Teddy Afro after his release“ቴዲ አፍሮ ኖቨምበር 28 ስዊድን ይመጣል” አቶ ሀብታሙ

“ቴዲ አፍሮ ኖቨምበር 28 ኖርዌይ ይመጣል” አቶ ደስታ

“ስዊድን የሚመጣው ዲሴምበር 5 ነው” አቶ ሙሉሰው (ኩኩሻ)

“ኖቨምበር 28 ኖርዌይ፣ ዲሴምበር 5 ስዊድን” አቶ ምትኩ ግርማ የቴዲ አፍሮ ፕሮሞተር

Ethiopia Zare (እሁድ ጥቅምት 1 ቀን 2002 ዓ.ም. October 11, 2009)፦ በቅርቡ ከእስር የተፈታው የአርቲስት ቴዎድሮስ ካሣሁን (ቴዲ አፍሮ) የአውሮፓ የኮንሰርት ጉዞ በስዊድን እና በኖርዌይ መቼ እንደሚካሄድ አፍቃሪዎቹን አደናግሮ ሰንብቷል። በተለይም በዚህ ባሳለፍነው ሣምንት ከሦስት ወገኖች የተለያዩ ማስታወቂያዎች በተለያየ መንገድ በመበተናቸውን የኢትዮጵያ ዛሬ ድረ ገጽ ተገንዝቧል።

 

በስዊድን ኖቨምበር 28 እና ዲሴምበር 5 ቀን ቴዲ አፍሮ ኮንሰርት እንደሚኖረው በሞባይል እና በተለያዩ መንገዶች የተበተኑት ማስታወቂያዎች የሚገልጹ ሲሆን፣ በተመሳሳይ ሁኔታ በኖርዌይ ደግሞ ኖቨምበር 28 ቴዲ አፍሮ ኮንሰርት እንደሚኖረው ከተሰራጩት ማስታወቂያዎች ለመረዳት ችለናል። ይህ ጉዳይ በተለይም ቴዲ አፍሮን በጉጉት እየጠበቁት ባሉት አፍቃሪዎቹ ዘንድ መደናገርን ከመፍጠሩም በላይ “ኮንሰርቱ ውሸት ነው” እስከማለት የደረሱ ወገኖች መኖራቸውን በመገንዘብ፤ የኢትዮጵያ ዛሬ ድረ ገጽ ጉዳዩ ይመለከተናል የሚሉትን ወገኖች አነጋግሯል።

 

በስዊድን ዋና ከተማ ስቶክሆልም የተጠቀሱት ሁለት ቀኖች ናቸው። ኖቨምበር 28 ቴዲ አፍሮ እንደሚመጣ ማስታወቂያውን ያስነገሩት ፕሮሞተር አቶ ሀብታሙ አለነ ሲሆኑ፣ የዲሴምበር 5ቱን ደግሞ አቶ ሙሉሰው ዋቄ (ኩኩሻ) መሆናቸው ታውቋል።

 

ፕሮሞተር አቶ ሀብታሙ አለነ

የስዌኢትዮ ፕሮሞሽን ኃላፊ የሆኑትና በስዊድን 20 ዓመት የኖሩት አቶ ሀብታሙ ከስዊድን ሆነው ኦገስት 27 ቀን ከቴዲ አፍሮ ፕሮሞተር ከሆኑት ከአቶ ምትኩ ግርማ (ቢጊ) ባደረጉት የቃል ስምምነት ለኖቬምበር 28 ቀን 2009 እ.ኤ.አ. አዳራሽ ለመከራየት ተነጋግረው ይበልጥ በሥራው ላይ ለመነጋገር ኦገስት 29 ወደ ኢትዮጵያ ማምራታቸውን ለኢትዮጵያ ዛሬ ገልጸዋል።

 

ኢትዮጵያ በገቡ በሣምንቱ ሴፕቴምበር 5 ቀን ምሽት ላይ ከአቶ ምትኩ (ቢጊ) ተደውሎ “ይሄን ያህል ገንዘብ ከፍለህ የስቶክሆልምን ሥራ ትወስዳለህ?” የሚል ጥያቄ እንደቀረበላቸው የገለጹት አቶ ሀብታሙ፤ እስከ ሴፕቴምበር 7 ምሳ ሰዓት አቶ ምትኩ ጊዜ እንዲሰጧቸው መጠየቃቸውን ጠቅሰዋል። ከዚያም ሴፕቴምበር 7 ምሳ ሰዓት ላይ ተገናኝተው ለማውራት ባለመቻላቸው ለመደዋወል ተስማምተው መለያየታቸውንና በማግስቱ ሴፕቴምበር 8 ቀን ስለጉዳዩ ቀጠሮ ይዘው እንዲነጋገሩ ለአቶ ምትኩ ሲደውሉ ሥራው ለሌላ ሰው እንደተሰጠ አቶ ምትኩ ሲገልፁላቸው ሊሠሩት ያሰቡት ሥራ ከእጃቸው እንዳመለጣቸው በማወቅ ሽንፈታቸውን መቀበላቸውን ይገልጻሉ።

 

እንደ አቶ ሀብታሙ ገለፃ ከሆነ በድጋሚ ሴፕቴምበር 13 (መስከረም 3) ቀን ከአቶ ምትኩ የስልክ ጥሪ እንደደረሳቸው፣ ለሴፕቴምበር 15 (መስከረም 5) ምሳ ሰዓት ድረስ ሙሉ ክፍያውን ከከፈሉ የስቶክሆልሙ ሥራ እንደሚሰጣቸው ቃል እንደተገባላቸው አስረድተዋል። ይህንን ተከትሎ አንዳንድ ወጪዎችን ማውጣትና ተያያዥ ሥራዎችን መጀመራቸውን የገለጹት አቶ ሀብታሙ፤ በድጋሚ ከአቶ ምትኩ ተደውሎ ሥራው ለሌላ ሰው መሰጠቱን እንደተነገራቸው፤ ከዚያም ውሉ መፍረስ የሚችለው ክፍያውን በሰዓቱ ካልከፈሉ ብቻ መሆኑን ለአቶ ምትኩ ገልጸው፣ እንዲህ መደረጉ የሕግ አግባብነት የሌለውና የሙያ ሥነምግባር የጎደለው አሠራር መሆኑን ለአቶ ምትኩ መግጻቸውን አስረድተዋል።

 

አቶ ሀብታሙ ከሴፕቴምበር 13 ቀን ጀምሮ ሥራቸውን መቀጠላቸውን ተከትሎ ኪሳራቸውን ለመሸፈን አዘጋጆቹ አነጋግረዋቸው የነበረ ቢሆንም፣ አቶ ሀብታሙ ያቀረቡላቸውን ኪሳራ ሊከፍሏቸው ያልቻሉ መሆኑን ገልፀዋል። እንደ አቶ ሀብታሙ ገለፃ ከሆነ በእሳቸውና የስዊድኑን ዝግጅት ከእሳቸው ጋር ለመሥራት የተስማሙ ስፖንሰሮች እምነት መሠረት ሕጋዊና በቂ ሰነዶች በእጃቸው ላይ ስለሚገኝ ሥራቸውን እስከመጨረሻ እንደሚቀጥሉ አስረድተዋል።

 

አቶ ሙሉሰው ዋቄ (ኩኩሻ)

ቴዲ አፍሮ በስዊድን የሚያደርገው ኮንሰርት ዲሴምበር 5 ነው የሚሉት አቶ ሙሉሰው ዋቄ (ኩኩሻ) በበኩላቸው፤ ከቴዲ አፍሮ ፕሮሞተሮች ጋር በተለይም አቶ ምትኩ ግርማ (ቢጊ) ከሚመሩት ኤም.ጂ. ፕሮሞሽን ጋር ኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኘው ወኪላቸው አማካኝነት ስምምነት የተፈራረሙት ሴፕቴምበር 8 ቀን መሆኑን ገልጸዋል።

 

“ቴዲ አፍሮ በስዊድን የሚያደርገው የሙዚቃ ዝግጅት ዲሴምበር 5 ነው” ከማለታቸውም ሌላ ከቴዲ ቀጥተኛ ፕሮሞተሮች ጋር በገቡት ውል መሠረት ተገቢውን ክፍያም መፈፀማቸውንና ስዊድንም ውስጥ ለዝግጅቱ አስፈላጊ የሆኑ ቅድመ ሁኔታዎችን እያዘጋጁ መሆኑን ለኢትዮጵያ ዛሬ ገልፀዋል።

 

አቶ ደስት ገብረሥላሴ (ከኖርዌይ)

ኖቨምብር 28 ቴዲ አፍሮ ኦስሎ ነው ወይንስ ስቶክሆልም? የሚል ጥያቄ ከኢትዮጵያ ዛሬ የቀረበላቸውና ነዋሪነታቸው በኖርዌይ የሆኑት የቴዲ አፍሮን ዝግጅት የሚያዘጋጁት አቶ ደስታ ገ/ሥላሴ፤ “ምንም ጥያቄ የለውም! ቴዲ አፍሮ ኖቬምበር 28 ኖርዌይ ነው” ሲሉ መልሰዋል።

 

አቶ ደስታ ገ/ሥላሴ በበኩላቸው የቴዲ አፍሮን የኖርዌይ ዝግጅት እሳቸው ማሸነፋቸውንና የሙዚቃ ድግሱም ኖቨምበር 28 ቀን 2009 በዋና ከተማዋ ኦስሎ መሆኑን ገልጸው፤ ከሁለት ወር በፊት በቃል፣ ከአንድ ወር በፊት ደግሞ በወረቀት ከአቶ ምትኩ ግርማ ጋር መስማማታቸውን ለኢትዮጵያ ዛሬ ገልጸዋል።

 

የቴዲ አፍሮ ዋና ፕሮሞተሮች

በተለይም ቴዲ አፍሮ ከእስር ከተለቀቀ በኋላ በኢትዮጵያና በተለያዩ የዓለም ክፍሎች በመዘዋወር ለሚያቀርባቸው ኮንሰርቶች በቀጥታ የተዋዋለው ከሦስት ድርጅቶች ጋር መሆኑን ለመረዳት ችለናል። እነሱም አቶ ምትኩ ግርማ (ቢጊ) ከሚመሩት ከኤም.ጂ. ፕሮሞሽን፣ አዲካ ቱር ትራቭል እና አዲስ ቪው ሆቴል ኤንድ ካር ሬንታል ናቸው። ቴዲ አፍሮ በ11 የአውሮፓ ሀገሮች የሚያደርጋቸውን ኮንሰርቶች ሙሉ ለሙሉ ፕሮሞት የሚያደርጉት እነዚህ ሦስት ድርጅቶች ናቸው።

 

ፕሮሞተር ምትኩ ግርማ (ቢጊ)

የቴዲ አፍሮን የስዊድን ኮንሰርት ከአቶ ሀብታሙ ጋር ነው ወይንስ ከአቶ ሙሉሰው (ኩኩሻ) ጋር ስምምነታችሁ? የሚል ጥያቄ ከኢትዮጵያ ዛሬ የቀረበላቸው አቶ ምትኩ (ቢጊ)፣ “ውላችን ከኩኩሻ ጋር ነው” ሲሉ መልሰዋል። ኖቨምበር 28 ደግሞ ኖርዌይ ኦስሎ ላይ፣ ዲሴምበር 5 ደግሞ ስዊድን ስቶክሆልም የቴዲ አፍሮ ኮንሰርት እንደሚካሄድ ገልፀዋል።

 

ለአቶ ሀብታሙ ቃል ገብተውላቸው ቃላቸውን ለምን እንዳፈረሱ አቶ ምትኩን ጠይቀናቸው፤ “እስከ ሴፕቴምበር 7 ቀን ምሳ ሰዓት ድረስ አቶ ሀብታሙ ገንዘቡን እንዲከፍሉ ጊዜ ሰጥተናቸው የነበረ ቢሆንም፤ ገንዘቡን ሳይክፍሉ በመቅረታቸው፤ ሴፕቴምበር 8 ቀን 2009 እ.ኤ.አ. ከኩኩሻ (አቶ ሙሉሰው ዋቄ) ጋር ተዋውለናል” በማለት ለኢትዮጵያ ዛሬ ምላሽ ሰጥተዋል።

 

አቶ ሀብታሙ ሥራውን ለማካሄድ ገንዘብ እያወጣሁ ነው ስለማለታቸውና በጉዳዩ ላይ ያላቸውን አስተያየት እንዲሰጡ ከኢትዮጵያ ዛሬ ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ምትኩ፤ “እኛ ከሀብታሙ ጋር ምንም አይነት ሕጋዊ ኮንትራት አልተፈራረምንም። ምንም አይነት ሕጋዊ ስምምነት ከእኛ ጋር ሳይኖረው ለምን ገንዘብ እንደሚያወጣም አይገባኝም።” ሲሉ ምላሽ ሰጥተውናል።

 

በዚህ ጉዳይ አርቲስት ቴዎድሮስ ካሣሁን (ቴዲ አፍሮ) ያለውን አስተያየት ለኢትዮጵያ ዛሬ እንዲሰጥ ያደረግነው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል።

 

የቴዲ አፍሮ ኮንሰርቶች

ቴዲ አፍሮ ዛሬ ጥቅምት 1 ቀን 2002 ዓ.ም. (ኦክቶበር 11) በአዲስ አበባ ስታዲየም ውስጥ ከእስር ከተፈታ የመጀመሪያውን ኮንሰርት ያቀርባል። ከኢትዮጵያ ውጪ ደግሞ በአውሮፓ 11 ሀገሮች፣ በዩናይትድ ስቴትስ 14 ስቴቶች፣ በካናዳ ሁለት ከተሞች፣ በአፍሪካ አራት ከተሞች (ናይሮቢ፣ ጆሃንስበርግ፣ ካምፓላ እና ጅቡቲ)፣ በአራት የዐረብ ሀገራት (አቡዳቢ፣ ዱባይ፣ ኩዌት እና ቤይሩት)፣ በአውስትራሊያ ሁለት ወይንም ሦስት ከተሞች የሙዚቃ ድግሱ እንደሚካሄድ ለማወቅ ችለናል።

 

የፊታችን ኦክቶበር 15 አቡዳቢ ላይ የመጀመሪያውን ኮንሰርት የሚያቀርብ ሲሆን፣ ኦክቶበር 16 ዱባይ፣ ኦክቶበር 22 ኩዌት ላይ የዐረብ ሀገራቱን ዝግጅት ይጠናቀቃል። የአውሮፓ ጉዞውን ኦክቶበር 31 ላይ ፍራንክፈርት ላይ ይጀምራል። እስከ ፌብሩዋሪ 6 ቀን 2010 እ.ኤ.አ. በተለያዩ ሀገራት እየተዘዋወረ የሙዚቃ ድግሱን ካቀረበ በኋላ ለሁለት ወራት ያርፍና አፕሪል 4 ቤይሩት ላይ ኮንሰርት ማቅረቡን ይጀምራል። ለጊዜው መቼና የት ጉዞውን እንደሚያጠናቅቅ የተረጋገጠ ነገር ባይኖርም፤ እስከሚቀጥለው የአውሮፓውያን 2010 አጋማሽ ድረስ እንደሚቀጥል ይገመታል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ