ዛሬ ሦስት ሰዎች በኮሮና መያዛቸው ይፋ ኾነ
በኢትዮጵያ በቫይረሱ የተያዙት ቁጥር በግራፍ
በአገሪቱ በበሽታው የተያዙት ቁጥር 194 ደረሰ
ኢዛ (ዓርብ ሚያዝያ ፴ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. May 8, 2020)፦ ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ከተደረገላቸው 1,861 ሰዎች ውስጥ ሦስት በቫይረሱ የተጠቁ አዳዲስ ሰዎች መገኘታቸውን የጤና ሚኒስቴር ዛሬ ይፋ አደረገ። በአገሪቱ በበሽታው የተያዙት ቁጥር 194 ደርሷል።
ሦስቱም የቫይረሱ ተጠቂዎች የውጭ አገር የጉዞ ታሪክ የሌላቸው መኾናቸው ታውቋል። ከሦስቱ ግለሰቦች ውስጥ ሁለቱ በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ግንኙነት የነበራቸው ሲሆን፣ ሦስተኛው ግለሰብ በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ግንኙነት እንደነበረው እየተጣራ መኾኑን የጤና ሚኒስቴር የዛሬው ሪፖርት ያስረዳል።
በዛሬው ሪፖርት ሁለት ሰዎች ከበሽታው ማገገማቸው የተነገረ ሲሆን፤ በድምሩ 95 ሰዎች ከበሽታው ማገገማቸው ታውቋል። እስከዛሬ ድረስ 30,306 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ የላቦራቶሪ ምርመራ የተደረገላቸው ሲሆን፤ በቫይረሱ ተይዘው በለይቶ ማቆያ ኾነው ሕክምና እየተከታተሉ ያሉ ሰዎች ቁጥር 95 መኾኑ ታውቋል። (ኢዛ)



