የክራር ንግስቷ አስናቀች ወርቁየቀብር ሥነ-ሥርዓቷ ነገ በሥላሴ ቤተክርስቲያን ይፈጸማል

Ethiopia Zare (ሐሙስ መስከረም 4 ቀን 2004 ዓ.ም. September 15, 2011)፦ ”የክራሯ ንግሥት” በመባል የምትታወቀው አንጋፋዋ የመድረክ ባለሙያ አስናቀች ወርቁ በ76 ዓመቷ ለረዥም ጊዜ በሕክምና ስትረዳ ከቆየች በኋላ ሕይወቷ አለፈ።

 

አስናቀች ወርቁ በተለያዩ የጥበብ ዘርፎች በመሳተፍ የመድረክ ባለሟልነቷን ያረጋገጠች ከመሆኗም በላይ ከሙዚቃው ባሻገር በመድረክ፣ በፊልም፣ በሥነ ግጥምና ዜማ ዘርፎች ከመሳተፏም ሌላ አንጋፋ ከሚባሉት ድምጻውያን አንዷ እንደነበረች ይታወቃል።

 

አስናቀች በማዘጋጃ ቤት ቲያትር በ1945 ዓ.ም. በታየው “የፍቅር ጮራ” በተሰኘው ቲያትር ለመጀመሪያ ጊዜ በመድረክ ላይ የተወነች እንስት ተዋናይት ከመሆኗም በላይ፤ ሕይወቷ እስካለፈችበት ወቅት ድረስ ክራሯ ከጎኗ እንዲቀመጥላት በማድረግ ለክራር የነበራትን ታላቅ ክብር የገለጸች መሆኗ ይታወቃል።

 

አስናቀች ወርቁ በሕፃንነት ዘመኗ ለክራር በነበራት ፍቅር የተነሳ የመጀመሪያ ክራሯን በ25 ሣንቲም በመግዛት ማንጎራጎር ስትጀምር፤ ለክራር ያላትን ጥልቅ ፍቅር እስከ ዕለተ ሞቷ ከጎኗ በማድረግ ገልጻለች። አርቲስቷ ከ30 ዓመታት በላይ በብሔራዊ ቲያትር አገልግላ ጡረታ መውጣቷ ይታወቃል።

 

የአርቲስት አስናቀች ወርቁ ቀብር ሥነ-ሥርዓት ነገ አርብ በቅዱስ ሥላሴ ቤተክርስቲያን ከቀኑ ስድስት ሰዓት እንደሚፈጸም ለመረዳት ተችሏል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ