የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ላለማድረግ ያመለጠው ግለሰብ ወሎ ላይ ተያዘ
በዐረብ አገራት የኮሮና ቫይረስ በማኅበረሰቡ ላይ ከፍተኛ ሥጋት የሳደረ ሲሆን፣ በርካቶች በጁምአ በመስጅዶች መገኘታቸውን አልተዉም
ከዐረብ አገር ወደ ኢትዮጵያ የተመለሰ ነው
ኢዛ (እሁድ መጋቢት ፮ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. March 15, 2020)፦ ትናንት መጋቢት 5 ቀን 2012 ዓ.ም. በነበረው ትኩሳት የኮሮና ቫይረስ ምርመራ እንደሚደረግለት የተገለጸለት አንድ ግለሰብ፤ ከምርመራ ጣቢያው ቢያመልጥም፤ ዛሬ ደቡብ ወሎ ላይ ተያዘ።
ከዐረብ አገር ወደ ኢትዮጵያ የተመለሰ ነው የተባለው ይህ ግለሰብ፤ ትናንት በኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ሲመረመር ትኩሳት ስለነበረው፤ በዚህ ጥርጥሬ ተጨማሪ ምርመራ እንዲደረግለት ተወስኖ ነበር።
ኾኖም ግለሰቡ ትናንት ምርመራውን ሳያደርግ አምልጦ የወጣ ሲሆን፤ ዛሬ ግን በሕዝብ ማመላለሻ እየተጓዘ ደቡብ ወሎ ዞን ላጋምቦ ወረዳ ላይ ሊያዝ መቻሉ ተገልጿል። ግለሰቡ በጥርጣሬ ተጨማሪ ምርመራ ያድርግ የሚል ውሳኔ ተላለፈ እንጂ፤ ቫይረሱ ይኑርበት አይኑርበት በሕክምና አልተረጋገጠም።
ኢንስቲትዩቱ ለሚመለከታቸው አካላት በሠጠው መረጃ መሠረት፤ በክትትል ግለሰቡ ሊያዝ መቻሉ ተገልጿል።
በዚህ ጉዳይ ላይ የአማራ ክልል የመገናኛ ብዙኀን ኤጀንሲ ከተሠጠ መረጃ መረዳት እንደተቻለው፤ ከግለሰቡ ጋር የነበሩ ተጓዦች ለጊዜው ሆስፒታል እንዲቆዩ ተደርጓል ብሏል። (ኢዛ)



