ይህ ምስል አውሮፓና አሜሪካ እንዳይመስልዎ፤ ኢትዮጵያ እንጂ
ዛሬ የበረዶ ክምር የወረራት አሾካ ቀበሌ፣ ምዕራብ አርሲ ዞን ኮፈሌ ወረዳ
ዛሬ በምዕራብ አርሲ ዞን ውስጥ፤ ኮፈሌ ወረዳ አሾካ ቀበሌ የተከሰተ በረዶ ነው
ኢዛ (እሁድ መጋቢት ፲፫ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. March 22, 2020)፦ እንዲህ ያለው የበረዶ ክምር ሲታይ የተለያዩ የአውሮፓና የአሜሪካ ጎዳናዎች ይታወሳሉ። በምስሉ ላይ እንደሚታየው የበረዶ ክምሩ መንገዶችን ዘግቷል። አካባቢውንም ሸፍኗል። ይህ ግን አውሮፓ ሳይኾን የኾነው በምዕራብ አርሲ ዞን ውስጥ፤ ኮፈሌ ወረዳ አሾካ ቀበሌ ዛሬ መጋቢት 13 ቀን 2012 ዓ.ም. ነው።

በአውሮፓና በሌሎች በረዶ የሚወዳቸው አገሮች ከበረዶው ጎን ለጎን ነዋሪዎቻቸውም ሙቀት ሰጭ፣ ብርዱን ተከላይ፣ በረዶውን የሚያንሸራትት ጃኬት፤ የእጅ ጓንት፤ ጆሮና ጭንቅላት የሚሸፍን ኮፍያ፤ ስካርፍና ጉልበታቸው የሚደርስ ለብርድ ተብሎ የሚሠራ ጫማ (አጭር ጫማም ቢኾን በረዶ ላይ የማያንሸራትት፣ በረዶ የሚቆነጥጥ፣ የሚሞቅና ምቹ ጫማ) ይጫማሉ። በረዶው ድንገት የኾነባቸው የኮፈሌና አሾካ አካባቢ ነዋሪዎች፤ በተለመደ አለባበሳቸው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ቢኾንም፤ ዐይተውት የማያውቁት፣ ያልተለመደና አስደንጋጭ በረዶ ጎብኝቷቸዋል።

እንዲህ ያለው በረዶ አስተናግዶ የማያውቀው አሾካ ቀበሌ፤ በረዶው የአካባቢውን ቤቶች የሸፈነ ሲሆን፤ ቀበሌዋን የሚያቋርጠውም መንገድ በበረዶ ተሸፍኖ የትራንስፖርት እንቅስቃሴዎችን አስተጓጉሏል።
የአካባቢው ነዋሪዎች በተለይም በረዶውን ከአስፋልት (አውራ ጎዳና) ላይ ለማንሳት የተቻላቸውን ጥረት ሲያደርጉ የነበረ ሲሆን፣ በረዶ ውስጥ ተቆልፈው መንቀሳቀስ ያቃታቸውን መኪኖችም ሲገፉና ከበረዶው ለማላቀቅ አካፋና የመሳሰሉ መሣሪያዎችን ሲጠቀሙ እንደነበር ታውቋል።

እንዲህ ያለውን በረዶ በመደበኛ የክረምት ወቅት የሚያገኙ የአውሮፓ አገሮች፤ በተለይም የስካንዲኔቪያን አገሮች፤ እንዲህ ባለው ወቅት ከአስፋልቶቻቸው ላይ በዶዘር በረዶውን ፍቀው ወደጎን በማስወገድ፤ አስፋልቱ ላይ ጨው በመነስነስ በረዶው እንዲቀልጥ ያደርጋሉ። የእግረኛ መንገድ ላይ ደግሞ ደቃቅ ጠጥር በመነስነስ የበረዶውን አንሸራታችነት በመቀነስ ሰዎች ተንሸራትተው እንዳይወድቁ ጥረት ያደርጋሉ። በዚህም መንግሥት ከፍተኛ ወጪ ያወጣል። በተለይም በረዶው ባየለ ወቅት ወጪውም ከፍ ይላል። ወጪው በበረዶው መጠን፣ የቆየበት ጊዜና በመሳሰሉት ይወሰናል።

ለምሳሌ ስዊድንን ብንወስድ፤ በክረምት ወቅት መኪኖች የበረዶ ጎማ የመቀየር ግዴታ አለባቸው። ይህንን አድርገው ባይገኙ ቅጣት ይቀጣሉ። ጎማው በረዶውን ቆንጥጦ የመያዝ ችሎታ ያለው ሲሆን፤ ፍሬን በሚያዝበትም ጊዜ ወደጎን ወይንም ወዳላስፈላጊ አቅጣጫ መኪናዋን እንዳያንሸራትታት ይረዳል። በዚህም በአንድ መኪና ምክንያት የሚደርስ ተቀጥያ አደጋን መከላከል ስለሚቻል ነው። በአርሲ አሾካ ቀበሌ ያሉ ነዋሪዎች እንዲህ ያለውን በረዶ ዐይተው ስለማያውቁም ኾነ ልምድ ስለሌላቸው፤ ክስተቱን በገመቱትና በመሰላቸው መንገድ ለመከላከል ርብርብና ጥረት ሲያደርጉ ታይተዋል። አካባቢው በክረምትና በዝናብ ወቅት ከበዛ ጭቃ እንጂ በረዶ አያውቅምና የሚቻላቸውን አድርገዋል።

የዓለም አየር ንብረት እጅግ እየተቀየረ መኾኑ ተደጋግሞ እየተነገረ ቢኾንም፤ የዓለም መንግሥታትም ኾኑ በርካታ የዓለማችን ነዋሪዎች ለጉዳዩ ቁብ የሠጡት አይመስሉም። ለንጽጽር ይረዳ ዘንድ በምዕራብ አርሲ ዞን ውስጥ፤ ኮፈሌ ወረዳ አሾካ ቀበሌ የተከሰተውን ይህንን በረዶ አንድ ብለን ብንመዘግብ፤ ከዚህ ሌላ ደግሞ ሰሞኑን የአዲስ አበባን አየር ንብረት ከከፍተኛ ሙቀት ወደ እጅግ የከፋና አስፈሪ ዝናብ መከሰትን ሁለት ብለን መመዝገብ እንችላለን። በሌላኛው አህጉር አውሮፓ ከስካንዲኔቪያን አገሮች ስዊድንን ሦስተኛ የንጽጽር አካባቢ አድርገን እንውሰድ።

ስዊድን በክረምቷ ወቅት ከኅዳር እስከ መጋቢት፤ ቢያንስ ሦስቱን ወራት ከፍተኛ በረዶ ይኖርባት ነበር። የአውሮፓውያን አቆጣጠር መገባደጃ ዲሴምበር ወር 2019 ጀምሮ እስካለንበት ማርች ወር 2020 ድረስ አብዛኞቹ የስዊድን ከተሞች ከሰባት ቀናት በላይ በረዶ አላገኙም። ይልቁንም ኃይለኛ ነፋስና ቀዝቃዛማ አየር ንብረት ነበራቸው።
የአገራችንን ሁለት ከተሞችና ስዊድንን ስንመለከትና ስናነጻጽር፤ የዓለም የአየር ንብረት ወዳልተጠበቀና ሊገመት ወደማይችል አቅጣጫ እየሔደ እንደኾነ ያሳያል። የዓለም መንግሥታትም ኾኑ በግለሰብ ደረጃ ሰዎች የዚህን ዓለም አቀፍ ችግር በጊዜ ተረድተው የሚበጅ መፍትሔ ማምጣት የማይችሉ ከኾነ፤ በመስኩ ያሉ ባለሙያዎች እያስጠነቀቁ ያሉት ዓለማችንን እስከማጥፋት የሚደርስ የአየር ንብረት ችግር ከመከሰት ምን ሊያግደው እንደማችል ጠቋሚ ነው። ዓለም ከአሁኑ መፍትሔ ካልወሰደ ምን እንደሚከሰት ምላሽ የሚሠጠው ጊዜ ብቻ ይኾናል። (ኢዛ)




