የእስልምና ጉዳዮች ፕሬዝዳንትና ሌሎች አመራሮች ኢህአዲግ ስላልሆንን ተባረርን አሉ
Ethiopia Zare (ረቡዕ ጥቅምት 18 ቀን 2002 ዓ.ም. October 28, 2009)፦ የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሐጅ ባህር አብደላ እና ሁለት ከፍተኛ አመራሮች በሰባት ወር ዕድሜያቸው ሥልጣናቸውን ያጡት የኢህአዴግ አባል አንሆንም በማለታቸው መሆኑን ገለጹ።
አመራሮቹ ለጋዜጠኞች እንደገለጹት የቀረበላቸውን የኢህአዲግ አባልነት ፎርም አንሞላም በማለታቸው በምክር ቤቱ ዋና ፀሐፊ ሐጂ ሁሴን ኑረዲን ፊርማ ከሥልጣን ተባረዋል።
ምክትል ፕሬዝዳንቱ ሐጂ አማን ኢብራሂምና የልማት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ከድር ራሕመቶ ከሥልጣናቸው ሲባረሩ በሦስቱም ላይ የቀረበው ምክንያት ከገንዘብ ወጪና የአንዋር መስጅድ አስተዳደር ጉዳይ ነው። አሥራ አንድ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ግምገማ አካሂደው በቱርክ ለተካሄደው ጉዞ በቀን 50 የአሜሪካ ዶላር ለውሎ አበል መውጣቱና የአንዋር መስጅድን የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች እንዲያስተዳድር በሐረር ከተማ ውሳኔ መስጠቱን እነዚህ የተባረሩ አመራሮች መቃወማቸው እንደወንጀል ተቆጥሮ ከሥልጣን ለመባረር ዳርጓቸዋል።
ሐጅ አማን “እኛ እንድንባረር የተደረገውን የአባልነት ፎርም ባለመሙላታችን ነው፤ የቱርኩ ጉዞ የዋና ፀኃፊውም ፊርማ ያለበት ስለሆነ እኛን ብቻ ሊያስጠይቅ አይችልም። ግምገማ የተባለውም በሕገ-ወጥ መንገድ የተደረገ ነው።” ሐጂ ባህር በበኩላቸው “ግምገማውን ለመታዘብ ከኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች የመጡት ተወካዮች ቀጥታ ተካፋይ ሆነው ወንጃይ አስወንጀይ ሆነዋል” ብለዋል።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮችና የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች በቀድሞው አመራር አባላት /በነኤልያስ ሬድማን/ ወቅት ከፍተኛ ውዝግብ ውስጥ ገብተው የነበረ ሲሆን፣ ውዝግቡ ረግቦ የሥልጣን ሽግሽግ ከተደረገ ገና ሰባት ወራት ብቻ ነበር የተቆጠረው። አሁን በተባረሩት አመራሮች ምትክ ሌሎች የተተኩ ሲሆን፣ በሊቀመንበርነት አንጋፋው ምሁር የአልአዝሃር ዩኒቨርስቲ ምሩቅና የቅዱስ ቁርዓን /1961/ ከተርጓሚዎቹ አንዱ የሆኑት ሐጅ በሽር ዳውድ ናቸው።
የአዲስ አበባና የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ኢህአዲግ በቀጥታ ከላይ ሆኖ የሚያስተዳድረው ሲሆን፣ ይህንኑ የማስተዳደር ሥራውን እንዲያቆምና ሙስሊሙ ራሱ በመረጣቸው መሪዎች እንዲመራ ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ማኅበር በድር ኢንተርናሽናል ለጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጥያቄ ቢያቀርብም ተቀባይነት ማጣቱ የሚታወስ ነው።



