በሴቶች ማራቶን አትሌት ቲኪ ገላና ክብረወሰን በመስበር ወርቅ አገኘች

Ethiopia Zare (እሁድ ሐምሌ 29 ቀን 2004 ዓ.ም. August 5, 2012)፦ በለንደኑ ኦሎምፒክ በዛሬው ዕለት በተካሄደው የሴቶች ማራቶን ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ቲኪ ገላና ውድድሩን በ2፡23፡07 ሰዓት አንደኛ ወጥታ በመጨረስ የወርቅ ሜዳሊያ ከማግኘቷም በላይ የኦሎምፒክ ክብረወሰንን ሰብራለች።

በሴቶች ማራቶን የኦሎምፒክ ክብረወሰን 2፡23፡14 ሰዓት የነበረ ሲሆን፣ የተመዘገበውም በ2000 እ.ኤ.አ. በተካሄደው በሲድኒው ኦሎምፒክ በጃፓናዊቷ አትሌት ናዑኮ ታካሃሺ ነበር። ዛሬ አትሌት ቲኪ ገላና ሰዓቱን በሰባት ሰከንድ አሻሽላ የኦሎምፒክን ክብረወሰን ሰብራለች።

በዚህ ውድድር የተሳተፉት ሦስት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ሲሆኑ፣ አትሌት ማሬ ዲባባ በ2፡28፡48 ሰዓት ውድድሩን በ23ኛነት ጨርሳለች። አትሌት አሰለፈች መርጊያ ደግሞ ውድድሩን በ2፡32፡03 ሰዓት በመጨረስ 42ኛ ወጥታለች።
ኬንያዊቷ ፕሪስቻ ጄፕቱ በ2፡23፡12 ሰዓት ሁለተኛ በመውጣት የብር ሜዳሊያ ስታገኝ፣ ሩሲያዊቷ ታቲያና ፔትሮቫ ደግሞ በ2፡23፡29 ሰዓት ሦስተኛ በመውጣት የነኀስ ሜዳሊያ አግኝታለች። ኬንያዊቷ ማሪያ ጄፕኮሰጌ ኬታኒ ደግሞ በ2፡23፡56 ሰዓት በመግባት ውድድሩን በአራተኝነት ጨርሳለች።
ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ቲኪ፣ ኬንያውያኖቹ ፕሪስቻ እና ማሪያ እንዲሁም ሩሲያዊቷ ታቲያና አርባውን ኪሎ ሜትር ሳይለያዩ ሲሮጡ የነበሩ ሲሆን፣ ውድድሩ ሁለት ኪሎ ሜትር ሲቀረው አራተኛ የወጣችው ኬንያዊቷ ማሪያ ትንሽ ወደኋላ ስትቀር ሦስቱ አትሌቶች ሳይለያዩ አንድ ኪሎ ሜትሩን ዘልቀዋል።

ውድድሩ አንድ ኪሎ ሜትር ሲቀረው ግን ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ቲኪ ገላና ቀድማቸው በመውጣት የማሸነፍ ብቃቷን ከማሳየቷም በላይ ለኢትዮጵያም እና ለራስዋ የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ ከማስገኘቷም በተጨማሪ የክብረወሰን ባለቤት ለመሆን በቅታለች።
በለንደን ኦሎምፒክ የኢትዮጵያ ደረጃ
በለንደኑ ኦሎምፒክ የሴቶች ማራቶን ከተጠናቀቀ በኋላ ኢትዮጵያ በሁለት የወርቅ እና በአንድ የነኀስ ሜዳሊያዎች በሀገሮች የሜዳሊያ ደረጃ ሠንጠረዥ 19ኛ ላይ ትገኛለች።
ኢትዮጵያ በኦሎምፒክ የሴቶች ማራቶን
የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት በኦሎምፒክ የማራቶን ሜዳሊያ ያስመዘገበችው ፋጡማ ሮባ ስትሆን፣ እ.ኤ.አ. በ1996 አትላንታ ላይ ተደርጎ በነበረው ኦሎምፒክ አንደኛ በመውጣት የወርቅ ሜዳሊያ በማግኘት ነበር። ከዚያ በፊትም ሆነ በኋላ ኢትዮጵያ በሴቶች የኦሎምፒክ ማራቶን ምንም አይነት ሜዳሊያ ያላገኙ ሲሆን፣ አትሌት ቲኪ ገላና ሁለተኛዋና የኦሎምፒክ ክብረወሰን ለመስበር በቅታለች።



