ኢትዮጵያና የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ግስጋሴ
በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ የሁኔታ መግለጫ (ሐሙስ ግንቦት 20 ቀን 2012 ዓ.ም.፤ በጤና ሚኒስቴር እና በኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የተዘጋጀ)
በአንድ ቀን 100 በቫይረሱ የተጠቁ ተገኙ፤ 94ቱ ከአዲስ አበባ የተገኙ ናቸው
ኢዛ (ሐሙስ ግንቦት ፳ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. May 28, 2020)፦ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሥርጭት በኢትዮጵያ ውስጥ እጅግ አስጊ ወደሚባል ደረጃ እየተሸጋገረ ስለመኾኑ አመላካች ሪፖርቶች እየወጡ ሲሆን፣ በዛሬው የጤና ሚኒስቴር ዕለታዊ መረጃ በአንድ ቀን 100 የሚኾኑ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች መገኘታቸውን አሳውቋል።
በአገሪቱ የመጀመሪያው በቫይረሱ የተጠቃ ሰው ከተከኘበት ከመጋቢት 4 ቀን 2012 ዓ.ም. ወዲህ፤ በአንድ ቀን 100 የቫይረሱ ተጠቂዎች የተገኙበት ዛሬ ግንቦት 20 ቀን 2012 ዓ.ም. ኾኖ ሊመዘገብ ችሏል።
ካለፉት ሦስት ሳምንታት ወዲህ እየጨመረ የመጣው የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር እያደገ መጥቶ፤ በ24 ሰዓታት ውስጥ ለ4,590 ሰዎች ምርመራ ተደርጎ፤ 100 የሚኾኑት ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል። እንደተለመደው ቀትር ላይ ይህ ሪፖርት ሲደረግ በብዙዎች ዘንድ ድንጋጤ የፈጠረ ሲሆን፣ ወረርሽኙ እየሰፋ ስለመምጣቱ አረጋጋጭ እንደኾነ ታምኗል።
በዛሬው ዕለት በቫይረሱ መጠቃታቸው ከተገለጹት መቶዎቹ ውስጥ፤ 94ቱ የሚኾኑት የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች መኾናቸው ደግሞ፤ ወረርሽኙ በአዲስ አበባ ከሌሎች አካባቢዎች በተለየ ፍጥነት እየተስፋፋ መሔዱን አመላክቷል።
ዛሬ የተገኙትን ጨምሮ በአጠቃላይ እስከአሁን በኢትዮጵያ በቫይረሱ የተጠቁት ሰዎች ቁጥር 831 የደረሰ ሲሆን፤ በዚህ ግስጋሴው በቀጣዩ ሁለትና ሦስት ቀናት የተጠቂዎች ቁጥር ከአንድ ሺህ በላይ ሊሻገር እንደሚችል ተገምቷል። ከ100 ተጠቂዎች ውስጥ 62ቱ የውጭ አገር የጉዞ ታሪክ የሌላቸውና በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር የታወቀ ግንኙነት የሌላቸው ናቸው። 35ቱ በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ግንኙነት ያላቸው ሲሆን፤ አምስቱ ደግሞ የውጭ ጉዞ ታሪክ እንዳላቸው ታውቋል።
ባለፉት ሁለትና ሦስት ሳምንታት ከጠቅላላው የቫይረሱ ተጠቂዎች ውስጥ አዲስ አበባ ከ60 - 65 በመቶ የሚኾኑ የተገኙበት ሲሆን፣ አሁን ግን ይህ ቁጥር ከ72 በመቶ በላይ ደርሷል።
በአዲስ አበባ ችግሩ ጎልቶ የታየባቸው ሁለት ክፍለ ከተሞች የእንቅስቃሴ ገደብ የተጣለባቸው ሲሆን፤ አሁንም ተጨማሪ እርምጃዎች ይወሰዳሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ከዛሬው የጤና ሚኒስቴር ሪፖርት፤ በቫይረሱ ተጠቅተው የሞቱት ሰዎች ቁጥር ሰባት መድረሱን ያመላከተ ሲሆን፤ አንድ ሰው ደግሞ በጽኑ ሕክምና ላይ ይገኛል። በአንጻሩ 10 አዲስ ያገገሙ ሰዎች በመኖራቸው፤ አጠቃላይ ያገገሙ ሰዎች ቁጥር 191 ደርሷል።
በኢትዮጵያ ምርመራ የተደረገላቸው ሰዎች 96,565 የደረሰ ሲሆን፤ 631 የሚኾኑት ታማሚዎች ደግሞ የሕክምና ክትትል እየተደረገላቸው ነው። (ኢዛ)



