Ethiopia Zare (ኀሙስ ነሐሴ 28 ቀን 2001 ዓ.ም. September 3, 2009)፦ ባለፈው እሑድ ነሐሴ 24 ቀን 2001 ዓ.ም. በሐዋሳ ከተማ አንድነት ፓርቲ ህዝባዊ ስብሰባውን ያካሄደ ሲሆን፣ በቦታው የተገኙ የኢ.ቴ.ቪ. ጋዜጠኞችና የፓርቲው ደጋፊዎች ጋር ግጭት ፈጥረው ስብሰባውን ሳይቀርጹ መመለሳቸውን የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች ገለጹ።

 

የራዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ሠራተኞች የሆኑት ጋዜጠኞች “ቅጥረኛ ናችሁ! ጋዜጠኞች አይደላችሁም” የተባሉት ህዝባዊ ስብሰባውን ካዘጋጁት የደቡብ ኢትዮጵያ የአንድነት ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት አደራጆች እና ከዋናው የፓርቲው መሪዎች ጋር ስብሰባው ወደሚዘጋጅበት ፒና ቁ.2 ሆቴል ዘልቀው ለመግባት ሙከራ ባደረጉበት ጊዜ በተፈጠረው አለመግባባት ነው።

 

ስብሰባው ከመካሄዱ በፊት ወደ ሆቴሉ አዳራሽ ገብተው የምስል እና የድምፅ መቅረጫ መሣሪያ ምሰሶ ለመትከል በመጣደፋ ላይ የነበሩት የኢትዮጵያ ራዲዮ እና ቴሌቪዥን ጋዜጠኞች በቅድሚያ የተጋጩት፤ ከሐዋሳ ከተማ የአንድነት ፓርቲ ደጋፊ ወጣቶች ጋር መሆኑን ምንጮች ከወደ ሥፍራው አስታውቀዋል። ወጣቶቹ ጋዜጠኞቹ እየተጠቀሙበት የነበረውን የመቅረጫ መሣሪያ ተሸካሚ ምሰሶ በማንሣት የጋዜጠኞቹን በሥፍራው መገኘት አጥብቀው የተቃወሙ ሲሆን፤ ይህን የመሰለው አለመግባባት ለሦስት ጊዜያት ማለትም ስብሰባው እስከተጀመረበት እና የስብሰባው የክብር እንግዶች ወደ አዳራሹ እስከዘለቁበት ጊዜ ድረስ መቀጠሉን ለመረዳት ተችሏል።

 

አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲን በተመለከተ የኢትዮጵያ ራዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ጋዜጠኞች የሚያሰራጩት ዘገባ ብዙውን ጊዜ ደስ የማያሰኘውና በእጅጉ የሚከፋበት መሆኑን በተደጋጋሚ ማስታወቁ ይታወሳል። ይህ በመሆኑም ፓርቲው በሐዋሳ ህዝባዊ ስብሰባ ላይ እንዲገኙ ከዚህ በፊት እንደሚያደርገው ሁሉ ለድርጅቱ ጋዜጠኞች በሥፍራው ይገኙ ዘንድ ጥሪ አላስተላለፈም።

 

በሐዋሳ በጋዜጠኞቹ እና በአንድነት ሰዎች መካከል አለመግባባት የተፈጠረውም ጥሪ ያልተደረገለትና ወደ ስብሰባው አዳራሽ እንዳይገባ የተከለከለው የኢትዮጵያ ራዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት የጋዜጠኞች ቡድን “መከልከሉን በመቃወም አምባጓሮ ለመፍጠር በመፈለጉ ነው” በማለት የአንድነት ሰዎች ተናግረዋል።

 

የገዥው ፓርቲ ልሳን መሆኑ የሚታወቀው የዚሁ የመገናኛ ብዙኀን ተቋም ሠራተኞችም፤ “ጋዜጠኞች ካልሆንን ምንድን ነን ታዲያ?” በማለት ላቀረቡትም ጥያቄ፤ “ቅጥረኞች ናችሁ!” የሚል መልስ ከአንድነት ደጋፊዎች በኩል ተሰጥቷቸዋል። ንዴታቸው የጋለው የኢትዮጵያ ራዲዮና ቴሌቪዥን ጋዜጠኞችም “ቅጥረኛ ማለት ምንድን ነው?” በማለት ሌላ ጥያቄ ሲሰነዝሩ ያለፍራቻ የቆሙት ወጣቶች፤ “ቅጥረኛ ማለት ለደሞዙ ብቻ ሲል የሚሠራ፣ በሙያው ሌላ የሚያዝበት፣ የሙያው ባለቤት ያልሆነ ወይም ለሙያው ነፃነት ደንታ ቢስ የሆነ ሰው ወይም የሆድ አደሮች ስብስብ ነው” የሚል ምልልሶችን ሲያደርጉ እንደነበር የዓይን እማኞች ተናግረዋል።

 

የድርጅቱ ጋዜጠኞች ማምሻውን በአንድነት አመራሮች የፓርቲው ህዝባዊ ስብሰባ እንዳይዘግቡ መከልከላቸውን በዜና እወጃቸው ላይ ተናግረዋል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ