በጀርመን ፍራንክፈርት የሻማ ማብራት ሥነሥርዓትና የፊርማ ማሰባሰብ ተካሄደ

Ethiopia Zare (ሰኞ መስከረም ፲፮ ቀን ፪፲፻፱ ዓ.ም. September 26, 2016)፦ በኢትዮጵያ በሥልጣን ላይ ያለው የወያኔ/ኢህአዴግ መንግሥት በኦሮሞ፣ በአማራና በተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች ውስጥ እየወሰደ ያለውን የመግደል፣ የማሰቃየትና የማሰር ተግባር በመቃወም፤ በጀርመን ሀገር ፍራንክፈርት ከተማ ቅዳሜ መስከረም ፲፬ ቀን ፪፲፻፱ ዓ.ም. ዕለት የሻማ ማብራት ሥነሥርዓት ተካሄደ። ይኸው ሥነሥርዓት የጀርመንዋ መሪ አንጌላ መርክል በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ የሚያደርጉትን ጉዞ እንዲሰርዙ የሚጠይቅ የፊርማ ማሰባሰብን ያካተተ እንደነበር ለኢትዮጵያ ዛሬ የደረሰው መረጃ ይጠቁማል።
በዚሁ ሥነሥርዓት ላይ የኃይማኖት አባቶች በሰላማዊ መንገድ ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ በኣጋዚ፣ በመከላከያ ሠራዊትና በፖሊስ ኃይሎች ሕይወታቸውን ላጡ ወገኖች ፀሎት ያደረጉ ሲሆን፤ ለቤተሰቦቻቸውም እግዚአብሔር መጽናናትን ይስጣችሁ ብለዋል።
በሥነሥርዓቱ ላይ ነዋሪነታቸው በጀርመን የሆኑ ኢትዮጵያውያን ውይይት ያካሄዱ ሲሆን፣ ወደመድረኩ የተጋበዙት ተናጋሪዎች በሀገሪቱ እየተካሄ ያለውን ሁኔታ ከማውገዛቸውም በላይ ምን መደረግ እንዳለበት የየበኩላቸውን ሃሳብ ሰጥተዋል።
ወ/ሮ አንጌላ መርክል በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ የሚያደርጉትን ጉዞ ይሰርዙ ዘንድ የሚጥይቅ የፊርማ ማሰባሰብ ላይ ከኢትዮጵያውያን በተጨማሪ ጀርመናውያንና የሌሎች ሀገር ዜጎች ተሳታፊ እንደነበሩ ለማወቅ ችለናል። (ይኽንኑ ሥነሥርዓት የሚያሳየውን ቪዲዮ ከዚኽ በታች ያገኙታል! ለመመለከት የማጫወቻ ቁልፉን ይጫኑ!)



