National Electoral Board Of Ethiopia

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

መመሪያ ከመጽደቁ በፊት ከፓርቲዎች ጋር የተለያዩ ውይይቶች መደረጋቸው ተገልጿል

ኢዛ (ረቡዕ ታኅሣሥ ፳፱ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. January 8, 2020)፦ በወራት ልዩነት በሚካሔደው አገር አቀፉ ምርጫ ዝግጅት እያደረገ ያለው የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ በአዲሱ የምርጫ ቦርድ አዋጅ መሠረት የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባን የተመለከተ መመሪያ አወጣ።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በአዋጅ 1162፡2011 በተሠጠው ሥልጣን መሠረት የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባን አስመልክቶ ያዘጋጀውን መመሪያ ማጽደቁና ይህንንም ፓርቲዎቹ እንዲያውቁት ይደረጋል ብሏል።

የኢትየጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ታኅሣሥ 26 ቀን 2012 ዓ.ም. በቦርዱ ተመዝግበው የሚገኙ የአገር አቀፍና የክልል ፓርቲዎች በአዋጅ ቁጥር 1162፡2011 መሠረት ማሟላት ያለባቸውን ግዴታዎች ምን ምን እንደኾኑ የሚያመላክተው መመሪያ ከመጽደቁ በፊት ከፓርቲዎች ጋር የተለያዩ ውይይቶች መደረጋቸውንም አስታውቋል።

ቦርዱ ባጸደቀው በዚህ መመሪያ ሁሉም ተመዝግበው የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአዋጅ 1162፡2011 የተቀመጠውን የመሥራች አባላት ፊርማ ለማሟላት ሁለት ወራት የጊዜ ገደብ እንደተሠጣቸው የሚያመላክት ነው። ሌላው ጠቅላላ ጉባዔ ሳያካሒዱ ያለፈባቸው ፓርቲዎች በአዋጅ 1162 መሠረት አሟልተው በሁለት ወር ውስጥ ማሳወቅ ይጠበቅባቸዋል ይላል።

ጠቅላላ ጉባዔ በወቅቱ ያካሔዱ አገር አቀፍ ፓርቲዎች በአዲሱ አዋጅ 1163 ላይ የተቀመጠውን የጠቅላላ ጉባዔ መሥፈርት በማሟላት እስከ ጥር 2012 ዓ.ም. ድረስ አጠናቀው ማቅረብ እንደሚኖርባቸው የሚጠቁም ሲሆን፤ ጠቅላላ ጉባዔ በወቅቱ ያካሔዱ ክልላዊ ፓርቲዎች በአዲሱ አዋጅ 1163፤ የተቀመጠውን የጠቅላላ ጉባዔ መሥፈርት ለማሟላት እስከ ታኅሣሥ 2012 ድረስ አጠናቀው መቅረብ እንደሚኖርባቸው የሚያስገነዝብ መመሪያ ነው።

በቦርዱ ያልተመዘገቡ ነገር ግን በቀድሞው ሕግ በሒደት ላይ ያሉ፣ በቀድሞ መሟላት ያለበትን አጠናቀው በአዲሱ አዋጅ ያሉትን መሥፈርቶችም ጨምረው በጋራ ማጠናቀቅ የሚኖርባቸው የሚደነግገው ይህ መመሪያ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ብሔረሰቦችን የሚወክሉ ፓርቲዎች፤ ሕጉ ላይ ያለውን የመሥራች አባላት ቁጥር ከማሟላት መሥፈርት ነፃ እንዲኾኑም በመመሪያው ተካቷል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለሁሉም የተመዘገቡና በሒደት ላይ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ማሟላት የሚገባቸውን መሥፈርትና ጊዜ ገደብ የሚገልጽ ደብዳቤ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ውስጥ ለሁሉም ፓርቲዎች እንደሚያደርስ የገለጸ ሲሆን፤ በዚህ መመሪያ ዙሪያ ቦርዱ ተጨማሪ ማብራሪያዎችን እየሠጠ ይገኛል።

አዲሱን የቦርዱን አዋጅ ተከትሎ ባወጣው በዚህ መመሪያ፤ አገር አቀፍ ፓርቲዎች 10 ሺሕ የድጋፍ ፊርማ፤ የክልል ፓርቲዎች ደግሞ አራት ሺሕ የድጋፍ ፊርማ ማሰባሰብ የሚጠበቅባቸው ስለመኾኑ የሚደነግግ እንደኾነ ይታወቃል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ