‘ዘመቻው ተጧጡፎ ቢቀጥልም መድረኩም ሆነ ዓረና ከምርጫው አይወጡም’ አቶ ገብሩ አስራት

Ethiopia Zare (ረቡዕ መጋቢት 1 ቀን 2002 ዓ.ም. March 10, 2010)፦ ኢንጂንየር ግዛቸው እና አቶ ስየ አብርሃ ወደ መቀሌ የሚያመሩት እሁድ መጋቢት 5 ቀን 2002 ዓ.ም. መድረክ በትግራይ በሚያደርገው የምርጫ ቅስቀሳ ላይ ተሳትፎ ለማድረግና በትግራይ ክልል የድርጅታቸውን የምርጫ ሂደት ለመከታተል መሆኑን በአዲስ አበባ የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች ጠቆሙ።

 

በተያያዘም አቶ ገብሩ አሥራት የዓረና ሊቀመንበር አስቀድመው በርዕስ መስተዳድርነት ይመሯት ወደነበረችው ትግራይ መንቀሳቀሳቸውን የመድረኩ ምንጮች ገልጸዋል።

 

አቶ ገብሩ አስራት የፓርቲያቸው ዕጩ ከተገደሉ በኋላ በተለያዩ የመገናኛ ብዙኀን በመቅረብ ማብራሪያ ከመስጠታቸውም በላይ የስድስት ልጆች አባት፣ በትግራይ የዓረና የምርጫ 2002 ተወዳዳሪ፣ በንግድ ሥራ ይተዳደሩ የነበሩት አቶ አረጋዊ ገ/ዮሐንስ የካቲት 22 ቀን ለ23 አጥቢያ 2002 ዓ.ም. ከለሊቱ በዘጠኝ ሰዓት አስገደ ጽንብላ ወረዳ ውስጥ ልዩ ስሙ “ሚካኤል ህፃጽ” በተባለው ሥፍራ በሚገኘው ሁለተኛ ቤታቸው ከመገደላቸው በፊት በሚወዳደሩበት ሥፍራና በሽራሮ አካባቢ ተይዘው ለሁለት ጊዜያት ለ8 እና ለ7 ሰዓታት ያህል ታሥረው የተፈቱ መሆናቸውን አቶ ገብሩ አሥራት ገልጸው እንደነበርና “ሰዎቹ ደንግጠዋል፤ በጣም ነው የደነገጡት። የድንጋጤያቸው ምክንያት በትግራይ ከሚገኙት 38 የምርጫ ጣቢያዎች ውስጥ በ36ቱ ዓረና ትግራይ ተወዳዳሪ ዕጩዎችን ለማቅረብ በመቻሉ ነው” ብለዋል አቶ ገብሩ።

 

አያይዘውም በወቅሮ ማራይ አካባቢ ለፌደራል ም/ቤት በዕጩነት ያቀረብነው አቶ አያሌው በየነ የተባለው አባላችን “ስምማ” በተባለውና ከወቅሮ ማራይ የሁለትና የሦስት ሰዓት ያህል መንገድ ርቆ በሚገኘው ሥፍራ በታጣቂዎች ክፉኛ ተደብድበዋል ሲሉ አክለዋል። በሁመራ በአንድ አባላቸው ላይ ጥይት የተተኮሰበትና ግለሰቡም ለግዜው ከግድያ ሙከራ አምልጦ መሰወሩን፤ የአቶ ቢኒያም ተስፋዬ ወላጅ እናት ልጃቸው ከዓረና አባልነት እንዲታቀብ ያሳሰቡት ዘንድ ማስጠንቀቂያ ከተሰጣቸው በኋላ ለሁለት ቀናት የመታሰራቸውንም ጉዳይ ይፋ አድርገዋል አቶ ገብሩ።

 

እሳቸው እንደሚሉት ዘመቻው ተጧጡፎ ቢቀጥልም “መድረኩም ሆነ ዓረና ከምርጫው አይወጡም። ከሠላማዊ ትግሉ አያፈገፍጉም። ይህን ማድረግም መጥፎ አማራጭ ነው። ስለዚህ መስዋዕትነቱ እየቀጠለ ቢሆንም ሠላማዊ ትግሉ ይካሄዳል” እያሉ ናቸው።

 

በተጨማሪም ህወሓት ኢህአዲግ በአክሱም የዓረና ትግራይ አባል ናቸው በሚል ወ/ሮ ወርቅነሽ የተባሉ አባላችንን ከሥራቸው ቢያባርርም፣ አባሎቻችንን ቢገድልም፣ ቢደበድብም፣ ዛቻና ማስፈራሪያው ወደተግባር እየተለወጠ ቢሆንም፣ ከምርጫ ሕግና ከዓለም አቀፍ ሁኔታዎች አኳያ ሲመዘን በኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ሊካሄድ እንደማይችል ቢታወቅም፤ … መድረክና አባል ፓርቲዎቹ በ2002 ዓ.ም. ምርጫ የሚያደርጉትን የተሳትፎ እንቅስቃሴ አይገቱም፤ በማለት ማብራሪያ ሲሰጡ የነበሩት አቶ ገብሩ አስራት፤ ችግሩን በቅርብ ለመከታተል ወደ ትግራይ ሲያመሩ የመድረክ አመራሮችና የአንድነት ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት ኢንጂንየር ግዛቸውና አቶ ስዬ አብርሃ በያዝነው ሣምንት መጨረሻ ወደ ክልሉ እንደሚያመሩ ለመረዳት ተችሏል።

 

ይህ በእንዲህ እንዳለ የመድረኩ ዕጩዎች ወ/ሮ አረጋሽ አዳነ እና አምባሣደር አወአሎም ወልዱ ከኢህአዲጎቹ ሰዎች መለስ ዜናዊና አባይ ወልዱ ጋር በየሚመረጡበት አካባቢ ተፎካከሪ ሆነው ይቀርባሉ። እነ ወ/ሮ አረጋሽ የዓረና ፓርቲ አባላት ሲሆኑ፣ ለትግራይ ክልል አስተዳዳሪነት … ዕጩ ሆነው የቀረቡት የህወሓቱ ሰው አቶ አባይ ወልዱ ደግሞ የመለስ ደጋፊ፣ የህወሓት አባልና የታላቅ ወንድማቸው የአምባሣደር አውአሎም ወልዱ ተቀናቃኝ ናቸው።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ