የ31 ዓመቱ ወጣት ረዳት አብራሪ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላንን ጠለፈ
”ጠላፊው ለአምስት ዓመታት በአየር መንገዱ አገልግሏል”መንግሥት
”በጠለፋው ሳይሆን ተሳፋሪዎቹን በማገቱ እስከ 20 ዓመት ሊያሳስር የሚችል ክስ ሊመሰረትበት ይችላል”የስዊስ አቃቤ ሕግ
Ethiopia Zare (ሰኞ የካቲት 10 ቀን 2006 ዓ.ም. Feb. 17, 2014)፦ ዛሬ ጠዋት ሮም ሊገባ የነበረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራ ”ኢቲ 702” በ31 ዓመቱ ረዳት አብራሪ ኃይለመድህን አበራ ተገኝ ተጠልፎ በስዊዘርላንድ፤ ጄኔቭ ከተማ ከንጋቱ 12 ሰዓት ላይ አረፈ። በጣሊያንና ስዊዘርላንድ ድንበር አካባቢ ሲደርስ በሁለት ተዋጊ ጀቶች ታጅቦ የነበረ ሲሆን፣ ረዳት አብራሪው በስዊዘርላንድ ጥገኝነት ጠይቋል። ተሳፋሪዎቹ አውሮፕላኑ መጠለፉን አያውቁም ነበር።
ትናንት ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት አካባቢ ከአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የተነሳው ይኸው መድረሻውን ጣሊያን ሮም ላይ የነበረው በረራ ”ኢቲ 702” ቦይንግ 767 ሲሆን፣ በውስጡ 202 ተሳፋሪዎችንና የአየር መንገዱን ሠራተኞች ጭኖ ነበር። አውሮፕላኑ ለበርካታ ደቂቃዎች በጄኔቭ አውሮፕላን ማረፊያ ሲያንዣብብ የነበረ ሲሆን፣ ሲያርፍ የሃያ ደቂቃ ነዳጅ ብቻ ቀርቶት እንደነበር የስዊስ ባለሥልጣናት ለመገናኛ ብዙኀን ገልጸዋል።

ረዳት አብራሪው አውሮፕላኑን የጠለፈው ዋናው አብራሪ ወደ መፀዳጃ ቤት በሄደበት ሰዓት የአብራሪዎቹን ክፍል ለብቻው ከውስጥ ሆኖ በመቆለፍ መሆኑ ታውቋል። አውሮፕላኑ መጠለፉን ለስዊስ ባለሥልጣናት የገለፀው ረዳት አብራሪው ኃይለመድህን ሲሆን፣ ጥገኝነት እንዲሰጠውና ለኢትዮጵያ መንግሥት አሳልፍው እንዳይሰጡት ጥያቄ ማቅረቡን የስዊስ ባለሥልጣናት አስታውቀዋል። አውሮፕላኑን ካሳረፈ በኋላ ከአብራሪዎቹ ክፍል ውስጥ በመስኮት በኩል በገመድ ተንጠላጥሎ በመውጣት እጁን ሰጥቷል።
በአውሮፕላኑ ውስጥ የነበሩት መንገደኞች አውሮፕላኑ መጠለፉን ያወቁት ጄኔፍ ካረፈ በኋላ ሲሆን፤ የስዊስ ፖሊሶች ተሳፋሪዎቹን ሁለቱንም እጆቻቸውን በጭንቅላቶቻቸው ላይ እንዲያደርጉ በማዘዝ ተራ በተራ እየፈተሹ የተዘጋጁ ተሽከርካሪዎች ላይ በመጫን ወደ መቆያ ክፍል መውሰዳቸው ታውቋል።
ንጋት 10፡40 ሮም ላይ ያርፋል ተብሎ ይጠበቅ የነበረው አውሮፕላን፤ በሰዓቱ እንደማያርፍና ነዳጅ ለመቅዳት ወደ ጄኔቭ አውሮፕላኑን እንዳዞረው ረዳት አብራሪው ለሮም አየር ማረፊያ መልዕክት ማስተላለፉ ታውቋል። በዚህን ጊዜ የስዊስ ባለሥልጣናት ጉዳዩን የሚያውቁ ቢሆንም፣ ሥራ የሚጀምሩት ጠዋት 2 ሰዓት ላይ በመሆኑ አውሮፕላኑ በተለይም በሌክ ኦፍ ጄኔቫ (ጄኔቫ ኃይቅ) አየር ክልል ላይ የበለጠ ሲያንዣብብ እንደቆየ ታውቋል።
የስዊስ ጋዜጠኞች እንዴት እንዲህ ባለው አስቸኳይ ጊዜ ሥራ አትጀምሩም በማለት በጥያቄ ያፋጠጧቸው የስዊስ አየር ኃይል ቃል አቀባይ ሎሮን ሳቫሪ ሲመልሱ፤ ”የሥራ ሰዓታችን ከጠዋቱ 2 ሰዓት እስከ 12 ሰዓት እና ከሰዓት በኋላ 7፡30 እስከ 11 ሰዓት ብቻ ነው፤ እኛ በማንሠራበት ሰዓት ጎረቤት ሀገሮቻችን እንዲረዱን ስምምነት ስለአለን ነው።” በማለት መልሰዋል።
”ኤርላይን ሪፖርተር ዶት ኮም” የተሰኘው ድረገጽ እንደዘገበው ከሆነ፤ ረዳት አብራሪው አውሮፕላኑን አሳርፎ የጥገኝነት ጥያቄውን እስቀሚያቀርብ ድረስ በስዊዘርላንድና በፈረንሳይ የአየር ክልሎች ላይ ሲያንዣብብ ነበር።

በጄኔቭ አቃቤ ሕግ የሆኑት አቶ ኦሊቭየ ዦርኖ እንደገለጹት ከሆነ፣ የስዊስ ባለሥልጣናት ጠለፋውን አስመልክቶ ጉዳዩን በጥልቀት እየመረመሩ መሆኑንና በአውሮፕላን ጠለፋው ሳይሆን ተሳፋሪዎቹን በማገቱ 20 ዓመት በእስራት ሊያስቀጣ የሚችል ክስ በረዳት አብራሪው ላይ ሊመሰረትበት እንደሚችል ጠቁመዋል። በስዊስ የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ውስጥ በአውሮፕላን የጠለፈን የሚያስቀጣ የሕግ አንቀጽ አለመኖሩን አክለው ገልጸዋል።
የጄኔቭ አውሮፕላን ማረፊያ ከጠለፋው ጋር በተያያዘ ለሁለት ሰዓታት ተዘግቶ እንደነበር ታውቋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት
ጉዳዩን አስመልክቶ የተጠየቁት የኢትዮጵያ መንግሥት ጉዳዮች ኮሙዩኒኬሽን ጽ/ቤት ሚኒስትሩ አቶ ሬድዋን ሁሴን የአውሮፕላኑን ረዳት አብራሪው አየር መንገዱ ውስጥ ለአምስት ዓመታት ማገልገሉን ገልፀዋል።

አቶ ሬድዋን “በሌላ መንገድ በሚመጣ መረጃ እስካልተረጋገጠ ድረስ እኛ ባለን መረጃ መሠረት ረዳት አብራሪው ሙሉ ጤነኛ ነው።” ብለዋል። ኃይለመድህን ስዊዘርላንድ ለመግባት የሚያስችል ሸንጋይ ቪዛ እንዳለውና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሠራተኛ በመኾኑ ነጻ ትኬት ማግኘት እንደሚችል በመግለጽ የትም ሀገር ሄዶ የመቀጠር ዕድል እያለው እንዲህ ማድረጉ እንዳስገረማቸው በንግራቸው ጠቁመዋል። አያይዘውም ”በፍርሃት አድርጎታል ሊያስብል የሚችል ምንም ዓይነት ወንጀል የለበትም” ብለዋል።
“እስካሁን ምን ፍላጎት እንዳለው አላወቅንም። ለዚህ ድርጊቱ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊም ኾነ ፖለቲካዊ ምክንያት ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም” ብለዋል።
አብራሪውን አሳልፎ መስጠትን በሚመለከት “ከስዊዘርላንድ መንግሥት ጋራ አሳልፎ የመስጠት የጋራ ስምምነት የለንም። ነገር ግን ሌሎች የተፈራረምናቸው ውሎች አሉን። በተጨማሪም በ1970 እ.ኤ.አ. የወጣውን የዓለም አቀፉን የበረራ ደህንነት ስምምነትን ስዊዘርላንድ በ1971 ኢትዮጵያ ደግሞ በ1979 ፈርመዋል። ለዚህ ሕግ ደግሞ የትኛውም ሀገር የመገዛት ግዴታ አለበት። ከዚህ አንጻር ተላልፎ የሚሰጥበት መንገድ ሊኖር ይችላል” ብለዋል። አቶ ሬድዋን ስዊዘርላንድ በመፈረምዋ ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅባታል ቢሉም፤ የስዊስ የመገናኛ ብዙኀን ግን ስለዚህ ስምምነት መኖር ከነጭራሹ ያልጠቀሱ ሲሆን፤ ከዚህም በላይ የስዊዘርላንድ አቃቤ ሕግ ሀገራቸው አውሮፕላን የጠለፈን የሚቀጣ ሕግ እንደሌላት መናገራቸውን ከላይ መጥቀሳችን ይታወቃል።
140 ጣሊያውያን፣ 11 አሜሪካውያን፣ 10 ኢትጵያውያ እና የኮንጎ፣ ስዊስ፣ ኢንግላንድ፣ ሩዋንዳ ዩክሬን፣ ጀመርን፣ ታንዛኒያ፣ ብራዚል እና ሌሎች ሀገር ዜጎች የተሳፈሩበት ይህ አውሮፕላን ስዊስ ካረፈ በኋላ መንገደኞቹን በሌላ አውሮፕላን ለማጓጓዝ ጥረት እየተደረገ እንደነበር በወቅቱ የገለጹ ሲሆን፤ ይኽንኑ ዜና አስመልክቶ ማምሻውን መንገደኞቹ ወደ ሮም መሄዳቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።
ከአንድ የውጭ ጋዜጠኛ “ረዳት አብራሪው የየት አካባቢ ሰው ነው?” ተብለው የተጠየቁት አቶ ሬድዋን “ኢትዮጵያዊ” ነው ሲሉ የመለሱት አቶ ሬድዋን “ጥያቄዬ ከየት ክልል?” በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ “ተወልዶ ያደገበትን አካባቢ አላውቅም” ሲሉ መልሰዋል።

ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ መንግሥት መሆኑን በማስታወስ በርካታ የመገናኛ ብዙኀን የኢትዮጵያ መንግሥት በሰብዓዊ መብት ጥሰት ግንባር ቀደም ከሆኑት የዓለም መንግሥታት ተርታ መሰለፉን ሳይጠቁሙ አላለፉም።
ሒዩመን ራይትስ ዎች የተሰኘው ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋም በበኩሉ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት የሰብዓዊ መብት ለበርካታ ተከታታይ ዓመታት ያለማቋረጥ እያየለ መምጣቱን ገልጾ፤ በነፃነት ሃሳብን መግለጽ፣ መሰብሰብ፣ መደራጀት፣ … የመሳሰሉት መሠረታዊ የሰው ልጅ ነፃነቶች እንደማይከበሩ አስታውቋል። የኢትዮጵያ መንግሥት ጋዜጠኞችን፣ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችንና ደጋፊዎቻቸውን፣ እንዲሁም የኃይማኖት ተቋማትን ሁሉ ያለማቋረጥ በማጥቃትና በማሰቃየት ላይ እንደሆነ ተገልጿል።



