ከ30 በላይ አንጋፋና ወጣት ምሁራን ይሳተፉበታል

Ethiopia Zare (ሐሙስ መጋቢት 30 ቀን 2002 ዓ.ም. April 8, 2010)፦ “ኢትዮጵያ ከየት ወዴት?” በሚል ርዕስ ዋና የመወያያ አጀንዳውን ሠላም፣ ፀጥታ፣ ዲሞክራሲና መልካም አስተዳዳርን ያደረገ በርካታ ኢትዮያዊያንና የውጭ ሀገር ምሁራን ጥናታዊ ጽሑፋቸውን የሚያቀርቡበት አውደ ጥናት ሊካሄድ ዝግጅቱ እንደተጠናቀቀ ምንጮቻችን ገለጹ።

 

በጉባዔው ላይ በአፍሪካ ቀንድና በኢትዮጵያ በተለይ አሉ በሚባሉ በአስተዳደር ችግሮች፣ ሠላምና የዜጎች ደህንነትን ጨምሮ ዘላቂ እድገትን ለማምጣት በሚቻልበት ጉዳዮች ላይ የጥናትና የምርምር ውጤቶች እንዲሁም የትግል ሃሳቦች እንደሚቀርቡ ለማወቅ ተችሏል።

 

በአውደ ጥናቱ ላይ በተለይ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊ እንዲሁም የመሬት ለባዕዳን ባለሀብቶች መሸጥ የሚያስከትለው ቀውስና የመፍትሔ ሃሳቦች፣ የብሔር ጉዳዮችና መፍትሔዎቻቸው፣ ኢትዮጵያ ያመለጧት ወርቃማ የለውጥ ዕድሎች፣ የህዝቦች መቻቻልና ሃሳብን በነፃነት የመግለጥ መብትን የሚመለከቱ ንግግሮች የሚቀርቡ ሲሆን፤ ከመላው ዓለም የተሰባሰቡ ባለሙያዎች፣ የፖለቲካ መሪዎች፣ ጋዜጠኞችና የሲቪክ ማኅበራት አመራሮችን ጨምሮ በርካታ የውጭ ሀገር ምሁራንና የመንግሥት ባለሥልጣናት እንደሚገኙ ታውቋል።

 

የስብሰባው አዘጋጆች በቃሊቲ እስር ቤት የምትገኘው ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳን የጉባዔው የክብር ሊቀመንበር አድርገው የሰየሟት ሲሆን፤ ብርቱካን ራሷ የመወያያ ርዕስ እንደምትሆን ተገልጿል። በስብሰባው ላይ የኢትዮጵያ ህዝብ የትግል አጋር የሆኑትና የአውሮፓ ፓርላማ አባል ፖርቱጋላዊቷ ወ/ሮ አና ጎሜዝ (ሃና ጎበዜ) እንደሚገኙም ለማወቅ ተችሏል።

 

ይሄንኑ በመጭው ዓርብ፣ አፕሪል 9 ቀን 2010 እ.ኤ.አ. የሚከፈተውና እሁድ የሚጠናቀቀው አውደ ጥናት ስኬታማ ለማድረግ ረዥም ጊዜ የወሰደ ዝግጅት የተደረገበት ሲሆን፤ ውይይቱ እንዳይካሄድና ስኬታማ እንዳይሆን አንዳንድ መቀመጫቸውን ውጭ ሀገር ያደረጉ የፖለቲካ ድርጅቶችና የገዥው ፓርቲ አባላት ለስብሰባው መሳካት ከፍተኛ እርዳታ ለሚያደርጉት ተቋማት አደናቃፊ ደብዳቤዎችን በመጻፍ ከፍተኛ ሽር ጉድ ሲያደርጉ እንደነበር አዘጋጆቹ ገልጸዋል።

 

በስብሰባው ላይ የቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ንግግር የሚያደርጉ ሲሆን፤ በስብሰባው የመጨረሻ ዕለት ከፖለቲካ መሪዎችና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች እንዲሁም ጋዜጠኞች ጋር ህዝባዊ ውይይት ይካሄዳል።

 

በስብሰባው ላይ ከሚገኙት ምሁራንና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች መካከል ፕሮፌሠር መሳይ ከበደ፣ አምባሳደር እምሩ ዘለቀ፣ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ፣ አቶ ኦባንግ ሜቶ፣ ዶ/ር አረጋዊ በርሄ፣ አርቲስት ታማኝ በየነ፣ ወጣት ተክለሚካኤል አበበ፣ ፕሮፌሠር አለማየሁ ገ/ማሪያም፣ አቶ አክሎግ ቢራራ፣ ወ/ሮ ዋሲ ተስፋ፣ ዶ/ር መስማኩ አስራት፣ … ጥቂቶቹ ናቸው።

 

በተያያዘ ዜናም ሰኞ አፕሪል 12 ቀን በዋሽንግተን የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ፊት ለፊት ብርቱካን ሚደቅሳና ሌሎች የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ የሚጠይቅና አሜሪካ ከህወሓት አገዛዝ ጋር ያላትን ሰብዓዊ መብትንና ዲሞክራሲን የሚያገል ግንኙነት የሚቃወም ታላቅ የተቃውሞ ሰልፍ እንደሚደረግ ተገልጿል። (ለተጨማሪ መረጃ የአዘጋጆቹን ድረ ገጽ እዚህ በመጫን ይጎብኙ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ