Ethiopia Zare (ሐሙስ ሚያዝያ 13 ቀን 2003 ዓ.ም April 21, 2011)፦ በካናዳ ዋና ከተማ ኦታዋ በያዝንው ወር ቅዳሜ ሚያዚያ 30 ቀን ለኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቭዥን ማጠናከሪያ የሚሆን የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ፣ አርቲስት ታማኝ በየነና የተለያዩ የካናዳ የፖለቲካ ሰዎች በተገኙበት እንደሚካሄድ ተገለጸ።

ይሄው በመናገሻዋ የሚካሄደው የገንዘብ ማሰባሰቢያ ዝግጅትን ከሌሎች የገንዘብ ማሰባሰቢያዎች ለየት የሚያደርገው፡ "በካናዳ በመጭው ወር ለሚደረገው የካናዳ ምርጫ ብዙ ጊዜ በጠባብ ልዩነት የሚሸናነፉትን ፓርቲዎች በኢትዮጵያ ነጻ የመገናኛ ብዙሀንን አስፈላጊነት ለማስረዳትና ለዴሞክራሲ ለሚደርገው ትግል አጋር ለማድረግ ጥሩ አጋጣሚ መሆኑ ነው" ሲሉ አዘጋጆቹ ገልጸዋል። በዚህ ዝግጅት ላይ ታዋቂው ፖለቲከኛ እና የዩኒቨርስቲ መምህር ዶ/ር ብርሀኑ ነጋና አርቲስት ታማኝ በየነ በክብር እንግድነት ተገኝተው ንግግር የሚያደርጉ ከመሆኑም በላይ በተለይ በአሁኑ ሰዓት በካናዳ ሀገር አቀፍ ምርጫ የሚሳተፉ የተለያዩ ፖለቲካ ድርጅቶች እጩ ተመራጮችም በስፍራው ተገኝተው ውይይት እንደሚያደርጉ ለማወቅ ችለናል። ብዙ ኢትዮጵያዊያን እንደሚሳተፉበት የሚገመተው ስብሰባ ላይ ነጻና ግልጽ የጥያቄና መልስ ጊዜ እንደሚኖር አዘጋጆቹ አብራርተዋል። ካናዳ የዳኝነት ስርአቱን ከማሻሻያ እንስቶ በተለያዩ ፕሮግራሞች በኢትዮጵያ በየአመቱ ከ200 ሚሊዮን ዶላር በላይ እንደምታፈስ ሲታወቅ ይህ ገንዘብ የታሰበለትን የዳኝነት ስርአት ከማሻሻል ይልቅ የዳኝነት ስርአቱን በማማሰን፣ የዜጎችን መብት በመጣስና የመገናኛ ብዙሀንን በማፈን ላይ እንደሚውል በኦታዋ ዩኒቨርስቲ የአለምአቀፍ ህግ ተማሪ ወጣት ተክለሚካኤል አበበ ገልጿል። ለምሳሌ በቅርቡ አንድ ኢትዮጵያዊ ካናዳዊ ዘመዶቹን ለመጎብኘት ወደ ሀረር ሄዶ እንደታሰረና ከሁለት ሳምንት በላይ ፍርድ ቤት እንዳልቀረበ፤ በተመሳሳይ መልኩም ሙክታል በሺር የተባለ የኦጋዴን ኢትዮጵያዊ ካናዳዊ የ2006ቱን የሕወሀት የሶማሊ ወረራ ተከትሎ ከኬንያ ታፍኖ ተወስዶ መታሰሩንና እስካሁንም በመጥፎነቱ በሚታወቀው ፍርድቤት እድሜ ልክ ተፈርዶበት በእስር ቤት እየማቀቀ እንደሆነ ይታወቋል። ዋንኛው የገንዘብ ማሰባሰቢያ ዝግጅት ቅዳሜ ሚያዚያ 30/2011 ከ1pm ጀምሮ በኦታዋ ዋናው ቤተመጻህፍት የሚደረግ ሲሆን ከአርብ ማታ ጀምሮ ግን ከተጋባዥ እንግዶቹ ጋር በአገራዊና አለማቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት እንደሚካሄድም ታውቋል።

ኢሳት በኢትዮጵያ ውስጥ በቀጥታ የሚተላለፍ የመጀመሪያው ነጻ ቴሌቭዥን ሲሆን በኢትዮጵያ መንግስት በተደጋጋሚ የስርጭት ማወኪያ ሞገድ ሲጠቃ መቆቱና ኢሳትም በተደጋጋሚ የስርጭት ሳተላይት እንዲቀይር መገደዱ ይታወሳል። 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ