ኢትዮጵያውያኖችና አሜሪካኖች ለፍትህና ዲሞክራሲ በኢትዮጵያ

ሎስ አንጅለስ

በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያውያን ስፖርት ፌደሬሽን ውስጥ የተሰገሰጉ የወያኔ ካድሬዎች ሲጋለጡ

ታህሳስ 30፤ 2004

 

የኢትዮጵያን የእግር ኳስ ፌደሬሽን በሰሜን አሜሪካ ከተመሠረተ እነሆ 28 ዓመቱን በሚመጣው ጁላይ መጀመሪያ፣ 2012 ዓም በዳላስ በሚያከብረው ዓመታዊ በዓሉ በደማቅ ሁኔታ ለማስታወስ በዝግጅት ላይ ነው። ይህ ፌደሬሽን ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በስደት ለምንገኘው ኢትዮጵያውያን በዓመት አንዴ በአንድ ከተማ ከያለንበት በመምጣት ተሰባስበን እግር ኳሱን ብቻ ሳይሆን፤ ባህላችንን ለልጆቻችንና ለምንኖርበት ዓለም የምናስታዋውቅበት ወቅት ነው። ስደተኛው ባመዛኙ በደርግና በተለይም በትግራይ ነጻ አውጭ ግንባር ግፈኛና ዘረኛ አገዛዝ ምክንያት ተመሮ ገሚሱም ህይወቱን ለማትረፍ ሲል ከውድ ሀገሩ ሳይወድ ተገዶ ከፍተኛ መስዋዕትነትን በመክፈል የተሰደድ ነው። የዚህን ዓመታዊና ኢትዮጵያዊ ባህል በተለይም ለወጣቱ ትውልድ የኢትዮጵያዊነት መሠረቱን የሚያስታውሰውና ከውድ ወገኖቹ ጋር በይበልጥ የሚያቀራርበው ለመሆኑም የሚያጠያይቅ አይደለም።

 

በሌላ በኩል ዘረኛው የትግራይ ነፃ አውጭ ግንባር የሀገራችንን መንግሥት በትረ ሥልጣን በሀይል ከተቆጣጠረ ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ከምድረ ገጽ ለማጥፋት የማያደርገውና የማይፈጽመው ተግባር እንደሌለ በሀያ ዓመታት አገዛዝ ዘመኑ በማያሻማ ሁኔታ አረጋግጦልናል። የኢትዮጵያ ታሪክ ከአንድ መቶ ዓመት ባላይ አያልፍም፤ ለዘመናት ተባብሮና ተቻችሎ የሚኖረውን ሕዝባችንን በዘር አጥር ውስጥ እንዲሰባሰብና አንዱ ባንዱ ላይ በጠላትነት እንዲነሳሳ፤ የሀገሪቱን ሀብት ለውጭ ባለሀብቶች አሳልፎ የሚሰጥ፤ ሀገሪቱን ያለባሕር ወደብ ያስቀረና አሁንም ህዝቡ የለፋበትን ሀብት በሚያሳፍርና በሚያስገርም ሁኔታ ከሀገር ውጭ በማሸሽ ላይ የሚገኝ የዘራፊና ‘የባዕድ መንግሥት’ ለመሆኑ የአደባባይ ምሥጢር ነው። የጭቆና ጊዜውን ለማራዘምም ሕዝቡን በከፋፍለህ ግዛው ፓሊሲ በሀገር ቤት እያመሰው ሲሆን፤ ይኅንኑም ፓሊሲውን በወጭው ዓለም ለማስፈጸም በቂ ዝግጅት ካደረገ ቆይቶአል። ለዚህም እንቅስቃሴው እንዲያመቸው በውጭ ጉዳይ ሚንስቴር መ/ቤቱ አማካኝነት የአፈጻጻም ሥራ መመሪያ አውጥቶ በውጭው ዓለም ለሚኖሩ ሆድ አደር ካድሬዎቹ እንዲተገበሩት ያለሀፍረት አሰራጭቶአል። የወያኔ ከፍተኛ ካድሬዎችና ባለሥልጣናት የነበሩ ታማኝ አገልጋዮቹን በዋና አስፈጻሚነት በመላው ዓለም በሚገኙ ኤምባሲዎቹ ሁሉ መድቦአል።

 

ዛሬ በየምንኖርበት አካባቢዎች ሁሉ በሀይማኖት ተቋሞች፤ በንግድ ድርጅቶችና ማህበሮች፤ ኢትዮጵያውያኖች በሚሰባሰቡበት አካባቢ   ሁሉ ወያኔ የስለላና የብተና ካድሬዎቹን በማሰማራት ቢቻል የወያኔ ተቀጥላ ድርጅት ማቋቋም ካልሆነም እንዲበተንና አባላቱ እንዲበጣበጡ እያደረጉ ነው። በየቤተ ዕምነት ቦታዎች ሁሉ ስለሀገር መቆርቆር፤ የሕዝባችንን ብሶት ማሳወቅና ማውራት ሁሉ የፓለቲካ ጉዳይ ስለሆነ አይቻልም በሚሉ የተሳሳቱ ካህናቶች አማካኝነት የሀገር ወዳዱን ጎራ ለማኮላሽት እየጣሩ ለመሆኑ የተዋህዶ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን የሆንን ሁሉ በሚገባ የምናውቀው ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ወደ ሀገር ግቡና ወይንም በሀገር ቤት የንግድ ሥራ ላይ ብትሰማሩ ድጋፍ እንሰጣለን ቢሉም በፕሮፓጋንዳቸው ተታለው የገቡ ወገኖች ንብረታቸው ተዘርፎ ልፋታቸውን ለወያኔ ባለሟሎች አስረክበው የተመለሱ ወገኖች ብዛት ቀላል አይደለም። በቅርቡም ከኢትዮጵያ ካዝና ከ2009 ጀምሮ እስከአሁን ወደ ውጭ ሀገር የወጣው 11.5 ቢሊዮን ዶላር የኢትዮጵያ ሕዝብ ገንዘብ ወዴት እንደገባ ምንም ማስረጃ እንዳልተገኘለት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታውቆአል። ስለዚህ የዚህ ዓይነቱ በንግድ ሥራ ስም የሚደረግ ጥሪ ለዘረፋ እንጂ ለልማት እንዳልሆነ ወገኖቻችን ሁሉ እንዲያውቁት ያስፈልጋል።

ከፍ ብሎ በተዘረዘረው መንገድ ነው ወያኔና ግብረ አበሮቹ በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያ የስፖርት ፌደሬሽን ውስጥ ስዎቻቸውን ሰርገው በማስገባት በተለያዩ ጊዜያቶች ድርጅቱን ወያኔ በኢትዮጵያንና ኢትዮጵያኖች ላይ ለሚያካሂደው የጥፋት ዘመቻ ማስፈጸሚያ ለማድረግ ያላሰለሰ ጥረት ሲያደርጉ የኖሩት። አንደኛው ፤ የወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳን እንግድነት በአለቆቻቸው ትዕዛዝ መሠርት ላለመቀበል ሲሉ የብዙሃኑን አባላት ድምጽ በማፈን የወያኔ ተገዥነታቸው የተረጋገጠበት ወቅት ነበር። ለዚህም የድርጅቱ አባላት ዓመታዊ ስብሰባቸውን በማካሄድ አባላትንና ሕዝቡን ለመካፋፈልና ድርጅቱን ለመበተን ሙከራ ያደረጉትን ከሀዲዎች በሀገርና ወገን ወዳድ አባላት እንዲተኩ አድርጓል። ድርጁቱም የነዚህን ሆድ አደሮች ሴራ በሚገባ ተገንዝቦ ለወሰደው እርምጃ እኛም ሆንን መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ወቅቱን ጠብቆ ውለታውን እንደሚከፍል አንጠራጠርም።

እነዚህ ግለሰቦች አሁንም ሴራቸውን ያላቆሙ ሲሆን፤ እንዳውም ከወያኔና አጫፋሪው መሀመድ አላሙዲ በሚያገኙት ከፍተኛ የገንዘብ ድጎማ በመደገፍ ሌላና አሰገራሚ የጥፋት ፕሮጀክት ይዘው ብቅ ብለዋል። እ ኤ አ  ዲሰምበር 28፤ 2011 በተጻፈ ደብዳቤ ግለስቦቹ በተመሳሳይ ስም የሚጠራ አዲስ የስፖርት ፌደሬሽን እንዳቋቋሙ ገልጸው የቀድሞውንና ህጋዊውን ድርጅት ትታችሁ እኛ በምንመራው ማህበር ውስጥ ኑና ተሰባሰቡ በማለት ለእያንዳንዱ አባል ማህበር ጥሪ አስተላልፈዋል። በያዝነው ዓመት ለሚደረገው ዝግጅትም ሙሉ ክፍያ ፈጽመው በዋሸንግተን ዲሲ አንድ ስታዲዮምና አንደኛ ደረጃ የሆነ ሆቴል በቅድሚያ መከራየታቸውን ገልጸዋል። በተጨማሪም ለእያንዳንዱ ፈቃደኛ ሆኖ ለሚመጣ አባል የአውሮፕላን መጓጓዧ ወጭ ጨምሮ እንደሚሸፍኑ ያለማፈር አስታውቀዋል። ይኅ ሁሉ ወጭም በማን እንደሚሸፈን የአደባባይ ምስጢር ነው። በቅርቡም ለቅድመ ዝግጅታቸው እንዲረዳ በማለት እነዚሁ ግለስቦች በሎስ አንጀለስ ከተማ ለሶስት ቀኖች የሚቆይ ስብሰባ ወጭውን ሙሉ በሙሉ በመሽፈን ለማካሄድ በዝግጅት ላይ እንደሆኑ ለማወቅ ተችሎአል። ጥሪአቸውን ለሚቀበል እያዳንዱ የስፖርት ቡድን አሥር ሺ ዶላር እንደሚለግሱም ቃል ገብተዋል።

 

በአንጻሩ የማህበሩ አባላት፤ ቡድኖችና ተባባሪዎች በአንድ ድምጽ እያወገዙአቸው ይገኛሉ። እኩይ ሤራቸውም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በይፋ ተጋልጦ፤ የሴራው አቀንቃኞች ታውቀው በዋናው ማህበር ተገቢው እርምጃ እንደሚወሰድ አንጠራጠርም። ድርጁቱን ነቅተው በመጠበቅ፤ ክነዚህ ከሀዲዎች ተከላክለው ያቆዩንና አሁንም ተንኮለኞቹ የፈለፈሉትን ሴራ ያከሸፉትን ወገኖች ከልብ ልናመሰግናቸው ይገባንል፤ ህዝብም በጎ ድርጊታችውን እንዲያውቅ የማድረግ ሁላችንም ሀላፊነት አለብን። በዚህ አኳያ በሎስ አንጀለስ የሚገኙት የዳሎል፤ የኤል ኤ ስታርስና የአበበ ቢቂላ የእግር ኳስ ማህበሮች እነኝህን ሆድ አደሮች አሳፍረው በመመለሳቸው መመስገንና አይዞአችሁ ሊባሉ ይገባል። እኛም በሎስ አንጀለስ የዲሞክራሲና ፍትህ በኢትዮጵያ ስብስብ አባላት እነዚህን ሴረኞች ለመቋቋምና የጥፋት ዓላማቸውን ለማክሸፍ በከተማችን ከሚገኙ የፌደረሽኑ አባላት ጎን የምንቆም መሆናችንን እንገልጻለን።

 

ኢትዮጵያውያንና አሜሪካኖች ለፍትህና ዲሞክራሲ በኢትዮጵያ

 

ሎስ አንጅለስ

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ