የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶስ መግለጫውን በሰጠበት ወቅት

መግለጫው በተሰጠበት ወቅት፣ ረቡዕ ነኀሴ ፳ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. August 26, 2020፣ ፎቶ (©EOTCTV)

የፖለቲካ ፓርቲዎች ርዕዮተ ዓለማዊ ጥቃት በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ እያደረሱባት እንደኾነ ተገለጸ

ኢዛ (ረቡዕ ነኀሴ ፳ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. August 26, 2020)፦ የአርቲስት ሐጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች የተፈጸመው ጥቃት ዋናው ዒላማ ኦርቶዶክሳውያን ምእመናን እንደነበሩ በመግለጽ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጠንከር ያለ መግለጫ አውጥታለች። በፖለቲካ ፓርቲዎች ርዕዮተ ዓለማዊ ጥቃት እየደረሰባት እንዳለ ያስታወቀችው ቤተ ክርስቲያኒቱ፤ ከ67 በላይ ምእመናን በግፍ እና በአሠቃቂ ኹኔታ መገደላቸውን ከዐቢይ ኮሚቴው የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት መረዳትዋን አስታውቃለች።

ሲኖዶሱ ዛሬ ረቡዕ ነኀሴ 20 ቀን 2012 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፤ የአርቲስት ሐጫሉን ግድያ ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የመንግሥትን መዋቅር ተገን ያደረጉ የእምነትና የብሔር ጽንፈኞች አስቀድመው ከተደራጁ ኃይሎች ጋር በመቀናጀት የፈጸሙት ስልታዊ እና አረመኔያዊ ጥቃት ዋና ዓላማ፤ ኦርቶዶክሳውያን ምእመናን እንደነበሩ፤ ጉዳቱ በደረሰባቸው አካባቢዎች በአካል በመገኘት ከተሰበሰበው መረጃና ሪፖርት ማረጋገጡን ጠቅሷል።

በዚያን ሰሞናዊ ጥቃት ከ67 በላይ ምእመናን በግፍ እና በአሠቃቂ ኹኔታ መገደላቸውን፤ 38 ምእመናን ቋሚ (ከባድ)፣ 29 ምእመናን ደግሞ ቀላል የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው በዚሁ መግለጫ ላይ ተጠቅሷል።

ከግድያና የአካል ጉዳት ባሻገር ከሰባት ሺሕ በላይ ምእመናን ከመኖሪያቸው ከመፈናቀላቸውን፤ ለሥነ ልቡናዊ እና ለሥነ አእምሯዊ ቀውስ ስለመዳረጋቸው፤ እንዲሁም ከአምስት ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረታቸውንም በዘረፋ እና በቃጠሎ ማጣታቸውን የዐቢይ ኮሚቴው የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት እንዳሳየ በዛሬው መግለጫ ላይ ተመልክቷል።

በዚህ መግለጫ አጽንኦት እንዲሰጣቸውና የሲኖዶሱን አቋም የሚያንጸባርቁ ውሳኔዎች የተለለፉበት ነው። ይህንንም በጉዳት ጥናት መረጃው መሠረት፤ ጊዜያዊ እርዳታን ከማድረስና ከመልሶ ማቋቋም ባሻገር መንግሥት በአስቸኳይ ሊፈጽማቸው የሚገቡ ተግባራት ብሎ ስድስት ዋና ዋና ነጥቦችን አስቀምጧል።

ሰፋ ያለ ይዘት ያለው ይኸው መግለጫ፤ አንዳንድ የመንግሥት ባለሥልጣናትና የፖለቲካ ፓርቲዎች የግፉዓን ሰማዕታቱን መጠቃት አላግባብ ለቡድናዊ እና ፖለቲካዊ ትርፍ በመጠቀም በኀዘናችን ከመሳለቅ እንዲቆጠቡ፤ መንግሥትም ተገቢውን ክትትል በማድረግ እንዲያስታግስ ቤተ ክርስቲያኒቱ አበክራ ጠይቃለች።

ወንጀለኞችም ለፍርድ እንዲቀርቡ ጭምር በጠየቀችበት በዚህ መግለጫ፤ በቤተ ክርስቲያኗ ላይ ተደጋጋሚ ጥቃት እየተፈጸመ በመኾኑ፤ ይህ በአስቸኳይ እንዲቆምም ከዚህ ቀደም የደረሱ ጥቃቶችን በማስታወስ የሁኔታውን አሳሳቢነት አመልክታለች። እነዚህ ጥቃቶች “በሽግግር ወቅት የሚያጋጥሙ” ተብለው ብቻ የሚታለፉ ሳይኾኑ፣ የተሳሳቱ ርእዮተ ዓለማዊ ትርክቶችንና ጂኦ-ፖለቲካዊ ዳራዎችን መነሻ በማድረግ በተቀነባበረ እና በተደራጀ ስልት የሚፈጸሙ ኦርቶዶክሳውያንን የ‘ማጽዳት’ እንቅስቃሴዎች እንደኾኑ ከጊዜ ወደ ጊዜ ግልጽ እየኾነ መምጣቱን ቤተ ክርስቲያኒት መገነዘቧን ገልጻለች።

በዚሁ መግለጫ ላይ፤ “በአጭር ጊዜ ሳይታረም በዚኹ ከቀጠለም፣ የከፋ ፍጻሜ ሊያስከትል እንደሚችል ከወዲሁ ታስገነዝባለች። ስለዚህም፣ የፌዴራል እና የክልል መንግሥታት፥ በእኒህ ስሑት አስተሳሰቦች እና ሐሳዊ ትርክቶች ማሕቀፍ፣ ኾነ ተብሎ የሚፈጸም ኦርቶዶክሳውያንን የማሣቀቅ እና የማዳከም ሃይማኖት ተኮር ጥቃትን አስቀድሞ በመከላከል፣ ፍትሕን በማስፈን፣ ተጎጂዎችን በአግባቡ በመካስ እና በማቋቋም፣ ሕገ መንግሥታዊ ግዴታቸውን እንዲወጡ በአጽንዖት ታሳስባለች” በማለት አጽንኦት ሰጥታ ገልጻለች።

ከአርቲስት ሐጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር ተያይዞ የተጎዱ ወገኖችንም ለመደገፍም ለምእመናን ጥሪ ተላልፏል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ያወጣችውን ሙሉ መግለጫ አስነብበኝ! (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ