የአውራምባ ታይምስ ም/ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ ታሰረ
”ጉዳዩ ከጋዜጣዋ ጋርም ሆነ ከሙያው ጋር ተያያዥነት የለውም” የመንግሥት የፀጥታ ተቋማት
”ጋዜጠኛው ለእስር የተዳረገበትን ምክንያትና የሚገኝበትን ሁኔታ መንግሥት ያሳውቀን” አውራምባ ታይምስ
Ethiopia Zare (ማክሰኞ ሰኔ 14 ቀን 2003 ዓ.ም. June 21, 2011)፦ የአውራምባ ታይምስ ም/ዋና አዘጋጅ የሆነው ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ እሁድ ሰኔ 12 ቀን 2003 ዓ.ም ከቀኑ 9፡00 ሰዓት አካባቢ በርካታ ቁጥር ባላቸው የፀጥታ ኃይሎች ተይዞ ከመኖሪያ ቤቱ መታሰሩን አውራምባ ታይምስ ከቤተሰቦቹ ማረጋገጡን ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታወቀ።
እንደ አውራምባ ታይምስ መግለጫ ከሆነ፤ ጋዜጠኛው በቁጥጥር ስር ሲውል መኖሪያ ቤቱ ተበርብሮ የተለያዩ ሰነዶች፣ ሲዲዎች፣ ካሜራዎች፣ የአውራምባ ታይምስ የተለያዩ ዕትሞች መወሰዳቸውንም ለማረጋገጥ ተችሏል።
የአውራምባ ታይምስ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ጋዜጠኛ ውብሸት የታሰረበትን ምክንያት እንዲገለጽለት ለሚመለከታቸው የመንግሥት የፀጥታ ተቋማት ጥያቄ አቅርቦ በትናንትናው ዕለት ባገኘው ምላሽ ”ጉዳዩ ከጋዜጣዋ ጋርም ሆነ ከሙያው ጋር ተያያዥነት የለውም” የሚል ምላሽ ማግኘቱን አስታውቋል። ጋዜጠኛ ውብሸት የታሰረበት ምክንያት በተጨባጭ ይህ ነው ተብሎ አለመገለጹ እጅግ እንዳሳሰበው የአውራምባ ታይምስ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል በመግለጫው አክሎ ገልጿል።
የም/ዋና አዘጋጁ መታሰር በተቀሩት የጋዜጣዋ ባልደረቦች ሥነልቦና ላይ መረበሽን በመፍጠሩ፤ በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጠውን ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ከግምት በማስገባት ጋዜጠኛው ለእስር የተዳረገበትን ምክንያት እንዲሁም የሚገኝበትን ሁኔታ መንግሥት እንዲያሳውቀን ሲል የአውራምባ ታይምስ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ጠይቋል።



