዮች ላይ እያካሔደ ባለው ስብሰባ ነው።

ይህ ዜና ከተሰማ በኋላ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክት አስተላልፈዋል።

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በዚሁ መልእክታቸው፤ “ኢትዮጵያ ከምትታወቅባቸው አንዱ በየዓመቱ ጥር 11 ቀን በመላ አገሪቱ ዳር እስከ ዳር ከልሂቅ እስከ ደቂቅ በሕብረት፣ በአንድነት፣ በሰላም፣ በስምምነትና በፍቅር ታቦቱን አጅቦ፤ ፈጣሪውን እግዚአብሔርን እያመሰገነ በየወንዙ፣ በየአደባባዩና በየመንገዱ በፍጹም ደስታ የሚያከብረው በዓለ ጥምቀተ ክርስቶስ ነው” ብለዋል።

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት

በዓሉ በዩኔስኮ እንዲመዘገብ ቤትክሕነቷ፣ መንግሥትና መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ በተለይም የኢትዮጵያ ኦርቶዶከስ ተዋኅዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ሊቃውንትና ዐበይተ አገር ምሁራን፤ በአጠቃላይ ምዕመናን የማያቋርጥ ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸውን ፓትርያኩ አስታውሰዋል።

በመሆኑም ይህ የዘመናት ሕልም እና ጥረት በዛሬው ዕለት በእግዚአብሔር ፈቃድ እውን ሆኖ ስለተመዘገበ ለደስታችን ወሰን የለውም። … ይህ በዛሬው ዕለት የተፈጸመው ታሪካዊ ጉዳይ የቤተክርስቲያናችን፣ የአገራችንና የሕዝባችን ስም በዓለም ላይ ደምቆና ጐልቶ እንዲታወቅ የሚያደርግ ነው። … ይህም እውን ሊሆን የሚችለው መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ የአገሪቱ ባህልና የቱሪዝም ተቋም፤ እንዲሁም በየአገሩ የሚገኙ የቤተክርስቲያናችን መሪዎችና አምባሳደሮች ስለበዓሉ ታላቅነት፣ ተወዳጅነትና እሴት ያለማቋረጥ የማስተዋወቅ ሥራ ሲሠሩ እንደሆነ ግንዛቤ ሊወሰድበት ይገባል! ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት

የጥምቀት በዓል በዩኔስኮ መመገቡ ለአገራዊና ለሃይማኖታዊ ተልእኮ እውቅና ስለሚሠጥ፤ በዓሉን፣ ሃይማኖቱን፣ ባህሉንና አገሪቱን በማስተዋወቅ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የድርሻውን ይወጣ ዘንድ አሳስበዋል። ፓትርያርኩ አክለውም ሳምንቱ ኢትዮጵያውያን ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ በሠሩት ሥራ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና በማግኘት የተሸለሙበት መኾኑን አስታውሰው፤ በዓለ ጥምቀቱም በዩኔስኮ መመዝገቡ ልዩ ክስተት እንደኾነ ሳይገልጹ አላለፉም። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ