መንግሥት ለኮሮና ቫይረስ አምስት ቢሊዮን ብር መደበ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ
ከጎረቤት አገሮች ወደ ኢትዮጵያ በየብስ መግባት ተከለከለ
ኢዛ (ሰኞ መጋቢት ፲፬ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. March 23, 2020)፦ የኮሮና ቫይረስን (ኮቪድ-19) ሥርጭትን ለመቀነስና ለመከላከል መንግሥት 5 ሚሊዮን ብር መመደቡን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ አስታወቁ። ከጎረቤት አገሮች ወደ ኢትዮጵያ በየብስ የሚገቡ ማናቸውንም እንቅስቃሴዎች መታገዱንም አስታውቀዋል።
ዛሬ መጋቢት 14 ቀን 2012 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሠጡት መግለጫ የቫይረሱ በኢትዮጵያ መገኘት ከታወቀ በኋላ ለሦስተኛ ጊዜ ሲሆን፤ በዛሬ መግለጫቸው ከዚህ ቀደም መንግሥት ቫይረሱን ለመከላከል በጅቶት የነበረውን የ500 ሚሊዮን ብር ወደ 5 ቢሊዮን ብር ማሳደጉን አስታውቀዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትምህርት ቤቶች በመላው አገሪቱ መዘጋታቸውን የገለጹበት መጋቢት 7 ቀን የመጀመሪያው መግለጫቸው እንደነበር ይታወሳል። ባለፈው ዓርብ መጋቢት 11 ቀን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ 30 የበረራ መስመሮቹን ማቋረጡን የገለጹበት ሁለተኛው መግለጫቸው ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ ለሦስተኛ ጊዜ በሠጡት መግለጫ፤ ቫይረሱ በፍጥነት ቢዛመት ክልሎች ለይቶ ማቆያና ማከሚያ እንዲሁም የሕክምና ባለሙያዎች እየተዘጋጁ መኾናቸውን ገልጸዋል።
ከዚህም ሌላ የሚደረጉና ከጎረቤት አገሮች ወደ ኢትዮጵያ በየብስ የሚገቡ ማናቸውንም የሰዎችን እንቅስቃሴዎች የመከላከያ ሠራዊት በድንበር አካባቢ እንደሚገታ ገልጸው፤ ይህ እርምጃ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ሸቀጦችንና አስፈላጊ መገልገያዎችን እንደማይጨምር አስታውቀዋል። የጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ያወጣውን ሙሉ መግለጫ ከዚህ በታች ያገኙታል። (ኢዛ)




