መንግሥት ያሰራቸውን ጋዜጠኞች በአስቸኳይ እንዲፈታ ተጠየቀ

ኢትዮጵያ ዛሬ (ኀሙስ ኅዳር ፰ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም. Nov. 17, 2016)፦ በምህጻረ ቃል ሲፒጄ በሚባል የሚታወቀው የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት ዛሬ ባወጣው መግለጫ በኢትዮጵያ ውስጥ እየተካሄደ ያለውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ የመንግሥትን አያያዝ የተቹ ጋዜጠኞች ለእስር መዳረጋቸውን አስታውሶ "በአስቸኳይ እንዲፈቱ" ሲል በአጽንኦት ጠይቋል።
"ጋዜጠኞችንና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች የሆኑ ግለሰቦችን ወህኒ በመጨመር የሚመጣ አገራዊ መረጋጋት የለም" ሲል የመንግሥትን ድርጊት የኮነነው መግለጫው፤ "ለንግግርና ለውይይት ሰፊ ቦታን መስጠት አስፈላጊ ነው" ሲል አትቷል።
ዞን ዘጠኝ በሚባል የሚጠራው የጦማሪያን ስብስብ መስራች የሆነው በፍቃዱ ኃይሉ ባለፈው ሣምንት ከመኖሪያ ቤቱ በፖሊስ ተወስዶ በምርመራ ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ እስካሁን ድረስ ምንም አይነት ክስ ለፍርድ ቤት አልቀረበም። ይሁን እንጂ አፍሪካ ኒውስ ኤጀንሲ ከቅርብ ሰዎች አገኘሁት ብሎ እንደዘገበው በፍቃዱ ለእስር የተዳረገው ለአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ መንግሥትን በመተቸት በሰጠው ቃለ መጠይቅ ሳይሆን እንዳልቀረ ነው።
መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመላ አገሪቱ በማወጅ ቁጥራቸው 12ሺህ የሚደርሱ ዜጎችን በተለያዩ የወታደር ካምፖስች ውስጥ አስገብቶ ያሰረ መሆኑን ገልጿል። ይሁን እንጂ እስረኞቹ በምን አግባብ እንደታሰሩና በምን አይነት ሁኔታ እየተያዙ እንደሆነ ዝርዝር መረጃ አልሰጠም።
ይህን ሁሉ ሁኔታ የታዘበ መሆኑን የገለጸው ሲፒጄ በፍቃዱ ኃይሉንና ሌሎች ጋዜጠኞች ይፈቱ ዘንድ ጠይቋል።



