በሜልቦርን የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ የተቃውሞ ሰልፍ አደረጉ
በደቡብ አፍሪካና በሊቢያ በወገኖቻችን ላይ የተፈጸመውን ኢሰብዓዊ ጥቃት ተቃወሙ
ሚያዝያ 16 ቀን 2007 ዓ.ም. (April 24, 2015) የሜልበርን ኢትዮጵያዊያን ኮሚኒቲ እና ዲሞክራሲ ለኢትዮጵያ ድጋፍ ቡድን በሕብረት ባስተባበሩት የተቃውሞ ሰልፍ እጅግ ከፍተኛ ቁጥር የነበረው ኢትዮጵያዊ ተሳትፎ ቁጣውን በመረረና እልህና ቁጭት በተንጸባረቀበት መልክ ሲገልጽ አርፍዷል።
በደቡብ አፍሪካ ደርባን ከተማ ጥቃት የደረሰባቸውን ወገኖች ዘግናኝ ምስልና ልዩ ልዩ መፈክሮችን አንግቦ ከጠዋቱ 5 ሰዓት (11 ኤም) ጀምሮ በደቡብ አፍሪካ ቆንስል ጽ/ቤት የተገኘው ሰልፈኛ ስሜት ይህን ይመስል ነበር።

ከኢትዮጵያዊ ሰልፈኛ ጋር አብራ የታደመች የደቡብ አፍሪካ ተወላጅ የሆነች ወጣት ያደረገችው ንግግር የሰልፈኝውን ስሜት የገዛ ነበር።
ወጣቷ በንግግሯ በደቡብ አፍሪካ ደርባን ከተማ በአፍሪካዊያን ላይ የተፈጸመው ጥቃት አስቃቂ፤ ዘግናኝ እና አሳፋሪ ነው ካለች በኋላ፤ ማንዴላ አረጋግቶ የያዘውን ደቡብ አፍሪካ ጃኮብ ዙማ እየገደላት ነው፤ ማንም ሰው አንድ ቦታ ላይ የውጭ ዜጋ ነው። እኔም እናተም የውጭ ዜጎች ነን በመሆኑም የውጭ ዜግነትን ምክንያት አድርጎ የሚሰነዘር ጥቃት አሳፋሪ ነው ስትል በወገኖቻችን ላይ የተፈጸመውን እንስሳዊ ጥቃት አውግዛለች።
አንድ እህት ያቃረበችው ግጥምም የሰልፍኛውን ስሜት በኀዘን አስደምሟል።

በሰልፉ ላይ የተለያዩ ወገኖች ንግግር ያደረጉ ሲሆን፣ የኦርቶዶክስ ኃይማኖቶት ካህን ቂም በቀልና ጥላቻ ዘላቂ ሰላም እንደማያመጣ በመግለጽ አሁንም ልባችን ለፍቅርና ለይቅርታ ክፍት ይሁን ሲሉ አስገንዝበዋል።

የሙስሊም ማኅበረሰቡ ተወካይም በተለይ በአይሲስ የተፈጸመውን ግድያ አስመልክቶ ባደረገው ንግግር፤ የአይሲስ ተግባርም ሆነ ምንነት ከእስልምና ኃይማኖት ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌለው አስረግጠው ተናግረዋል።

ሌሎችም ተናጋሪዎች ወገናችንን ለስደት የሚዳርገው ዘረኛው የወያኔ መንግሥት ከኢትዮጵያ ህዝብ ጫንቃ ላይ እስካልተወገደ በወገናችን ላይ እየደረሰ ያለው ጥቃት አያቆምም። አስተዳድረዋለሁ ለሚለው ህዝብ ደህንነትና የአገር ሉዓላዊነት ደንታ ቢስ የሆነው ህወሓት መራሹን መንግሥት በጽናት መታገል እንደሚያስፈልግ አጽኖት ሰጥተው ተናግረዋል።

ሰልፈኛው በዚሁ መልክ ቁጣውን ሲግልጽ ቆይቶ ለቆንሲሉ ጽ/ቤት የተዘጋጀውን መልዕክት አስተላልፎ ሰልፉ ተጠናቋል። (ቪዲዮውን ለመመልከት የማጫወቻ ቁልፉን ይጫኑ!)



