እሁድን በአራዳ ምድብ ችሎት
![]() |
|
ጽዮን ግርማ
This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. |
የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ለዛሬ የተቀጠሩትን ሦስቱ የዞን ዘጠኝ ጦማሪዎች አቤል ዋበላ፣ በፍቃዱ ኃይሉና ማኅሌት ፋንታሁን መዝገብ ለማየት የተሰየመው የተጠርጣሪዎቹ ቤተሰቦች ችሎት ሳይገቡ ነበር። ከመጀመሪያው ችሎት በኋላ ችሎቱ ባለው ቦታ ልክ ቤተሰብ እንዲገባ ተፈቅዶ የነበረ ቢኾንም ዳኛዋ የዕለቱን ሥራ ሲጀምሩ ስለዚህ ጉዳይ የሚያውት ነገር ያለ አይመስልም። ከመደበኛ የሥራ ሰዓት ውጪ የሚሰየሙት ዳኞች ተረኛ ዳኞች በመኾናቸው የዛሬዋ ዳኛም ለመዝገቡና ለጉዳዩ አዲስ ነበሩ።
የተጠርጣሪዎቹ ጠበቃ አቶ አመሐ መኮንን ኹኔታውን በመረዳት ቀደም ሲል የነበረውን አሠራር ለችሎቱ ጠቁመው ተጠርጣሪዎቹ ቤተሰቦቻቸው እንዲገቡላቸው ተፈቀደና ለአንድ ተጠርጣሪ አንድ ቤተሰብ እንዲገባላቸው ተደረገ።
ችሎቱ ሥራውን የጀመረውም ልክ እንደ ቅዳሜው ኹሉ የፖሊስን የተጨማሪ ጊዜ መጠየቂያ በማንበብ ነበር። ”ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ በወንጀል በሥነ ሥርዓት ሕጉ አንቀጽ 59/2 መሰረት የምርመራ ጊዜ ቀጠሮ ጠይቀን በምርመራ ላይ ነበሩ። ይሁን እንጂ እነዚህ ተጠርጣሪዎች ሚስጥራዊ በኾነ መንገድ በሕቡዕ በመደራጀት በሕጋዊ መንገድ ሥልጣን የያዘውን መንግሥት በሕገ ወጥ መንገድ ከሥልጣን ለማውረድ በማሰብ፣ ይህንንም ሐሳብ በውጭ አገር ከሚገኙ አሸባሪ ድርጅቶች ጋራ በመስማማትና አገሪቱን ለማተራመስ ትእዛዝ በመቀበል፣ ትእዛዙን ለማሳካት የሚያስችላቸውን ገንዘብ በመቀበል፣እንዲሁም ስልጠና በመውሰድ በአገሪቱ ላይ ብጥብጥ ለማነሳሳትና ብጥብጡንም ለመምራት በመንቀሳቀስ የሽብር ተግባር ፈፅመዋል። በመኾኑም ይህን የሽብር ተግባር ለማጣራት እንዲረዳን በፀረ ሽብር ዐዋጁ ቁጥር 652/2001 አንቀፅ 28 መሰረት ተጨማሪ 28 ቀናት የምርመራ ጊዜ እንዲሰጠን እንጠይቃለን” ሲል ፖሊስ ማመልከቻ አቅርቧል።
ጠበቃው አቶ አመሐ መኮንን በበኩላቸው፤ ”ፖሊስ ቀደም ሲል ሁለት ጊዜ በችሎት ሲያቀርባቸው ለጥርጣሬዬ ዋና ምክንያት ነው ያለው ተጠርጣሪዎች በማኅበራዊ ድረ-ገፅ ላይ በጻፉት ጹሑፍ በሚል እንጂ አንድም ጊዜ የሽብር ተግባር በመፈፀማቸው ነው ሲል አልተሰማም። ጉዳዩን ከሽብር አንጻር እየመረመረው እንደኾነም ገልፆ አያውቅም። ፍርድ ቤቱ ከመዝገቡ መረዳት እንደሚችለው ከዚህ በፊት በመደበኛው የወንጀል ሕግ የጊዜ ቀጠሮ ሥነ ሥርዓት አጠያየቅ መሠረት ዐሥራ አምስት ቀን ጠይቆ ዐሥር ቀን ተፈቅዶለታል። እንዲሁም የሽብር ዐዋጁን አንቀፅ ጠቅሶ አያውቅም። ፖሊስ በውጭ አገር ከሚገኝ አሸባሪ ድርጅት ጋር ከማለት በስተቀር የትኛው ድርጅት የሚለውን በስም እንኳን አልጠቀሰም። አሁን ከተጠርጣሪዎቹ በኩል ያለው መረጃ አለን ሁለቱንም ተጠርጣሪዎች ለአንድ ግዜም ቢኾ አግኝቼ አነጋግሬያቸዋለሁ። እነሱም ስለተደረገላቸው ምርመራ ሲነግሩኝ በጥያቄም ቢኾን ስለሽብር ተግባር ወይም ደግሞ አሸባሪ ስለሚባል ድርጅት የተጠየቁት አንድም ጥያቄ የለም የመለሱትም ነገር የለም። ሥልጠና ወሰዳችሁ የተባለውንም በሚመለከት ስልጠና የወሰዱት ”አርቲክል 19” እና ”ፍሪደም ሀውስ” ከተባሉ ድርጅቶች ነው። እነዚህ ድርጅቶች ደግሞ ከአሜሪካና ከእንግሊዝ መንግሥስት እውቅና የተሰጣቸው ሐሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ላይ የሚሠሩ ዓለም አቀፍ ሕጋዊ ድርጅቶች ናቸው። እነዚህ ድርጅቶች በኢትዮጵያም ቢኾን አሸባሪ ድርጅቶች ተብለው አልተፈረጁም። አሁንም ጉዳዩን ወደ ሽብር ከማዞር በስተቀር ለዚህ የሚያበቃ ምንም አዲስ የጨመረው መረጃ የለም”በማለት መከራከሪያቸውን አቀረቡ።
ዳኛዋ የምርመራ መዝገቡን ከመረመሩ በኋላ፤ ”ምን አዲስ ነገር አመጣችሁ?” በማለት ለፖሊስ ጥያቄ አቀረቡ። ፖሊስ፤ ”ፓስ ወርዳቸውን ተቀብለን ኢሜላቸውን ፈትሸናል ከዛም ውስጥ ከሽብርተኛ ድርጅት ጋር የተጻጻፉትን አግኝተናል” ሲሉ መለሱ። ዳኛዋም ”ይህ የምትሉት ከመዝገቡ ጋር ተያይዟል?” ሲሉ መልሰው ጠየቁ። ፖሊስ የተባለውን ከመዝገቡ ጋር አለማየያዙን እያረገ ያለው ምርመራ ግን ጉዳዩን ወደ ሽብር ተግባር እንዲያመራ እያደረገው መኾኑን በመጥቀስ ቢከራከርም ዳኛዋ፤ ”መዝገቡ እንደሚያሳየው መጀመሪያ ሲከፈት ከተከፈተበት የጥርጣሬ ምክንያት በተለያ የጠቀሳችሁት አዲስ ነገር የለም።” በማለት ፖሊስ በፀረ ሽብር ዐዋጁ ቁጥር 652/2001 አንቀፅ 28 መሰረት የጠየቀውን ተጨማሪ 28 ቀናት የምርመራ ጊዜ ቀጠሮ ከልክለው ዐሥራ አራት ቀን ፈቅደዋል።
ችሎቱ ከተጠናቀቀ በኋላ ከወትሮው በተለየ መልኩ ችሎቱን ለመታደም የመጣውን ሰው ፖሊስ ከግቢው በማስወጣት ተጠርጣሪዎቹ ከችሎት ሲወጡ ማንም እንዳያያቸው አድርጓል። ከግቢው ውጪ ኾኖ መውጣታቸውን ይጠባበቅ የነበረው ታዳሚ በመኪና ተጭነው ሲወጡ እጁን እያውለበለበ፣ ስማቸውን እየጠራና እያጨበጨበ ሸኝቷቸዋል።




