በስዊዘርላን ኒዮን ከተማ የሚካሄደው የኢትጵያውያን ፌስቲቫል ዛሬ ይጠናቀቃል
ያሬድ ክንፈ ከኒዮ፣ ስዊዘርላንድ (ጥቂት ፎቶግራፎች ይዘናል)
Ethiopia Zare (ቅዳሜ ሐምሌ 13 ቀን 2005 ዓ.ም. July 20, 2013)፦ ረቡዕ ሐምሌ 10 ቀን 2005 ዓ.ም. (ጁላይ 17፣ 2013) በኒዮን የስዊዘርላንድ ከተማ የተጀመረው 11ኛው የአውሮፓ የኢትዮጵያውያን የስፖርትና የባህል ፌስቲቫል ዛሬ ቅዳሜ ይጠናቀቃል። ከተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት፣ ከሰሜን አሜሪካ፣ ከኢትዮጵያ እንዲሁም ከተለያዩ አህጉራት የመጡ በርካታ ኢትዮጵያውንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ለበዓሉ ድምቀት አስተዋጽዖ አድርገዋል።
ይህ በአውሮፓ የኢትዮጵያውያን ፌስቲቫል ላለፉት 11 ዓመታት በተከታታይ ሲካሄድ የቆየ ሲሆን፣ በአህጉሪቱ የሚገኙና ከሌሎች አህጉራትም ጭምር በመሰባሰብ በርካታ ኢትዮጵያውያን የሚሳተፉበትና በድምቀት የሚያከብሩት ፌስቲቫል ነው።
በዚህ ፌስቲቫል ይሳተፋሉ የተባሉት የእግር ኳስ ቡድኖች በአንደኛ ዲቪዚዮን 18 ሲሆኑ፣ በአራት ምድብ ተከፍለዋል። በሁለተኛ ዲቪዚዮን ደግሞ 8 ቡድኖች በሁለት ምድብ ተከፍለው ውድድሩን አካሂደዋል። ከአውሮፓ 24 ቡድኖች፣ ከዩናይትድ ስቴትስ አንድ እና ከደቡብ አፍሪካ አንድ ናቸው።
በአንደኛው ዲቪዚዮን በምድብ አንድ ኢትዮ-ሽቱትጋርት፣ ኢትዮ-ኢታሊ፣ ኢትዮ-ስዊድን፣ ኢትዮ-ሎንዶን፤ በምድብ ሁለት ኢትዮ-ኮሎን፣ ኢትዮ-በርሚንጋም፣ ኢትዮ-ፍራንክፈርት፣ ኢትዮ-ዙሪክ፣ ኢትዮ-ናይል ሎንዶን፤ በምድብ ሦስት ደግሞ ኢትዮ-ኖርዌይ፣ ኢትዮ-ስዊዝ፣ ኢትዮ-ካታንጋ፣ ኢትዮ-ሙኒክ የተመደቡ ሲሆን፤ የምድብ አራቶቹ ደግሞ ኢትዮ-ቱሉዝ፣ ኢትዮ-ሮማ፣ ኢትዮ-ቤልጂየም፣ ኢትዮ-ኑረምበርግ እና ኢትዮ-ሆላንድ ነበሩ።
በሁለተኛ ዲቪዝዮን ምድብ አንድ የነበሩት ኢትዮ-በረገን፣ ኢትዮ-አሜሪካ፣ ኢትዮ-ፊንላንድ፣ ኢትዮ-ስካንዲኔቪያን ሲሆኑ፤ በምድብ ሁለት ደግሞ ኢትዮ-ኦስትሪያ፣ ኢትዮ-ሙኒክ 2፣ ኢትዮ-ፍራንስ፣ ኢትዮ-ደቡብ አፍሪካ ናቸው።
ከአንደኛ ዲቪዝዮን በዚህ ውድድር ሳይሳተፉ የቀሩት ሦስት ቡድኖች ሲሆኑ፣ እነርሱም አምስተርዳም፣ ስቱትጋር እና ኢትዮ-ካታንጋ ከሎንዶን ናቸው። ከሁለተኛ ዲቪዝዮን ደግሞ ማልታ እና ደቡብ አፍሪካ ሲሆኑ፤ የደቡብ አፍሪካው ቡድን በቪዛ ችግር ምክንያት አለመሳተፉን ለመረዳት ችለናል።
ኒዮን ከተማ እስከ ማክሰኞ ድረስ ከ20 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በላይ ፀኃያማ የነበረች ሲሆን፣ ከረቡዕ እስከ ዓርብ ቀን ከ20 እስከ 28 ዲግሪ ሙቀት የነበራት ቢሆንም ከሰዓት በኋላ ከ17 ሰዓት (በኢትዮጵያ 11 ሰዓት) ጀምሮ የማያቋርጥ ዝናብ ሲዘንብ ቆይቷል። ዝናቡ በመጠኑም ቢሆን በሥፍራው የነበረውን ህዝብ አውኮታል። ከዚህም ባሻገር ዓርብ ዕለት የነበሩት የከሰዓት በኋላው የአንደኛ ዲቪዝዮኑ የግማሽ ፍጻሜ ሁለት ውድድሮች እና የሁለተኛ ዲቪዝዮኑ የፍጻሜ ውድድር ተሰርዘው ለቅዳሜ እንዲሻገሩ ተደርገዋል።
ይህንኑ አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ዛሬ ድረ ገጽ ለቀረበላቸው ጥያቄ የፌዴሬሽኑ ሊቀመንበር አቶ ዮሐንስ መሰለ እና የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው አቶ ግርማ ሣህሎ (የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን ተጫዋች) ሲመልሱ፤ መብረቅና ኃይለኛ ነፋስ የቀላቀለ ዝናብ በመኖሩ እና ከአየር ንብረት ትንበያው እንደተረዳነው ጨዋታውን አቋርጠን ለቅዳሜ ማሸገር ግድ ብሎናል ብለዋል።
ከረቡዕ እስከ ዓርብ ዕለት በአራት ምድብ የተከፈሉት የአንደኛ ዲቪዚዮን ቡድኖች ባደረጉት ጨዋት ለግማሽ ፍፃሜ የደረሱት ቡድኖች ኢትዮ-ስዊድን ከሎንዶን እና ኢትዮ-ስዊዝ ከኢትዮ-ኖርዌ ናቸው። በሁለተኛው ዲቪዝዮን ለፍጻሜው የደረሱት ኢትዮ-ፊንላንድ እና ኢትዮ-ፍራንስ ናቸው።
በዚህ ፌስቲቫል ላይ በክብር እንግድነት የተጋበዙት የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ እግር ካስ ቡድን ተጫዋችና አሠልጣኝ የነበሩት አቶ ወርቁ ደርገባ ሲሆኑ፣ ባደረጉት ንግግር ለፌስቲቫሉ ያላቸውን መልካም ምኞት ገልጸዋል።
በእንዲህ ዓይነት ፌስቲቫሎች እንደሚዘወተረው ሁሉ የምግብ፣ የመጠጥ፣ የቡና፣ መጻሕፍት እንዲሁም የኢትዮጵያን ባህል የሚያስተዋውቁ አልባሳትና ቁሳቁሶች ሲሸጡ ነበር። ከዚህም ሌላ ኢትዮጵያ ዛሬን ጨምሮ ከተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ጋዜጠኞች የተገኙ ሲሆን፣ አርቲስትና አክቲቪስት ታማኝ በየነም ተገኝቷል።
ቅዳሜ ማምሻውን ለአሸናፊ ቡድኖች ዋንጫና ሜዳሊያ በመስጠት የሜዳው ፌስቲቫል የሚጠናቀቅ ሲሆን፣ ሌሊቱን ደግሞ ድምጻዊ ቴድሮስ ካሣሁንን (ቴዲ አፍሮ) በፌዴሬሽኑ አማካኝነት ኮንሰርት እንዳለው ለመረዳት ችለናል።
ከረቡዕ እስከ ዓርብ ድረስ የነበረው ዝግጅት ምን ይመስል እንደነበር በዝግጅቱ ላይ በመገኘት ያነሳናቸውን ፎቶግራፎች ልናካፍላችሁ ወደድን፤ እነሆ! (ለፎቶግራፎቹ መግለጫ በእያንዳንዱ ፎቶ ላይ የኮምፒዩተርዎን መጠቆሚያ ሲያውሉ ያገኙታል። ተጨማሪ ፎቶግራፎችን በቀጣዮቹ ሪፖርቶች ለማቅረብ እንሞክራለን።)
ቀን አንድ (ረቡዕ ሐምሌ 10 ቀን 2005 ዓ.ም.)
ቀን ሁለት (ሐሙስ ሐምሌ 11 ቀን 2005 ዓ.ም.)
ቀን ሦስት (ዓርብ ሐምሌ 12 ቀን 2005 ዓ.ም.)



