”አዲሱ ዓመት ለኢትዮጵያ በአንድነት የምንሠራበት ዘመን ሊሆን ይገባል” ዳኛ ብርቱካን ሚደቅሳ
ዳኛ ብርቱካን አዲሱን ዓመት በስዊድን ከኢትዮጵያውያን ጋር አሳለፉ
ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ የአዲስ ዓመት የመልካም ምኞት መግለጫ አስተላለፉ

Ethiopia Zare (ሰኞ መስከረም 1 ቀን 2004 ዓ.ም. September 12, 2011)፦ ዳኛ ብርቱካን ሚደቅሳ በስዊድን ዋና ከተማ ስቶክሆልም ከኢትዮጵያውያን ጋር አዲሱን ዓመት ለመቀበል በተዘጋጀ ልዩ ዝግጅት ላይ በመገኘት በስደት ላይ ለሚገኙና በሀገር ውስጥ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የአዲስ ዓመት የመልካም ምኞታቸውን ገለጹ። ዜጎችን ያስጎነበሰውን የየሀገራቸውን ሥርዓት ለሁልጊዜ እንደቀየሩት ህዝቦች ሁሉ፤ በአዲስ ተስፋ፣ በአዲስ ሃሳብ ለኢትዮጵያ በአንድነት የምንሠራበት ዘመን ሊሆን ይገባል ሲሉ ተናገሩ።
በስዊድን የሚገኘው የኢትዮጵያ ድምፅ ራዲዮ 18ኛ ዓመቱን ምክንያት በማድረግ የኢትዮጵያን ሁለት ሺህ አራት ዓ.ም. አዲስ ዓመት አስታክኮ ቅዳሜ ጳጉሜን 5 ቀን 2003 ዓ.ም. (ሴፕቴምበር 10 ቀን 2011 እ.ኤ.አ.) ባዘጋጀው ልዩ የአዲስ ዓመት መቀበያ ዝግጅት ላይ በክብር እንግድነት የጋበዘው ዳኛ ብርቱካንን ከልጃቸው ከሕፃን ሐሌ ሚደቅሳ ጋር ነበር።

ዝግጅቱን ”እንኳን አደረሳችሁ!” በማለት በንግግር የከፈቱት የኢትዮጵያ ራዲዮ ድምፅ የሥራ አስኪያጅ ኮሚቴው ሰብሳቢ የሆኑት አቶ እንዳለ ወልደሥላሴ፤ በዝግጅቱ ላይ ከልጃቸው ጋር አህጉር አቋርጠው በክብር እንግድነት የተገኙትን ወ/ት ብርቱካንን አመስግነዋል። ዛሬ ራዲዮኑ ለደረሰበት ደረጃ ላለፉት 18 ዓመታት የደከሙትን በሙሉ በሥራ አስኪያጅ ኮሚቴውና በራሳቸው ስም ያላቸውን ታላቅ አክብሮት ገልጸዋል።
ዳኛ ብርቱካን ከ647 ቀናት ረዥም የእስር ቆይታ በኋላ ባለፈው ዓመት መስከረም 26 (ኦክቶበር 6 ቀን 2010 እ.ኤ.አ.) ከእስር ከተፈቱ በኋላ የመጀመሪያቸውን የእንቁጣጣሽ በዓል ያከበሩት በስዊድን ከሚገኘው ኢትዮጵያዊ ማኅበረሰብ ጋር ነው። ዳኛ ብርቱካን ይህንን አስመልክተው፤ ”ከአስቸጋሪ የእስር ቆይታ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የማከብራትን የዛሬዋን እንቁጣጣሽ ከምወዳችሁ በስዊድን እና አካባቢዋ ከምትኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር ላሳልፍ በመቻሌ ደስታዬ ለከት የለውም። ...” በማለት ተናግረዋል።

በዚህ ዝግጅት ላይ ከስዊድን እና ከአካባቢው ሀገራት በርካታ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች የተገኙ ሲሆን፤ ከዚህም በተጨማሪ የስዊድን የፓርላማ አባል፣ የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ አባል፣ በአውሮፓ ካውንስል የስዊድን የልዑክ ቡድን አባል የሆኑት የስዊድን ሶሻል ዴሞክራት ፓርቲ ተወካይ ወ/ሮ ካሪና ሄግ በዝግጅቱ ላይ ተገኝተዋል። በርካታ ሕፃናት ከቤተሰቦቻቸው ጋር በመገኘት የዚህ በዓሉ ተቋዳሽ ነበሩ። ከታዋቂ ኢትዮጵያውያን መሃል ደግሞ ታላቁ ገጣሚና ባለቅኔ ኃይሉ ገብረዮሐንስ (ገሞራው) ይገኝበታል።

ልዩ ዝግጅቱ የቀን እና የማታ ፕሮግራሞች የነበሩት ሲሆን፤ የቀኑ ዝግጅት የቡፌ የምሳን ጨምሮ የዘመናዊ የሀገር ባህል ልብስ ዕይታ (ፋሽን ሾው)፣ የሕፃናት ልዩ የችሎታ ውድድር (ታለንት ሾው) ቀርበውበታል። ከዚህም ሌላ ነዋሪነታቸው በስዊድን የሆኑት ”ወለላዬ” እና ”ማራኪ” በሚል የብዕር ስም የሚታወቁት ገጣምያን በጋራ ቅብብሎሽ የግጥም መነባንብ አሰምተዋል። ከሕፃናት ደግሞ አሃዱ ማትያስ ግጥሙን አቅርቧል። በኢትዮጵያ ትያትር ቤቶች ታዋቂ የነበሩ ተወዛዋዦች ደግሞ የተለያዩ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ውዝዋዜዎችን አሳይተዋል። በምሽቱ ዝግጅት ላይ ደግሞ ድምፃዊ ግርማ ገመቹ የምሽት ታዳሚዎቹን ሲያዝናና ማምሸቱን ለመረዳት ችለናል።

ዳኛ ብርቱካን ከልጃቸው ሕፃን ሐሌ ሚደቅሳ ጋር ከሚኖሩበት ከሰሜን አሜሪካን በክብር እንግድነት በስዊድን በተጋበዙበት በዚህ ዝግጅት ላይ ያደረጉትን ሙሉ ንግግር እና የመልካም ምኞታቸውን መግለጫ ከዚህ በታች አቅርበነዋል።
የዳኛ ብርቱካን ሚደቅሳ ንግግር
መልካም አዲስ ዓመት/እንቁጣጣሽ!
ከአስቸጋሪ የእስር ቆይታ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የማከብራትን የዛሬዋን እንቁጣጣሽ ከምወዳችሁ በስዊድን እና አካባቢዋ ከምትኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር ላሳልፍ በመቻሌ ደስታዬ ለከት የለውም።
ስለዚህም በዚህ በደመቀ በዓል ላይ እንግዳ ሆኜ እንድገኝ የጋበዘኝን በስዊድን የኢትዮጵያውያን ማኅበርን እጅግ አድርጌ ላመሰግን እወዳለሁ። ከዚህም በላይ ከእስር ሰንሰለት ወጥቼ የዛሬዋ የነፃነት ቀን የእኔ እንድትሆን አቅማችሁ የፈቀደውን ሁሉ በማድረግ ከፍተኛ ተጋድሎ ስታደርጉ ለቆያችሁ ወገኖቼ ከፍተኛ ምስጋናዬን አቀርባለሁ። እግዚአብሔር ይስጥልኝ!
አዲስ ዓመት ሲመጣ ሁላችንም መጪውን ዘመን በአዲስ ተስፋ፣ በአዲስ ጉልበት እና በአዲስ ሃሳብ መቀበልን እናስባለን። ይህ ነገር በእኛ ባህል ብቻ ያለ ተግባር አይመስለኝም። እዚህ በምዕራቡ ዓለም የሚገኙ ህዝቦችም የሚያደርጉት ይህንኑ ነው። በእኛ ዘንድ ግን ዕሳቤው ትንሽ ለየት ያለ ይመስለኛል። እንደ ሀገርና እንደ ህዝብ የዓመታት መፈራረቅ ያላስቀረው፣ የመከራና የስቃይ ታሪክ ባለቤቶች በመሆናችን በአዲሱ ዘመን አዲስ ነገርን ለማየት እየተመኘንም እንኳን በጭንቅላታችን ጀርባ ’ምን ዋጋ አለው እንደድሮው ነው’፣ በማለት ስናንጎራጉር ኖረናል። ይህን የሚያሳየኝን የባህል ትውስታዬን ላካፍላችሁ።
ሁላችሁም እንደምታውቁት እንቁጣጣሽ በዓል ከማንም በላይ ለሕፃን ሴት ልጆች የፈንጠዝያ ጊዜ ነው። እኔም እንደማንኛውም ሕፃን የእንቁጣጣሽ ቀን ነግቶ እስከአየው አያስችለኝም ነበር። መንጋቱ አይቀርምና በበዓሉ ቀን ትንሽዋን ከበሮአችንን ይዘን በመንደራችን እንዞራለን። ከሀሴቴ ብዛት ልቤ በአፌ የምትወጣ ይመስለኝ ነበር። ይህን የልጅነት ደስታ ደመና የሚያጠላበት ነገር ግን አላጣሁም። ዜማው ተጀምሮ አበባየሆሽ ለምለምን ስንቀባበል በዘፈኑ አጋማሽ ላይ አንድ ግጥም ትመጣለች፣ ...
ንፍሮ ቀቅዬ ብላ ብለው፣
ጉልቻ አንስቶ ጎኔን አለው፤
ከጎኔም ጎኔን ኩላሊቴን፣
እናቴን ጥርዋት መድኃኒቴን፤ ...
በልጅነት ዕዝነ ሕሊናዬ፣ የዛችን ሴት በጉልቻ የደቀቀ ጎን አስብ ነበር። እናም ይከፋኛል። የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት የሀገራችንን ጎን ካነከተው፣ ቅስሟን ከሰበረው፣ ካለፈ ስቃይ ትዝታችን አያላቅቀንም። ይዘነው ወደ መጪው ዓመት መጓዛችን የማይቀር መሆኑንም እናስባለን።
በአንድ በኩል አይፈረድብንም። ዓለም የት በደረሰበት በዚህ ዘመንም እንኳን፣ ዛሬም የሀገራችን ልጆች በልቶ ማደር ወደ ጠፍር የመምጠቅን ያህል ርቆባቸዋል። ምን አልባትም አንዳንዶቹ ዛሬ በዓል መሆኑንም ዘንግተውት ይሆናል። በረሃብ ጣር ተይዘዋልና። ይኸውስ የተፈጥሮ ፍርጃ ነው እንል ይሆናል። ለነገሩ የተፈጥሮ ሳይሆን፣ ሀገሪትዋን ለዓመታት የተፈናጠጡባት የገዥዎችዋ ችግር ነው። ይባስ ተብሎ ሀገርህ ላይ በሠላም ልትኖር የምትችለው፣ አስብ ያልንህን ስታስብ፣ ተናገር ያልንህን ስትናገር፣ አድርግ ያልንህን ስታደርግ ብቻ ነው ተብሎ ኩሩ ኢትዮጵያዊ አንገቱን ተሰንጎ ይኖራል። ይህን እምቢ ያለውንም ማሰር ሰለቸኝ በሚለው፣ በእርግጥ ግን ሰልችቶት በማያውቀው ሥርዓት እስር ቤቶች ይበሰብሳል።
ዛሬ ጋዜጠኛ ርዕዮት ዓለሙ ሊኖሩበት ቀርቶ ሊያዩት በሚያፀይፈው የስታሊኑ ጉላግ አምሳያ በሆነው በማዕከላዊ እስር ቤት ታፍጋ አዲስ ዓመትን ታሳልፋለች። ጥፋትዋ ጠንካራ ሰብዕናዋ፣ እንደሰው ለመኖር መወሰንዋ ነው። የፖለቲካ እስረኛ የሆኑት የሌሎቹ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ታሪክም ከዚህ የተለየ አይደለም።
ወገኖቼ! ሀገራችን የዓመታት ሰቆቃ እግራችንን ሊጎትተን፣ መልካምን ነገር ለሀገራችን ከማለምና ከመመኘት ሊያቆመን አይገባም። የሰው ልጅ ታሪክ እንዳሳየን እንደዚሁ እልህን ያስጨረሱ፣ የዜጎችን ልብ ያሸነፉ የመሰሉ ቁጥር የለሽ ታሪካዊ ሁኔታዎች በትክክለኛው ወቅትና ጊዜ እንዳልነበሩ ሆነው ተቀያይረዋል። ለወገኖቻችን እንግልት ምክንያት የሆኑትን ክስተቶች ደጋግሞ በመንገዳችን እያመጣ ተስፋችንን የተፈታተነው ጊዜ በሌላው ተራ ደግሞ ለትውልድ እፎይታ የሚሆንን እውነታ አምጥቶ ያለፈውን ሁሉ ተረት ያደርገዋል። ይህ የሚኖነው ግን የሁሉ ሀብት የሆነውን ጊዜ ቁጭ ብለን ስንጠብቀው አይደለም። ጊዜን፣ አዲስ ዓመትን የእኛ አጋር፣ የበጎ ተግባር አስፈፃሚ ልናደርገው የምንችለው፤ ከዛሬ አሻግረን የተሻለን ነገን እስካለምን ለህልሙም እውንነት እስከጨከንን ጊዜ ብቻ ነው።
የምወዳችሁ ኢትዮጵያውያን! ይህ አዲስ ዓመታችን ልብን አዝሎ ያው እንደድሮ ነው የማለት ወቅት ሊሆን አይገባም። ለሀገራቸው የፍትሕና የነፃነት በጎ ሃሳብ አጥርተው አስበው፣ የሀገራቸውንና የራሳቸውን መፃዒ ዕድል በራሳቸው እጅ አስገብተው፣ በሀገራቸው ለዘላለም የተተከለ ይመስል የነበረውን፣ ዜጎችን ያስጎነበሰውን የየሀገራቸውን ሥርዓት ለሁልጊዜ እንደቀየሩት ህዝቦች ሁሉ፣ በአዲስ ተስፋ፣ በአዲስ ሃሳብ ለሀገራችን በአንድነት የምንሠራበት ዘመን ሊሆን ይገባል።
በስዊድንና አካባቢው ነዋሪ ለሆናችሁ ወገኖቼ፣ እንዲሁም በሀገር ቤትና በውጭ ሀገር ለምትኖሩ ኢትዮጵያውያን መልካም አዲስ ዓመት እንዲሆንላችሁ ከልብ እመኛለሁ። ሀገራችን ኢትዮጵያም ሠላምና ፍትሕ የሚሰፍንባት ሀገር ትሁንልን!
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!
ኢትዮጵያን እግዚአብሔር ይባርክ!



