ነገ ማለዳ ኢትዮጵያ የመጀመሪያዋን ሳተላይት ታመጥቃለች
ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ በቻይና የሕዋ ቴክኖሎጂ አካዳሚ የመጀመሪያዋን የኢትዮጵያ ሳተላይት (ETRSS-1) ሲጎበኙ
ETRSS-1 ሳተላይት ከቻይና መንግሥት ጋር በመተባበር የተሠራች
ኢዛ (ሐሙስ ታኅሣሥ ፱ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. December 19, 2019)፦ ነገ ታኅሣሥ 10 ቀን 2012 ዓ.ም. ማለዳ 12፡20 ሰዓት ላይ ኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ የሚኾነውን ሳተላይት ወደ ሕዋ ለማምጠቅ ተዘጋጅታለች።
ETRSS-1 የሚል ስያሜ ያላትን ይህቺን ሳተላይት ከቻይና መንግሥት ጋር በመተባበር የተሠራች ሲሆን፣ ነገ ከቻይት ትመጥቃለች።
የሳተላይት ማምጠቅ ፕሮጀክት አራት ዓመታት የፈጀ ሲሆን፣ ዋነኛ ተግባርዋም መረጃዎችን በማሰባሰብ ለተለያዩ ተቋማት ማቀበል ነው።
በተለይ ኢትዮጵያ ከተለያዩ ተቋማት በክፍያ ታገኝ የነበሩትን የተለያዩ መረጃዎች ከራሷ ሳተላይት በማግኘት ከፍተኛ ተጠቃሚ ያደርጋታል።
በቻይናውያንና በኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች በጋራ ዲዛይን የተሠራ ሲሆን፣ ከመጠቀች በኋላ መረጃ የምትቀበለው አዲስ አበባ እንጦጦ ላይ በተገነባው የመረጃ ማዕከል ነው። ለዚህም ሥራ ሥልጡን ባለሙያዎች ተዘጋጅተዋል። እነዚህ ባለሙያዎች 20 ሲሆኑ፣ ከእነዚህ ውስጥ አምስቱ ሴቶች ናቸው።
ባለሙያዎቹ ከሳተላይቷ የሚቀበሉትን መረጃዎች በመሰብሰብና ትንተና በመሥጠት ለሚመለከታቸው ተቋማት ያሠራጫሉ።
ነገ ማለዳ ላይ የምትመጥቀው የመጀመሪያዋ የኢትዮጵያ ሳተላይት ወደ ሕዋ የምታደርገውን ጉዞ በመገናኛ ብዙኀን በቀጥታ ይተላለፋል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ስለፕሮጀክቱና ስለሳተላይቷ የተለያዩ መረጃዎች እየተሠጡ ነው።
ETRSS-1 ሳተላይት በምትመጥቅበት ወቅት የኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በማምጠቂያ ማዕከሉ የሚገኙ ሲሆን፣ ዕለቱን በታሪካዊነት ለመዘከርም በአዲስ አበባ የተለያዩ ፕሮግራሞች እንደሚካሔዱ ታውቋል። (ኢዛ)



