Ethiopian Youth National Movement የኢትዮጵያ ወጣቶች ብሔራዊ ንቅናቄየኢትዮጵያ ወጣቶች ብሔራዊ ንቅናቄ

የኢትዮጵያ ወጣት ሆይ በአሁኑ ወቅት ስራ ሰርተን፤ እዚህ ደረጃ ላይ እንደርስበታለን፤ ህይወታችንን በዚሀ የስራ መስክ እንገነባለን ብለን እንድናልም የሚያደርገን እድል ከፊታችን ጠፍቷል። ዛሬ ሥልጣን ላይ በተፈናጠጡትና ሀገሪቱን በተቆጣጠሩት ኃይሎች ዙሪያ ባለማጨብጨባችን ብቻ የወደፊት እድላችን፤ እጣፈንታችን ሁሉ እየተዘጋብንና ጊዜ እያለፈብን በገዛ አገራችን የበይ ተመልካች ሆነናል።

 

 

የትምህርት ጥራት ጉድለት፤ ስራ አጥነት፤ በሱስ መጠመድ፤ ስደት፤ የወጣት ሴተኛ አዳሪነት እና የመጠለያ እጦት ችግሮች እየተፈራረቁብን ነው። ከተጠቀሱት ችግሮች መካከል የትምህርትን ብቻ እንኳ ብንወስድ፤ በዚህ ስርዓት ውስጥ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃን ካጠናቀቁ ከ1000 ተማሪዎቸ ውስጥ አምስት ተማሪዎች ብቻ ወደ ከፍተኛ ተቋማት እንዲገቡ ይደረጋል። ይህም በዓለም በጣም ዝቅተኛ ከተባሉት ጎራ የሚመደብ ነው። ከዚህ ቁጥር የተረፉት ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ሁሉ የጨለመ እድል ከፊታቸው ተደቅኗል። ታዲያ በወያኔ ኢህአደግ ስርዓት ውስጥ የከፋና የመረረ፤ ትርጉም የለሽ ህይወት እየኖሩ ካሉት ሚሊዮን እትዮጵያውያን ውስጥ ከሆንን መጪውን አብዮት ከሚመሩት የለውጥ መሪዎች እራሳችንን እንደ አንዱ ልንቆጥረው ይገባል። ማንም መርቶ ነጻ አያወጣንም። እራሳችን የራሳችንን እድል የመወሰንና ወደተሻለ ለውጥ የማምጣት ግዴታ አለብን።

 

በዓለም ላይ የታወቁ ታላላቅ የፖለቲካ ለውጦች ካንድ ቦታ፤ በጥቂት ግለስቦች የተጀመሩ ናቸው። ስለዚህም ልክ የቱኒዚያና የግብጽ ወጣቶች እንዳደረጉት አኛም የኢትዮጵያን አብዮት ለማቀጣጠል እድሉና ምክንያትነቱ በእጃችን ይገኛል። ስኬታማ ለመሆንም መጀመሪያ ከቤታችን እጀምር። ከዚያ ለወዳጆቻችን፤ ለጎረቤቶቻችን፤ እንንገር። ትግላችንን እናፋጥን። ሐሳቡ ወያኔና አጫፋሪዎቻቸውን ወደ ጎን በመተው፤ ትግላችንን ከኢትዮጵያ ወጣቶች ብሄራዊ ንቅናቄ ጋር በማጣመር ህብረተሰቡ ከጎናችን እንዲቆም ማድረግ ነው። የምንፈጥረው ቡድን የሚነድፋቸው ስልቶችና የሚከውናቸው ድርጊቶች፤

 

1. የወያኔን የኢኮኖሚና የፖለቲካ መሰረቶች ማናጋት

 

2. ወያኔና ደጋፊዎቻቸውን ለይቶ ማወቅና ትግሉን እንዲቀላቀሉ ጥረት ማድረግ

 

3. አብዮቱን ማቀጣጠልና ማፋፋም

 

4. ከወያኔ ውድቀት በሗላ የወጣቱ ንቅናቄ ከሌሎች የሲቪከ ሀይሎች ጋር በመተባበር ለሚፈጥረው የሽግግር አካል አጋር መሆን

 

የኢትዮጵያ ህዝብ የፍትህ የነጻነትና የዲሞክራሲ ባለቤት እንዲሆን ለሀገራችን የፖለቲካ ለውጥ ማምጣት የወጣቱ ትውልድ ግዴታ ነው። ብሎም ወጣቶች ህልማችንን እውን ለማድረግ የሀይማኖት፤ የጎሳ፤ የጾታ፤ የቋንቋ ልዩነት ሳይገድበን የሀገራችንን የወደፊት እጣ ፈንታ ለመወስን እስክንችል ለማይበገር ቀጣይ ህዝባዊ እምቢተኝነት አመጽ በቆራጥነት መንቀሳቀስ ይጠበቅብናል። ፕሬዚደንት ኦባማ ለጋናና ለግብጽ ህዝቦች ባደረጉት ንግግር እንደተናገሩት፡ “የአፍሪካ የወደፊት ብሩህ ተስፋ በአፍሪካ ወጣቶች እጅ ላይ ነው።” ስለሆነም መጪው አዲስ ዘመን የለውጥና የወያኔ ግፍ አገዛዝ ማክተሚያ እንዲሆን የሕዝባዊ እምቢተኝነቱን እንቅስቃሴ ከዛሬ ጀምሮ ለማቀጣጠል እያንዳንዳችን እንዘጋጅ።

 

የኢትዮጵያ ወጣቶች ብሄራዊ ንቅናቄ ለራሱ የፖለቲካ ስልጣን የማይታገል ከማንኛውም የውስጥና የውጭ የፖለቲካ ሆነ የሲቪክ ተቋማት ተጽኖና ቁጥጥር ነጻ የሆነና ለህዝብና ለህግ የበላይነት፤ ለዜጎች መብትና እኩልነት፤ ለሀገር ሉዓላዊነት፤ ለፍትህና ለዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታና እድገት የሚታገል የቆራጥ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ዓለም አቀፍ ንቅናቄ ነው።

ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!

የኢትዮጵያ ወጣቶች ብሔራዊ ንቅናቄ

ድረገጽ : www.eynm.org

ኢሜይል : This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. / This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

ፌስ ቡክ : www.facebook.com/TheEthiopianRevolution2011

ትዊተር : @EthioYouthMove

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ