ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና የ2010 የአሜሪካ የብዕር ተሸላሚ ሆነ
በሎስ አንጀለስ ከተማ፣ በካሊፎርንያ ግዛት የሚገኘው ዕውቁ የፔን ዩ.ኤስ.ኤ. (Pen USA) የፀሐፍትና ጋዜጠኞች ዓለም አቀፍ ማኅበር ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌናን የ2010 ዓ.ም. . ‘ፍሪደም ቱ ራይት’ የተሰኘው ሽልማት አሸናፊ መሆኑን ይፋ አደረገ።
የሽልማቱ ሥነ ሥርዓት ረቡዕ ኅዳር 8 ቀን 2003 ዓ.ም. . (ኖቨምበር 17 ቀን 2010 እ.ኤ.አ.) በሎስ አንጀለስ ከተማ ቤቨርሊ ሂልስ ሆቴል ውስጥ እንደሚካሄድ ሲታወቅ፤ በዕለቱም ጄምስ ሳልተር፣ ሔንሪ ዊንክለር፣ ሊን ኦሊቨር፣ ሂው ሃፍነር እና አስራ ሁለት በሙያቸው ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደረጉና ሕዝባዊ ዕውቅና ያተረፉ አሜሪካውያን ፀሐፍት በተለያዩ ዘርፎች ሽልማታቸውን እንደሚቀበሉ ከፔን ጽሕፈት ቤት የወጣው መግለጫ አስታውቋል።
የፔን ዩኤስኤ 20ኛውን የሽልማት ሥነ ሥርዓት በሚያከብርበት በዚህ በዓል ላይ የኢትዮጵያ ነፃ ጋዜጠኞች ማኅበር (ኢነጋማ) የሥራ አስፈጻሚ አባል የሆነው የኢትኦጵ ጋዜጣ አዘጋጅና ባለቤት ሲሳይ አጌና ለሽልማት የበቃው በሙያው ላሳየው ወደር የሌለው ፅናትና ከፍተኛ አስተዋጾ መሆኑን መግለጫው ገልጿል። የፔን የሥራ አስፈጻሚ አባል የሆኑት አቶ ኤልያስ ወንድሙ “ይህ ሽልማት የኢትዮጵያ ህዝብ የሰብዓዊና የዜግነት መብቱ ለሆነው የመጻፍና የመናገር ነፃነቱ ለሚያደርገው ትግል የአለም አቀፍ ማኅበረሰብን ታላቅ ድጋፍ ያሳያል” ብለዋል።
ሲሳይ አጌና በኢትኦጵ ጋዜጣ አዘጋጅነቱ ሣቢያ ከ1987 ዓ.ም. እስከ 1998 ዓ.ም. ለስድስት ጊዜያት በተለያየ ምክንያት የታሰረ ሲሆን፣ ከእነዚህ የእስር ጊዜያት ውስጥ ከህዳር 1988 ዓ.ም. ጀምሮ ለአንድ ዓመት በፍርድ ሲታሰር፣ ቀሪውን ሁለት ዓመት የታሰረው ያለፍርድ እንደነበር ይታወሳል። የኢትኦጵ ጋዜጣ በመንግሥት እስከታገደበት ህዳር ወር 1998 ዓ.ም. ድረስ ለአሥራ ሁለት ዓመታት በተከታታይ ኢትዮጵያውያን አንባቢዎቹን ሲያገለግል የቆየ ሲሆን በሀገራችን የጋዜጣ ህትመት ታሪክ ውስጥ አንድ መቶ ሰላሳ ሺ ኮፒ በማሳተም ቀዳሚ ሥፍራን የያዘና በህዝቡ ዘንድ እጅግ ተወዳጅና ተነባቢ እንደነበረ ይታወቃል።
በ1998 ዓ.ም. ሲሳይ አጌና እና እስክንድር ነጋ በብቸኛ የጭለማ እስር ቤት በሚንገላቱበት ጊዜ ፔን ዩ.ኤስ.ኤ. የ2006 ዓ.ም. የክብር አባል አድርጎ ሰይሟቸው እንደነበር ይታወሳል። ምርጫ 97ን ተከትሎ የታሰሩት ጋዜጠኞች ከተፈቱ በኋላ ግን መንግሥት ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌናን፣ እስክንድር ነጋን እና ሰርካለም ፋሲልን ጨምሮ በፖለቲካ ውሳኔ የህትመት ሥራ ፈቃድ በመከልከል በሞያቸው ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን እንዳያስተዳድሩ አግዷቸዋል። ምንም እንኳን ጋዜጣ አሳትመው በሰፊው ህዝቡን እንዳያገለግሉ ቢታገዱም በሀገሪቱ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ አሁንም ሞያዊ ግዴታቸውን እየተወጡ እንደሆነ በየጊዜው ለንባብ የሚበቁት ጽሑፎቻቸው ዋቢ ምስክር ናቸው።
ይህንኑ በማስመልከት በስደት የሚገኙት የኢነጋማ ፕሬዝዳንት አቶ ክፍሌ ሙላት ለፔን ዩ.ኤስ.ኤ. ባስተላለፉት መልዕክት፤ “ይህ ሽልማት በአቋሙ ጽናትና አይበገሬነት ለማደንቀውና ለማከብረው የሞያ ባልደረባዬ ሲሳይ አጌና ብቻ ሳይሆን፤ በትግሉ የመጀመሪያ ረድፍ ለተሰለፉና ለነፃው ፕሬስ ህልውና መስዋዕት ለሆኑ ሁሉ መታሰቢያ፣ ለትውልድና ለታሪክም ክቡር ቅርስ ነው” ብለዋል።
ከፔን ‘ፍሪደም ቱ ራይት’ ሽልማት ተሸላሚዎች መካከል ኩባዊው ራኡል ሪቬሮ፣ ሟቿ ሩሲያዊት አና ፖሊስካያ፣ የአሜሪካ የቤተ መጻሕፍት ማኅበር እና በኢትዮጵያ መንግሥት የታገደው ኢነጋማ የሚጠቀሱ ናቸው።



