መንግሥትና መከላከያ የታሉ?
ፓርላማው በእንባ ሲራጭ ዋለ
ፓርላማው የጀገነበት የፓርላማ ውሎ
ኢዛ (ማክሰኞ ጥቅምት ፳፫ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. November 3, 2020)፦ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በዛሬው ዕለት ያካሔዱት ስብሰባ በተለየ መልኩ የተካሔደ ነበር። በጥቁር የኀዘን ልብስና በእንባ ጭምር የታጀበው የዛሬው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ፤ በዕለቱ ለውይይት ተይዞ የነበረውን አጀንዳ በመተው መወያየት የምንፈልገው በወቅታዊ የአገራችን ጉዳይ ነው በማለት የጀገኑበት ነበር ማለት ይቻላል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከመቼውም ጊዜ በተለየ ሥልጣኑን የተጠቀመበት ጭምር ነበር። የዛሬው (የማክሰኞ ጥቅምት 23 ቀን 2013 ዓ.ም.) የፓርላማ ውሎ በተለየ መንገድ እንዲካሔድ ያደረገው ደግሞ ከትናንት በስቲያ በምዕራብ ወለጋ የተፈጸመው ማንነት ላይ ያተኮረ አሰቃቂ ግድያ ነበር።
ከዚህ የበለጠ አጀንዳ የለንም በማለት በዚሁ ጉዳይ ላይ መምከር የጀመሩት የፓርላማ አባላት፤ “መንግሥት የታለ?” ብለው እስከመጠየቅ የደረሱበት ነበር።
በዛሬው የፓርላማ ውሎ በቀጥታ በፓርላማው አስተያየታቸውን ከሰጡት ውስጥ ምክትል አፈ ጉባዔ ወይዘሮ ሽታዬ ምናለ አንዷ ነበሩ።
ወይዘሮ ሽታዬ አስተያየታቸውን የጀመሩት ከሁለት ዓመት በፊት የነበራቸው ተስፋ ዛሬ የሌለ መኾኑን በመግለጽ ነበር። እንደ ምክር ቤት እኛ መኖር የምንችለው ሕዝብ ሲኖር ነው ያሉት ወይዘሮ ሽታዬ፤ እንዴት ሕፃናት ይገደላሉ? እንዴት እናቶች ይገደላሉ? በማለት አምርረው ተናግረዋል።
“የሕዝባችንን ሰላምና ደኅንነት ካላስጠበቅን፤ የምክር ቤት አባልነታችን ምንድነው የሚጠቅመን? በማለትም እንደ ምክር ቤት ቁርጥ ያለ አቋም መያዝ አለብን” ብለዋል።
“ኃላፊነታችን ባለመኾኑ እርምጃ ለመውሰድ ባንችልም፤ መከላከያው ምን እየሠራ ነው? ሰላም ሚኒስቴር ምንድነው የሚሠራው? መንግሥት ምንድነው የሚሠራው?” በማለት በቁጭት ጠይቀዋል።
መንግሥት በሕገ መንግሥት የተሰጠው ሥልጣን መጠቀም አለበት። ከልማትና ከብልጽግና በፊት የሕዝብ ደኅንነት መቅደም እንደሚኖርበትም ወይዘሮዋ አመላክተዋል።
የዛሬው የፓርላማ አባላት አስተያየት በዚህ ያቆመ አልነበረም፤ አሁን ስላለው ሁኔታ ሁሉ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ የሚመለከታቸው የሥራ ኃላፊዎች ሁሉ በአጭር ጊዜ ማብራሪያ እንዲሰጡዋቸው የጠየቁበት ነበር።
እንደ አልሸባብና አይኤስኤስን ለመመከት በሰው አገር ሰላም እስከማስከበር የደረሰው የአገሪቱ መከላከያ ሠራዊት፤ ኦነግ ሸኔን ማሸነፍ አቅቶት ነው? ያሉት አንድ የምክር ቤት አባል፤ ይህንን ጥያቄያቸውን ያቀረቡት በዚህ መልኩ ነበር።
“ሰላም በማስከበር የሚታወቀው ሠራዊታችን፣ የደኅንነት ተቋማችን ምን እየሠራ ነው? አልሸባብን፣ አይኤስኤስን ድባቅ እንዳልመታ፤ ኦነግ ሸኔ አሸንፎት ነው? ሕወሓት አሸንፎት ነው? በዚህ ሕዝብ ላይ ለምንድነው ግፍ የሚፈጸመው? ይህ የሚኾነው የእርምጃ አወሳሰዳችሁ ደካማ ስለኾነ ነው። ይህንን ማሸነፍ የሚችል ኃይል አጥተን አይደለም።” በማለት በእንባ ጭምር ነበር የጠየቁት።
እኒሁ የፓርላማ አባል አያይዘው፤ “የውስጥ ኃይላችንን መርምረን ካላስተካከልን፤ ነገ የውጭ ጠላትን እንዴት ነው የምንመክተው? መመለስ ካለበት ይህ ጥያቄ መመለስ አለበት” ያሉ ሲሆን፤ አክለውም “እንደ ሰላም ሚኒስቴር ያሉ ተቋማት የትኛውን መግባባት ነው ያመጡት?” በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
በስሜት የታጀቡት የዛሬው የፓርላማ አባላቱ አስተያየት፤ የመንግሥት አካላት በአስቸኳይ ማብራሪያ ይስጡ ከሚል ጥያቄ ባሻገር፤ ሕወሓትና ኦነግ ሸኔ በምክር ቤቱ በሽብርተኝነት እንዲፈረጁ የጠየቁ የፓርላማው አባላት ነበሩ።
በዜጐች ላይ ያለማቋረጥ እየደረሰ ያለው ጥቃት በምሬት ሲናገሩ የነበሩት የምክር ቤቱ አባላት፤ የጥቃቱ መደጋገም መንግሥት ሕግን ለማስከበር ደካማና ቸልተኛ በመኾኑ ጭምር ነው በማለት የተናገሩበት ነበር።
መንግሥትን መጠበቅ የለብንም፤ አቋማችንንና መወሰድ ያለበትን እርምጃ ወስነን ለመንግሥት በማሳወቅ በየጊዜ የሚወሰደውን እርምጃና ሁኔታዎችን መከታተል ነው ያለብን እኛ ነን በማለት አስተያየት የሰጡ የምክር ቤቱ አባላትም ነበሩ። (ኢዛ)



