የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ በኦነግ ላይ ውሳኔ አሳለፈ
ምርጫ ቦርድ (ዓርማ)፣ አቶ ዳውድ ኢብሳ (በቀኝ)፤ አዲስ የተመረጡትና ምርጫ ቦርድ እውቅና የነፈጋቸው ሥስቱ አመራሮች (በግራ)
በቅርቡ ጠቅላላ ጉባዔ ያካሔደው ኦነግ ተቀባይነት የሌለው ነው ብሏል
አዳዲሶቹን አመራሮች ተቀባይነት የላቸውም በማለት ውሳኔ አሳልፏል
በምርጫው እንሳተፍ የሚለው ጥያቄያቸውም ውድቅ ኾኗል
ኢዛ (እሁድ መጋቢት ፲፱ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. March 28, 2021)፦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በቅርቡ የተካሔደውን የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (የኦነግ) ጠቅላላ ጉባዔ እና የተመረጡትን አዳዲስ አመራሮች ተቀባይነት የሌለው መኾኑን ውሳኔ አሳለፈ።
ቦርዱ ዛሬ ይፋ ባደረገው መግለጫ፤ ከዚህ ውሳኔ የደረሰበትን ዝርዝር ጉዳዮችን ያስቀመጠ ሲሆን፤ በዚህ ጠቅላላ ጉባዔ የተሰጡትን አዳዲስ አመራሮች እንደ ኦነግ አመራሮች መቀበል እንደማይችል አስታውቋል።
በቅርቡ በተካሔደው ጠቅላላ ጉባዔ የተመረጡት አመራሮች በምርጭ ውስጥ ለመሳተፍ እና እጩ ለማቅረብ ያቀረቡትን ጥያቄም፤ የተመረጠው አመራር ተቀባይነት የሌለው በመኾኑ፤ ጥያቄውን ተቀብሎ ለማስተናገድ እንደማይችልም ቦርዱ ወስኗል።
ኦነግ በቅርቡ ባካሔደው ጠቅላላ ጉባዔው አቶ አራርሳ ቢቂላን ሊቀመንበር አድርጎ የመረጠ መኾኑን መዘገባችን የሚዘነጋ አይደለም። በምክትል ሊቀመንበር ደግሞ አቶ ቀጄላ መርዳሳን እና አቶ ብርሃኑ ለማን መምረጡ ይታወሳል። ድርጅቱን ለረዥም ጊዜ ሲመሩ የነበሩት አቶ ዳውድ ኢብሳ ይህንን ጠቅላላ ጉባዔና ምርጫ አስመልክተው የተቃውሞ ድምፃቸውን አስምተው ነበር። ዛሬ የወጣው የምርጫ ቦርድ ውሳኔ ሙሉ ቃል የሚከተለው ነው። (ኢዛ)
የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) አመራር አባላት ያከናውኑትን ጠቅላላ ጉባዔ አስመልክቶ ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተሰጠ መግለጫ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) አመራሮች መካከል በተፈጠረ መከፋፈል እና ውዝግብን የተመለከቱ እግዶች፣ አቤቱታዎች እና ከሁለቱም ወገን የሚመጡ ማሳወቂያ ደብዳቤዎችን ሲቀበል መቆየቱ እንዲሁም ችግሩን ለመፍታት ቡድኖቹን በተናጠል እንዲሁም የፓርቲውን የሥነሥርዓት እና የቁጥጥር ኮሚቴን በማነጋገር ያሉትን አስተዳደራዊ እና ሕጋዊ መንገዶች ሁሉ እንደተጠቀመ መፍትሔዎችን ለመስጠት ጥረት ሲያደርግ እንደነበር ይታወሳል። በመጨረሻም ጠቅላላ ጉባዔ በመጥራት ፓርቲው ካለበት ችግር ብቸኛ መውጫ መንገድ መኾኑን በመረዳት እና በውዝግብ ውስጥ ያሉ አመራር ክፍሎችም ያመኑበት በመኾኑ በአመራሮች መካከል ያለው ችግር በጠቅላላ ጉባዔ እንዲፈታ መወሰኑ ይታወሳል።
ኦነግ መጋቢት 7 ቀን 2013 ዓ.ም በቁጥር 19/ABO/2013 በተጻፈ ደብዳቤ ድርጅቱ መጋቢት 4 ቀን 2013 ዓ.ም ጠቅላላ ጉባዔ በማካሔድ አዲስ የአመራር አባላት መምረጡን በመግለጽ፣ በውስጥ ችግሩ ምክንያት የጠቅላላ ጉባዔ ሳያካሒድ በመቆየቱ የምርጫና የእጩ ምዝገባ ጊዜ አልፎብናል በማለት ቦርዱ የነበረበትን ችግር ግምት ውስጥ በማስገባት የምልክት መረጣና የእጩ ተወዳዳሪዎች ምዝገባ እንዲያደርግ እንዲፈቅድለት ጠቅላላ ጉባዔውንም እንዲያጸድቅለት ጠይቋል። ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም የቀረቡትን ሰነዶች በአዋጅ ቁጥር 1162/2011 እና በፓርቲው ሕገ ደንብ መሠረት ምርምሯል።
ፓርቲው ያደረገውን ጠቅላላ ጉባዔ ቃለ ጉባዔ፣ በስብሰባው ላይ የተገኙትን አባላት ስም ዝርዝርና ፊርማ፣ በመጋቢት 5 ቀን 2013 ዓም ያደረገውን የድርጅቱን ብሔራዊ ምክር ቤት ስብሰባ ቃለ ጉባዔ፣ የተሻሻለውን የፓርቲውን የመተዳደሪያ ደንብ በኦሮምኛ የተመዘገበና በአማርኛ የተተረጎመ ሰነድ፣ መጋቢት 4 ቀን 2013 ዓም ጠቅላላ ጉባዔ ስብሰባ ላይ ከ500 በላይ ተሳታፊዎች መገኘታቸውን፣ ምላተጉባዔው የተሟላ መመኾኑን በማሳየት ፣ በመተዳደሪያ ደንቡ ላይ የተደረጉት ማስተካከያዎች በአዋጅ ቁጥር 1162/2011 መሠረት የተደረጋቸውን ገልጾ ጠቅላላ ጉባዔው እውቅና እንዲያገኝለት ጥያቄ አቅርቧል። ቦርዱም ሰነዶቹን በመመርመር፤
1. ፓርቲው መጋቢት 4 ቀን 2013 ዓ.ም የተደረገውን የጠቅላላ ጉባዔ ማስፈጸም የሚችለውን አስፈጻሚ ኮሚቴን ያቋቋመበት ስብሰባ በመተዳደሪያ ደንቡ አንቀጽ 23(4) በተመለከተው መሠረት የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው 2/3ኛ አባላት በተገኙበት መኾን ሲገባው የተባለው የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ 2/3ተኛ አባላት የተገኙበት ሳይሆን ሦስት የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ብቻ ያከናወኑት ምልዓተ ጉባዔው ያልተሟላ ስብሰባ ነው። ስለዚህ የጠቅላላ ጉባዔውን ለማካሔድ የተቋቋመው ኮሚቴ በደንቡ መሠረት ምልዐተ ጉባዔ ሳይሟላ የተቋቋመ በመኾኑ የጠቅላላ ጉባዔውን መጥራትና ማስፈጸም አይችልም ሲል ወስኗል።
2. በሌላም በኩል በፓርቲው የመተዳደሪያ ደንብ አንቀፅ 16.2 የጠቅላላው ጉባዔ የሚያቅፋቸውን አካላት በግልጽ የተመለከቱ ሲሆን፤ በዚህ ጉባዔ ላይ ሊሳተፋ የሚገባቸው የብሔራዊ ምክር ቤት አባላት፣ ሙሉ የአባልነት መብት ያላቸው የቀድሞ የኦነግ አመራር አባላት፣ በየደረጃው ከሚገኝ መዋቅር የሚወከሉ የኦነግ አባላት፣ ለኦሮሞ ሕዝብ የነፃነት ትግል የተለየ ድርሻ በማበርከት የሚታወቁ ሰዎች (የጉባዔተኛው 5% የማይበልጡ)፣ ከፓርቲው ጋር በቅርበት በመሥራት ላይ የሚገኙ ሕዝባዊ ድርጀቶች ማለትም የሴቶች፣ ወጣቶች፣ ባለሙያዎች … ወዘተ ማኅበራት ተወካዩች (ብዛታቸው በሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የሚወሰን) መኾናቸው ተመልክቶ እያለ፤ ፓርቲው አካሔድኩት በማለት ባቀረበው የጠቅላላ ጉባዔ ተካፋዩች ዝርዝር ከፍ ብሎ የተመለከቱት የጉባዔው የሚያቅፋቸው አካላት መኖራቸው አልተመለከተም፣ በመኾኑም ተሳታፊዎቹ በድርጅቱ መተዳደሪያ ደንብ መሠረት ለመወከላቸው ቦርዱ ማረጋገጥ አልቻለም።
3. እንዲሁም በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 17.1 ተወካይ ኾኖ ለጠቅላላ ጉባዔ የሚመረጥ አባል ቢያንስ ለሁለት ዓመታት ያለማቋረጥ ያገለገለና ግዳጁን በአግባቡ የፈጸመ መኾን እንዳለበት በሚደነግገው መሠረት መጋቢት 4 ቀን 2013 ዓ.ም በተደረገው ጠቅላላ ጉባዔ የተሳተፉ አባላት ይህንን በደንቡን የተመለከተውን መስፈርት ማሟላታቸው ለማረጋገጥ የቀረበ ነገር የለም።
4. የተከናወነውን ጠቅላላ ጉባዔ የድርጅቱ ሊቀመንበር እና ጠቅላላ ጉባዔ ለማከናወን ከአመራሮቹ ውዝግብ በፊት ተቋቁሟል የተባለ ኮሚቴ እውቅና ውጪ የኾነ የድርጅቱን ሕገ ደንብ እና አሠራር የተከተለ አይደለም በማለት ለቦርዱ ተቃውሞ የቀረበበት መኾኑንም ተገንዝቧል።
5. ቦርዱ ጥር 19 ቀን 2013 ዓ.ም ባስተላለፈው ውሳኔ ላይ የፓርቲው አመራሮችን፣ መዋቅሮቹን እና አባላቶቹ የተለያዩ በፓርቲው ሕገ ደንብ ላይ በተቀመጡ መንገዶች በመጠቀም በጠቅላላ ጉባዔ ችግሩን እንዲፈቱ የወሰነ መኾኑ የሚታወስ ሲሆን፤ የተደረገው ጠቅላላ ጉባዔ ይህንን መሠረት አድርጎ የተከናወነ ጉባዔ መኾኑን አያሳይም። ጠቅላላ ጉባዔውን የሚያደራጅ ኮሚቴ ያቋቋሙትም ሦስት የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ብቻ መኾናቸው ቦርዱ ጥር 19 ቀን ከወሰነው የፓርቲው አመራሮች መዋቅር እና አባላቶች የተለያዩ ሕጋዊ መንገዶችን በመጠቀም ጠቅላላ ጉባዔ ማካሔድ አለባቸው ከሚለው አንጻር ሲታይ የቦርዱን ውሳኔ አያሟላም።
በመኾኑም ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች የተከናወነውን ጠቅላላ ጉባዔ ተቀባይነት የለውም ሲል ቦርዱ ወስኗል። ውሳኔውን መሠረት በማድረግም በዚህ ጉባዔ የተመረጡትን አዲስ አመራሮች እንደኦነግ አመራሮች መቀበል አይችልም። ከዚህም በተጨማሪ ምርጫው ውስጥ ለመሳተፍ እና እጩዎች ለማቅረብ ያቀረቡትን ጥያቄ አሁን የተመረጠው አመራር ተቀባይነት ካለማግኘቱ ጋር ተያይዞ ቦርዱ ጥያቄውን ማየት እንዳላስፈለገው ለማሳወቅ ይወዳል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ
መጋቢት 19 ቀን 2013 ዓ.ም.



