ከፑንትላንድ የመጡ ሦስት ኢትዮጵያውያን የኮሮና ቫይረስ ተገኘባቸው
በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ የሁኔታ መግለጫ (ሰኞ ሚያዝያ 26 ቀን 2012 ዓ.ም.፤ በጤና ሚኒስቴር እና በኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የተዘጋጀ)
አምስት አዳዲስ ተጠቂዎች ተገኝተዋል፤ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 140 ደረሰ
ኢዛ (ሰኞ ሚያዝያ ፳፮ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. May 4, 2020)፦ ባለፉት 24 ሰዓታት ለ1,758 ለሚኾኑ ሰዎች የኮሮና ቫይረስ የላቦራቶሪ ምርመራ ተደርጎላቸው፤ አምስት የቫይረሱ ተጠቂዎች በመገኘታቸው በኢትዮጵያ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 140 ደረሰ።
ዛሬ ሰኞ ሚያዝያ 26 ቀን 2012 ዓ.ም. ጤና ሚኒስቴር ይፋ ባደረገው ዕለታዊ ሪፖርት፤ በተለያዩ የምርመራ ማዕከላት በተደረጉ ምርመራዎች አዲስ የተገኙት የቫይረሱ ተጠቂዎች አራት ኢትዮጵያውያንና አንድ ትውልደ ኢትዮጵያዊ ናቸው።
ከ17 - 24 በሚደርስ የዕድሜ ክልል ውስጥ ካሉት አምስቱ የቫይረሱ ተጠቂዎች ውስጥ ሦስቱ ከፑንትላንድ የተመለሱና በጅጅጋ አስገዳጅ ለይቶ ማቆያ የነበሩ ናቸው። አንዱ ደግሞ በባሕር ዳር ነዋሪ ሲሆን፤ ከቫይረሱ ተጠቂ ሰው ጋር ግንኙነት ያለው ሰው እንደነበር ታውቋል።
ስዊድናዊው ትውልደ ኢትዮጵያዊ ደግሞ ከስዊድን የተመለሰና በአዲስ አበባ አስገዳጅ ለይቶ ማቆያ ውስጥ የነበረ መኾኑ ተገልጿል።
በዛሬው መረጃ እስካሁን የተመርማሪዎች ቁጥር 24,088 ደርሷል። ቫይረሱ ተገኝቶባቸው በሕክምና ላይ ያሉ 60 ሲሆኑ፣ ያገገሙት ደግሞ 75 ደርሰዋል። (ኢዛ)



