ጥሩነሽ ዲባባ ደግሞ ነኀስ

አትሌት መሰረት ደፋር በ5000 ሜትር የለንደኑን ኦሎምፒክ በአሸናፊነት ስትወጣ Meseret Defar of Ethiopia celebrates winning gold in the Women's 5000m Final

Ethiopia Zare (ዓርብ ነኀሴ 4 ቀን 2004 ዓ.ም. August 10, 2012)፦ አትሌት መሰረት ደፋር ዛሬ ማምሻውን በለንደን ኦሎምፒክ በተካሄደው የአምስት ሺህ ሜትር የሴቶች ሩጫ ውድድሩን በአንደኝነት በመጨረስ የወርቅ ሜዳሊያ ስታገኝ ጥሩነሽ ዲባባ ደግሞ ሦስተኛ በመውጣት የነኀስ ሜዳሊያ አግኝታለች። ገለታ ቡርቃ ደግሞ አምስተኛ ሆናለች።

 

 

መሰረት ደፋርና ጥሩነሽ ዲባባ የወርቅና የነኀስ ሜዳሊያ ማግኘታቸውን አረጋግጠው በደስታ ተቃቅፈው Meseret Defar of Ethiopia celebrates with Tirunesh Dibaba of Ethiopia after winning

በእ.ኤ.አ. 2000 በቤጂንግ በተካሄደው የሴቶች 5 ሺህ ሜትር ውድድር አትሌት መሰረት ደፋር ሦስተኛ በመውጣት የነኀስ ሜዳሊያ ያገኘች ሲሆን አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ ደግሞ የወርቅ ሜዳሊያ ማግኘቷ ይታወሳል። በዘንድሮው የለንደኑ ኦሎምፒክ ሁለቱ አትሌቶች ደረጃቸውን ተቀያይረዋል። ውድድሩ ከፍተኛ ፉክክር የታየበትም ነበር።

 

በዚህ ውድድር ሁለተኛ፣ አራተኛ እና ስድስተኛ የወጡት ኬንያውያን ሲሆኑ፣ ውድድሩን ከአንድ እስከ ስድስተኛ በመውጣት አፍሪካውያኑ የኢትዮጵያና የኬንያ አትሌቶች በርቀቱ የአንበሣ ድርሻውን ተቀራምተውታል።

 

አትሌት መሰረት ደፋር ውድድሩን ስታሸንፍMeseret Defar of Ethiopia celebrates winning gold

አትሌት መሰረት ደፋር የአሸናፊነት የወርቅ ሜዳሊያዋን ካጠለቀች እና አበባ ከተቀበለች በኋላ የኢትዮጵያ ባንዲራ ሲሰቀልና የህዝብ መዝሙሩ ሲደመጥ ከንፈሮችዋ እየተንቀጠቀጡ በደስታ አልቅሳለች።

 

መሰረት ደፋር በ5000 ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤትነቷን ካረጋገጠች በኋላ Meseret Defar of Ethiopia celebrates winning gold in the women's 5000m Finalውድድሩን በ15፡04፡25 ደቂቃ በአንደኝነት የጨረሰችው መሰረት ደፋር ስትሆን፣ ሁለተኛ የወጣችው ኬንያዊቷ ቪቪያን ጄፕኬሞይ ቼሩዮት በ15፡04፡73 ደቂቃ፣ ሦስተኛ የወጣችው ኢትዮጵያዊቷ አቴሌት ጥሩነሽ ዲባባ በ15፡05፡15 ደቂቃ፣ አራተኛዋ ኬንያዊት ሳሊ ጄፕኮሰጊ ኪፕዬጎ በ15፡05፡79 ደቂቃ፣ ኢትዮጵያዊቷ ገለታ ቡርቃ በ15፡10፡66 ደቂቃ፣ እንዲሁም ኬንያዊቷ ቪኦላ ጄላጋት ኪቢዎት በ15፡11፡59 ደቂቃ ውድድሩን በተከታታይ ጨርሰዋል።

 

አትሌት መሰረት ደፋር ከውድድሩ በኋላ ከጋዜጠኞች ለቀረቡላት ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥታለች። ውድድሩ ቀለል ብሏት እንደነበር፣ ውድድሩ ሊፈፀም 150 ሜትር እስከሚቀረው ድረስ ማድፈጥዋንና ከዚያ በኋላ ግን ተፈትልካ እንደወጣች ገልፃለች። ”ባለቤቴ ”ከ150 ሜትር በፊት እንዳትወጪ” ብሎ ባስጠነቀቀኝና በመከረኝ መሠረት እስከ 150 ሜትር ድረስ ተፈትልኬ ሳልወጣ ቀርቻለሁ። የባለቤቴን ምክር በመስማቴ ለአሸናፊነት በቅቻለሁ። እግዚአብሔር ይመስገን!” በማለት ለጋዜጠኞች ምላሽ ሰጥታለች።

 

አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ በዚህ በለንደኑ ኦሎምፒክ ለኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ ከማግኘቷም በላይ ለሀገሯ ሦስተኛውን የነኀስ ሜዳሊያ አግኝታለች።

 

የሴቶች 1500 ሜትር

ነዋሪቷ ስዊድን የሆነውና ጥንድ ዜግነት ያላት ኢትዮጵያዊቷ አትሌት አበባ አረጋዊ በሴቶች የ1500 ሜትር ውድድሩ ሊፈፀም አስራ አምስት ሜትር አካባቢ እስኪቀረው በሁለተኝነት ስትመራ ቆይታ እግሮቿ ተደናቅፈውባት ሚዛንዋን መጠበቅ ተስኗት በተፎካካሪዎችዋ ተቀድማ ውድድሩን በ5ኛነት ፈፅማለች።

 

አትሌት አበባ አረጋዊ ውድድሩ ሊፈፀም አንድ ዙር ሲቀረው አፈትልካ ልትወጣ ጥረት በምታደርግበት ጊዜ ሌሎች አትሌቶች አደናቅፈዋት ልትወድቅ የነበረ ቢሆንም፤ ሚዛንዋን በመጠበቅና የተቻላትን ጥረት በማድረግ አፈትልካ ወጥታ ነበር። በዚህ ድንቅፍቅፍ ውስጥ አንዲት አትሌት ልትወድቅ ችላለች።

 

ነዋሪነትዋ በስዊድን የሆነችው አትሌት አበባ አረጋዊ ሐማርቢ ለሚባለው የስዊድን ክለብ ተሰላፊ መሆንዋን ኢትዮጵያ ዛሬ ድረ ገጽ ለመረዳት ችላለች።

 

አትሌት አበባ አረጋዊን ቀድመዋት ከገቡትና ሦስተኛ የወጣቸው አትሌት በትውልድ ኢትዮጵያዊ የሆነችው ማሪያም ዩሱፍ ጀማል አንዷ ነች።

 

ኢትዮጵያ በለንደን ኦሎምፒክ የሜዳሊያ ሰንጠረዥ ደረጃ

በለንደኑ ኦሎምፒክ የሴቶች 5000 ሜትር ከተጠናቀቀ በኋላ ኢትዮጵያ በሦስት የወርቅ እና በሦስት የነኀስ ሜዳሊያዎች በሀገሮች የሜዳሊያ ደረጃ ሠንጠረዥ 22ኛ ላይ ትገኛለች። የወርቅ ሜዳሊያዎቹን ያገኙት አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ በ10 ሺህ ሜትር፣ አትሌት ቲኪ ገላና በሴቶች ማራቶን እና አትሌት መሰረት ደፋር በ5000 ሜትር ናቸው። የነኀስ ሜዳሊያዎቹን ያገኙት ደግሞ አትሌት ታሪኩ በቀለ በ10000 ሜትር፣ አትሌት ሶፊያ አሰፋ በ3000 ሜትር የሴቶች መሰናክል እንዲሁም አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ በ5000 ሜትር ናቸው።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ