“... በታሪክ መድረክ ሚናቸውን ተጫውተው ያለፉ ሰዎች እንደ ተውኔት ገፀ ባህርያት ናቸው። ስለሆነም የዕለት ተዕለት ሰብዓዊ ግኑኝነቶችም ሆኑ በመሪና ዜጋ መካከል ያለው ግንኙነት ኅሊናችንን ሳይጫነው ልንፈርድባቸውም ሆነ ልንፈርድላቸው ይገባል ...” ያሉት እውቁ የታሪክ ሊቅ ፕሮፌሠር ባህሩ ዘውዴ ናቸው።

 

በርግጥም ታሪክ የትናንት ሁነትን ዛሬ ማንበብ ወይም መስማት እንደመሆኑ፣ የየባለታሪከኞችን ገፀ-ባህሪ ከመመልከት ባለፈ ኅሊናዊ ፍርድ ሰጪው የታሪክ ተመልካቹ ነው። ይህን እውነታ ተከትለን ከዛሬ 92 ዓመት በፊት በዚህ ቀን በሀገራችን ተከናውኖ ስለነበረ አንድ ታላቅ ታሪካዊ ድርጊት ማውሳት ፈለግን።

 

ጉዳዩ የሚጀምረው ከአጤ ሚኒልክ ሞት በኋላ አልጋውን በወረሱት አቤቶ አያሱ ነው። በአንዳንድ ታሪክ ፀሐፊዎች ዘንድ መልካምም እኩይም ባህርይ ተሰጥቷቸው የተጻፉት አቤቶ አያሱ በርግጥም በዘመናቸው ጠንካራ ተቃውሞ አላጣቸውም። የዚህ ተቃውሞ ውጤት ደግሞ እርሳቸውን ከሥልጣን አውርዶ፣ ለአልጋው ተገቢ የሆነ ሰው መምረጥ ነበርና ለቅዋሜው ምክንያት የሆኑ ነገሮች ምን እንደሆኑ ህዝብ እንዲያውቅ ተደርጓል።

 

እናም አቤቶ ኢያሱን ከሥልጣን ለማውረድ ውስጥ ለውስጥ ሲብላላ የቆየው ሤራ በመጨረሻ ላይ ይፋ የሆነው ከዛሬ 92 ዓመት በፊት መስከረም 17 ቀን 1909 ዓ.ም. ነበር።

 

በክርስቲያን ኢትዮጵያ ያውም በበዓለ መስቀል የደመራንና የመስቀሉን ሥርዓት አስታጉሎ፣ የሸዋ መኳንንት በኢያሱ ላይ ያስነሱት ተቃውሞ ምንድነው? መርስዔ ኀዘን ወልደቂርቆስ “የዘመን ታሪክ ትዝታዬ ካየሁትና ከሰማሁት” በሚል ርዕስ ካዘጋጁት መጽሐፍ እንዲህ ይነበባል፡-

 

“… መስከረም 17 ቀን ረቡዕ በ3 ሰዓት አቡነ ማቴዎስና ዕጨጌ ወልደጊዮርጊስ፣ በሊጋባው ተጠርተው ወደ ግቢ መጡ። እንዲሁም ሚኒስትሮችና በአዲስ አበባ ያሉ መኳንንት፣ ሻለቆችና ሻምበሎች ሁሉ ሠራዊታቸውን እያሠለፉ መጥተው በቤተመንግሥቱ ግቢ ተሰበሰቡ። ከሚኒስትሮች ደጃዝማች አብርሃ ብቻ በቤታቸው ቀርተው ነበር።

 

እነዚህ ኹሉ በግቢው ውስጥ በአዳራሹ አጠገብ በአደባባዩ ላይ ወደ ተተከለው አጅባር ድንኳን ገብተው አቡኑና ዕጨጌ በመካከል፣ ሚኒስትሮችና መኳንንት፣ ሻለቆችና ሻምበሎች በቀኝና በግራ በየማዕረጋቸው ከተቀመጡ በኋላ ልጅ ኢያሱን ለመሻርና አዲስ መንግሥት ለማቋቋም የተፈለገበትን ምክንያት ለህዝብ ለማስረዳት፣ በጉባዔው መሪዎች ተዘጋጅቶ የተጻፈውን ቃል ከንቲባ ወልደ ጻድቅ ጐሹ አነበቡ፣ ቃሉም ከዚህ ቀጥሎ ያለው ነው፡-

 

ጃንሆይ ዐፄ ምኒልክ ከኃይማኖትዎና ለመንግሥትዎ እጅግ ተጨናቂ ነበሩና እንዳለፉት ነገሥታት ጊዜ፣ ሠራዊትዎ እርስ በርሱ እንዳይተላለቅብዎ፣ በመንግሥትዎ ነፋስ እንዳይገባበት አስበው ፈጽመው እቤት ሳይውሉ በ1901 ዓ.ም. ሊቀጳጳሱና እጨጌው ቆማችሁ፣ መኳንንቱንና ህዝቡን ሰብስበው፣ “ልጅ ኢያሱን ሰጠቻችኋለሁና ከሱ ፈቃድ የወጣ ሰው ርጉም ይሁን፣ ጥቁር ውሻ ይውለድ” ብለው ሰጡን። እሱም እናንተን ያለአግባብ የበደለ እንደሆነ ርጉም ይሁን፣ ጥቁር ውሻ ይውለድ ብለው ሰጡን። አባታችንም ዕጨጌም በዚሁ ቃል አውግዛችሁ ሰጣችሁን። እኛም ደስ ብሎን ተቀበልን። የግዝትም ቃል እንዳይናወጥብን ተጠንቅቀን በእያለንበት ሀገር ሁሉ በትሕትና ራሳችንን ደፍተን፣ በተቻለን በሙሉ ልባችን መንግሥታችንን እየረዳን እስካሁን ቆየን። ከግዝትም ቃል የወጣ ሥራ እንዳልሠራን አባታችንም መላ ኢትዮጵያም ያውቃል። የምናስታውቀውም ቃል ይህ ነው፤

 

መጀመሪያ

ጃንሆይ ማረፋቸውን ሰው ሁሉ በልቡ እያወቀው፣ ባረፉበት ዘመን በልጅ ኢያሱ ትዕዛዝ ሰው ሁሉ ፈረሱን እየጫነ ጉግሥ ሲጫወት ሰነበተ። የቀረው ቢቀር በዚያው ሰሞን ማዘን መተከዝ ይገባ ነበር። መኳንንቱና ህዝቡም ለጌታው ሳያለቅስ ዕንባውን እንዳረገዘ ቀረ። ምኒልክን የመሰለ የድኻ አባት እናት፣ የነጋሢው ንጉሣችን መላ ኢትዮጵያን አንድ አድርገው አስማምተው፣ አህዛብን አቅንተው፣ ባጸኑት መንግሥት፣ ባሠሩት አብያተክርስቲያናት ጥዋፍ ዕጣን ሳይባል ቀረ።

 

ዐፅምዎም የወደቀበትን ቦታ አባታችን ያውቁታል። በጃንሆይ ማረፍ ህዝቡ በግልጥ እንዳያለቅስ ማድረጋቸውና ፍታት አለማስፈታታቸው፣ መንግሥት እንዳይነቃነቅባቸው ይሆናል። ተዛሬ ነገ ፍታት አስፈቱ፣ ምጽዋት አድርጉላቸው ይሉናል እያልን ስንጠብቅ ይህንን ያህል ቀን ቆየን። ያባታቸውን ማረፍ ከምንም ሳይቆጥሩት የቀሩት ለካስ ኃይማኖታቸውን ከለወጡ ብዙ ጊዜያቸው ኑሮዋል።

 

ሁለተኛ

ኃይማኖታቸውን መለወጣቸውንና ከክርስቲያን መንገድ መውጣታቸውን መግለጥ ከወጠኑበት ቀን ጀምሮ፣ የሠሩትን ያልተገባ ሥራ ሁሉ ጽፈን ለመጨረስ አይቻልምና ዋና ዋናውን ብቻ ባጭር ቃል እናመለክታለን።

 

ጌታችን ጃንሆይ እኔው ተሽቀዳድሜ፣ በቶሎ ባገሬ የአውሮጳን ሥራት ካላስገባሁና በሁሉም ነገር እነሱን ካልመሰልኋቸው አይሆንም ብለው፣ የአውሮጳን ሥራት ማስለመጃ ይሁን ብለው፣ የሌሊት ዘበኛ ቢያቆሙ ልጅ ኢያሱ አስር፣ አስር አሽከሮቻቸውን እያስከተሉ ሌሊት እየዞሩ፣ ዘበኞቹን እየገደሉ በከንቱ ደማቸውን እያፈሰሱ፣ የቆመውን ደንብ ስለማይረባ ነገር በገዛ እጃቸው አፈረሱት።

 

ሦስተኛ

የእስላም ቃልቾች እየሰበሰቡ፣ የመሐመድንና የግራኝን ታሪከ-ነገሥት እያስነበቡ የአያቶቻቸውን ዘር እያስቆጠሩ፣ የይማሞች ዘር ከመሐመድ ዘር የወረደ ነው አሰኝተው እስላምነታቸውን ካደላደሉ በኋላ፣ የእስላም ቤት እየፈለጉ የጅማ አባ ጅፋርን ልጅ፣ የእህቱንም ልጅ፣ የአሚር አብዱላሂን ልጅ፣ የነጋድራስ መሐመድን ልጅ፣ የአዳልንም የባላባት ልጅ፣ ያሰን አንጃሞንም ልጅ እነዚህን ሁሉ እያስፈለጉ አግብተው ቁባት ቀበቱ።

 

የቀሩትማ የእስላም ሴቶች ስንቱ ተጽፈው ያልቃሉ፣ እንኳንስ ያልተጠመቀችውንና ክርስቲያንም ብትሆን በመጽሐፋችን የታዘዘው አንድ ወንድ ላንዲት ሴት ነው።

 

አራተኛ

አባታችንም ዕጨጌም ይህን ሁሉ ሥራ ሲሠሩ እያወቁና እየሰሙ፣ መክረው ለመመለስ ተሸነፉ። አባታቸውም ንጉሥ ሚካኤል ልጃቸውን መክረው ከዚህ ክፉ መንገዳቸው ይመልሱልናል ብለን ተስፋ ስናደርግ አሸንፈዋቸው ኖሩ።

 

አምና በፍልሰታ የእስላም ጦም ገጥሞ ነበር። በአባታቸው ከተማ በደሴ ላይ የሠሩት የክህደት ሥራ፤ በጅሌና በጥሙጋ፣ በጨኖ በጅላሌ ሲያደርጉት የከረሙት ሥራ ሁሉ ቢጽፉትም አያልቅ። ለመስማትም ደስ አያሰኝ። ይህን ሁሉ ሥራ ሲሠሩ መኳንንቱም ሠራዊቱም እያየ፣ እየሰማ ሕፃን ቢሆን ነው እያለ ትዕግሥት ቢያበዛ፣ ልጅ ኢያሱ ዘውዳቸውን ጭነው፣ በክርስትና ፀንተው፣ መንግሥታቸውን ጠብቀው መያዝና ማጥናት ጠልተው ዕድሜያቸው ለዕውቀት ሲደርስ ሃያ ዓመት ሲሞላቸው የቃልቻ ቃል እየሰሙ፣ የክርስቲያን መንግሥት አልቋል፣ ከመሐመድና ከግራኝ ዘር የወረዱት የይማሞች መንግሥት መነሻው ደርሰዋል እያሉ በሐሰት ቢያታልላቸው፣ እውነት መስሎዋቸው ልጅ ኢያሱ አምና ሐረርጌ የወረዱ ጊዜ አራቱ አድባራት ቤተክርስቲያን ገብተው አንድ ጊዜ እጅ ሳይነሡ ቀሩ። ከዚያም ሁሉ አብያተክርስቲያናት ላንዱ እንኳ ገንዘብ ሳይሰጡ የመላ ሐረርጌ እየተሰበሰበ ከሚሠግድበት መስጊድ ሂደው አብረው ሰገዱ። በአምስቱ በር ዙሪያ ላሉት መስጊዶችና ቃልቾች አትርሱኝ እያሉ ብዙ ገንዘብ ሰጡ።

 

አምስተኛ

ጃንሆይ ሐረርጌን የሰበሩ ጊዜ ከክርስቲያን ሲዋጋ ያለቀውን እስላም፣ ቦታውንና ቤቱን ሁሉ ጃንሆይ በፈቃድዎ ለመንግሥት ርስት ይሁን ብለው፣ ለካህናትና ለከተማው ዘበኛ ከከተማ ለማይለይ ሰው ሰጥተው፣ ይህን ያህል ዘመን ይዞት የኖረውን ቤትና ቦታ ለእስላሙ ልቀቁ ብለው አስለቀቁት። ካህናቱም ከታቦት ተለይተው እያዘኑ ወደ ውጪ ወጡ። ድኻውም እያለቀሰ ለቀቀ።

 

ስድስተኛ

ያሩሲ ኦሮሞ ሸፍቶ፣ ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስና ቢትወደድ ኃይለጊዮርጊስ ሽፍታውን ለማረጋጋት ሰው ቢልኩ፣ ይኸው ከጥፋት ተቈጥሮባቸው ተነቀፉበት። ይህም እስላም እንዳይነካ በማድላት ነው።

 

እንደዚሁም የመሰለ በደጃዝማች ተፈሪ ግዛት በውጋዴን 45ቱን የክርስቲያን ወታደር ሱማሌ አርዶዋቸው ሥራት ሳይታይላቸው ቀረ። ከቶውንም ሱማሌዎቹ ወደ አዲስ አበባ ቢመጡ ተሸልመው እንደገና ወደ ውጋዴን ሄዱ። የክርስቲያኑም ደም እንደ ውሻ ደም ሆኖ ቀረ። በዚህም ነገር እስላሙ በክርስቲያን ደም መቀባቱ በርሳቸው ዘንድ የተመሠገነ እንደሆነ በሥራቸው ተገለጠ።

 

ሰባተኛ

በአዲሱ ከተማ በድሬዳዋ ላይ ቀድሞ ያልነበረው መስጊድ ተሠርቶ፣ አሁን ከዚህ የወረዱ ጊዜ የእስላም ዓሊሞች ልብስ ለብሰው፣ የእስላም አጠማጠም ጠምጥመው፣ ግልድም አገልድመው፣ ፈጽመው የክህደት ሥራ ሠርተው እመስጊድ ገብተው አብረው ሠገዱ። ለመስጊዱም ብዙ ገንዘብ ሰጡ።

 

የኛ ታቦት ግን አስቀድሞ በዚያ ተቈርቁሮ፣ ተተክሎ የነበረውን በመቃኞ የኖረውን፣ ካህናቱም መኳንንቱም ቢያስታውቁ እምቢ ብለው እስካሁን ሳይሠራ ቀርቶ፣ የመስጊዱ ሥራ በልጦ ቀደመው።

 

ስምንተኛ

ጅጅጋ ላይ ዳርቻ ሀገር ነውና በዚያ ውስጥ የሚቀመጥ ክርስቲያን መቅደስ ካልተተከለበት ሰውነቱን ያረክሳል፣ ያማግጣል ብለን የተከልነውን ታቦት ይህ ለመስጊድ የሚሆን ቦታ ነውና ታቦቱ ከሌላ ቦታ ሄዶ ይደረብ ብለው፣ ካህናቱም ታቦቱን ይዘው ጊሪ ከሚባል ቦታ ተዳብለው ተቀምጠዋል። ይህስ እስላም ነኝ፣ የእስላም ኃይማኖትን አጽኚ ነኝ ማለት አይደለምን። አሁን መጠቅለያውን ደግሞ የሐረርጌ መድኃኔዓለም ቦታ ቀድሞ መስጊድ ነበርና ታቦቱ ይውጣና እንደ ጥንቱ መስጊድ ይሁን ብለው ነበር። ነገር ግን በቅርብ ቀን ነገር የሚነሣባቸው ቢሆን ለጊዜው ተዉት፤ በኋላ ግን ያሰቡትን ሳይፈጽሙት አይቀሩም ነበር።

 

ዘጠነኛ

ከዚህ ሁሉ የሚከፋ ሥራ ሲሠሩ፣ እስካሁን ድረስ ከእስላም ጋር እየተጋደለ፣ በክርስትና ፀንቶ፣ በዓለሙ ሁሉ ታውቆ፣ ራሱን ችሎ የኖረውን የኢትዮጵያን መንግሥት ስሙን ከምድር አጥፍተው፣ ኃይማኖቱን አስለውጠው፣ የመንግሥታችን ስም የክብር መጠሪያ በሆነው በሰንደቅ ዓላማችን ላይ “ላኢላህ ኢላላህ መሐመድ ረሱል አላህ” ብለው አስጥፈው፣ ወስደው ለቱርክ መንግሥት ቆንስል አስረከቡት።

 

ሰንደቅ ዓላማ ማለት ትርጓሜው በመንግሥት ፈንታ ሆኖ ለዓለም ሁሉ የሚታይና የሚታወቅ ምልክት ማለት ነው። ለዚሁም ምስክር መንግሥት ሲባል ሰንደቅ ዓላማ የሌለው መንግሥት የለም።

 

የቱርክ መንግሥት ቆንስልም፣ ይህንን ሰንደቅ ዓላማ ተቀብሎ፣ ብዙ ደስታ አድርጎ ሻምፓኝ እየጠጣ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የእስላም ኃይማኖት ከዓለም ሁሉ ኃይማኖት የተመረጠ መሆኑን ተረድቶ ዛሬ አመነ፣ ለዚህም ምስክር ሰንደቅ ዓላማውን ለእስላሞች ጠቅላይ ለቱርክ መንግሥት ሰጠ፣ እንግዲህ ከዛሬ ጀምሮ የቱርክና የኢትዮጵያ መንግሥት አንድ መሆኑን የሚጠራጠር ሰው ቢገኝ ወንጀል ይሆንበታል ብሎ በጉባዔ መካከል ቆሞ መረቀ።

 

የውጪ መንግሥት እንደራሴዎች ይህን ሰምተው፣ ሰንደቅ ዓላማችሁን አስመልሱ እያሉ ቢመክሩ የሚሰማቸው ጠፍቶ፣ ሰንደቅ ዓላማው አሁንም በቱርክ መንግሥት ቆንስል እጅ እንዳለ ነው።

 

ዓሥረኛ

በፍፁም መስለማቸውን የሚያስታውቅ እስከ 40 የእስላም ትውልዳቸውን ቈጥረው፣ በጠርቡሽ ላይ አስጥፈው፣ እኔ ወገናችሁ ነኝና እስላምነቴን ዕወቁ ብለው፣ ለሐረርጌ እስላምና ለሱማሌ ሽልማት ሰጡ። ይህም ያልተሰወረ በግልጥ የሆነ ህዝብ ሁሉ ያየው ነገር ነው።

 

ይህስ የክርስቲያንን ኃይማኖት መካድና ክርስቲያንን መጥላት፣ በእስላም ኃይማኖት ማመን፣ እስላምን መውደድ አይደለምን።

 

ዓሥራ አንደኛ

ሐረርጌ የእስላሙን ቃዲ ጠላና ጠጅ ትጠጣለህ አሉ፤ ስለምን የእስላም መጽሐፍ የማያዘውን ሥራ ትሠራለህ ብለው ከሳሽ ሰው ሳይነሣበት፣ በአደባባይ በግድ ፍረዱ ብለው ክርስቲያኑንም እስላሙንም አስፈርደው አሠሩት። እስላሙስ ይፍረድ፣ ክርስቲያኑን በማያውቀው ሕግ ቀላቅለው በፍርሃት ማስፈረዳቸው የምን ማድረግ ይመስላል።

 

ዓሥራ ሁለተኛ

አሁን ጅጅጋ ከወረዱ የሱማሌውን ውጋዝና ባላገር ሰብስበው፣ ሙሉ የጦር ልብስ ሸልመው፣ የኢትዮጵያን መንግሥት ባለግርማ ሰንደቅ ዓላማችንን፣ እዚህ አዲስ አበባ ለቱርክ መንግሥት ቆንስል የሰጡት አንሶ፣ ዓሥራ ሁለት ሰንደቅ ዓላማ ላይ “ላኢላህ ኢላላህ መሐመድ ረሱል አላህ” የሚል ተጽፎበት፣ ምሣሌ የሚሆን ቀይ ክር ከሰንደቅ ዓላማው ላይ ተንጠልጥሎ፣ ይህንኑ ክር የሚበጥስ ፋስ የያዘ፣ ጠርቡህ ያደረገ የእስላም ሰው ሥዕል ተስሎበት ለሱማሌዎች ሰጥተዋቸው፣ ባደባባይ ይዘውት ወጥተው ፎከሩበት። ይህስ በክርስቲያኑ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የመነሣት ምልክት አይደለምን።

 

ዓሥራ ሦስተኛ

 

የኢትዮጵያ መኳንንትና ህዝብ ወደ ጥፋት መሄዱን እያየና እያወቀ፣ ዝም ብሎ ትዕግሥት ቢያበዛ፣ ፈረንጆች የልጅ ኢያሱን ሥራ ሁሉ ተመልክተው፣ ይህ ነገር ጀሃድ የማሰኘትና የኢትዮጵያን ክርስቲያን አጥፍቶ፣ በመጨረሻው በኛ ላይ የሚከፋ ነገር ለማምጣት ነውና ይህን ነገር ለመንግሥት እናመልክትና ለራሱ ብልሃት ቢያበጅ ያብጅ፣ በተቀረ እኛ የምንሠራውን እናውቃለን ብለው፣ አንድነት ሆነው በግልጥ አስታወቁን። ይህንን ነገር አስቀድመው ለመንግሥት ማስታወቃቸው ብናውቅበትማ ለኛ እጅግ መልካም ነገር ነው። ክፋት አስበው ቢሆን ግን ዝም ብለው ቆይተው ልጅ ኢያሱ አሳባቸውን ከፈጸሙ በኋላ ባገራችን ላይ በክፉ ለመነሣት ይመቻቸው ነበር።

 

ጃንሆይ የመሠረቱትን ውል ጠብቀን ተጠንቅቀን ከኖርን ግን ኢትዮጵያን የሚነካት ሰው የለም። ባንድ በልጅ ኢያሱ ብቻ ውል ማፍረስ ምክንያት፣ የኢትዮጵያን ህዝብ ሳይጠሩ እንዴት ለምለም ሀገራችንን እንዴት እናስወስዳታለን፣ ኃይማኖትስ ሲፈርስ ዝም ብለን ምን እናስተውላለን።

 

አሁን ደግሞ ጀሃድ እያሉ የጃንሆይን አሽከሮችና የክርስቲያንን ደም ያፈሰሱትን እስላሞች ሼኸ ጦልሃን፣ ያሰን አንጃንም ልጅ፣ ያባ ጅፋርን ልጅ፣ ደግሞ ሌሎችን እንደነዚህ ያሉትን ይዘው እዋናው እስላም ሀገር ጅጅጋ ተቀምጠው፣ ውጋዴን ውስጥ ሽፍታ ሆኖ እያስቸገረ ከሚኖረው፣ ጅጅጋም ድረስ መጥቶ ክርስቲያንን ሲፈጅ ከነበረው ከከቢራ ጋር እየተላላኩ ብዙ ጠበንጃና ጥይት መትረየስም ሰደዱለት። ደግሞም የእንግሊዝንና የኢጣልያንን ዜጎች ጠርተው እየሰበሰቡ፣ ጀሃድ እንበል እያሉ መከረዋል።

 

ጅጅጋ ወርደው ይህን መምከራቸው የእስላም መሃከለኛ ሀገር ነውና ጀሃድ የሚሉበት ጊዜ ኃይላቸው እንዲበረታ ነው።

 

እርሳቸው ግን እስላም ያረደውን እየበሉ፣ እኔ ይህን ማድረጌ ሀገር ለማስፋፋትና ሰው ለማባበል ነው እንጂ ስለሌላ ነገር አይደለም እያሉ የሚያታልሉት፣ ይህ ሱማሌና እስላም ከዚህም በፊት አሁንም ለጃንሆይ የገበረ የቀቀለ ዜጋቸው ነው። ልጅ ኢያሱ ግን ከእስላም ጋር አብረው መብላታቸው፣ የራሳቸውን እስልምና ለማጽናት ነው እንጂ በማባበላቸውስ ፊት ከቀናው ከገበረው ሀገር በቀር ሌላ አንድ ስንዝር መሬት የጨመሩት የለም።

 

ይህንም እስልምናቸውን ለማጽናት እንዳደደረጉት በጣም የሚገልጥና የሚያስረዳ፣ ከሁሉ በፊት አስቀድመው የእስልምና ምልክትን ሲያሳዩ፣ ሐነፊ ለሚባል እስላም ሚስት ስምዋ ነፍሳት ለተባለች ልጄን አንቺ አሳድጊልኝ ብለው ልጃቸውን ሰጡዋት።

 

ልጅ ኢያሱ ያደረጉት ይህ ነገር ምንድር ነው፣ እንዴት የንጉሠ ነገሥት ክርስቲያን ልጅ የእስላም ምግብ እየተመገበች፣ የእስላም ልማድ እየተማረች፣ በእስላሞች አፍ የእስላም ኃይማኖት ሲከበርና ሲመሠገን፣ የክርስቲያን ኃይማኖት ሲሰደብና ሲነቀፍ ሁልጊዜ ጥዋት ማታ እየሰማች፣ ከእስላሞች ጋር አድጋ፣ የክርስቲያንን ኃይማኖት መጻሕፍትን ሳትሰማ፣ በመስማትም ክፉን ከመልካም ለይታ ሳታውቅ፣ ሥጋ ወደሙን ሳትቀበል፣ ከእስላም ጋር እንዲህ ሆና አድጋ በኋላ እንዴት ክርስቲያን ልትሆን ትችላለች ብለን ልባችንን እያመመን ይህ ነገር ምንድር ነው? የምን ምልክት ነው እያልን በሆዳችን ሲከፋን፣ ከዚህ ጋር ደግሞ በጣም ይድነቃችሁና ይውጣላችሁ ብለው፣ ምንስ የፊቱም ሽሽግ ባይሆን በግልጥ ሐረርጌ ከእስላም ሀገር አውርደው፣ ከፉቅራ ቤት የእስላም ኃይማኖት እንድታጠና፣ ቁርዓንን አስተምራት ብለው አኖሩዋት። እነሆ ሌላው ሁሉ ቀርቶ ይህ የተገለጠ ነገር ነውና አስተዋይ ልቡና፣ መርማሪ ሕሊና ላለው ይህ ብርቱ የእስልምና ምልክት እንደ ሆነ ፈጽሞ ይታያል።

 

ዳግመኛም የእስልምና ምልክትን ሲያሳዩ ልጅ ኢያሱ፣ የደጃዝማች ጆቴን ልጅ አስካለ ማርያም የምትባለውን ዳዊት ደጋሚቱን ሐረርጌ ወስደው፣ ስምዋን ለውጠው፣ በእስላሞች ሴቶች ስም ሞሚና አሉዋት። ምቅና የሚባል የተለየ የእስላም ሴቶች መሸፈኛ አለበሷት። ይህም ወርቁን በነኀስ፣ ንጽሑን በርኩስ እንደ መለወጥ ያለ ነውና ክፉ ምልክት ነው። እርሳቸውም የእስላም ልብስ ለብሰው፣ እመስጊድ ገብተው፣ መስገዳቸው በከበረው በኢትዮጵያ መንግሥት ሰንደቅ ዓላማ የመስቀል ምልክት ባለበትና “ሞዓ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ” ተብሎ በሚጻፍበት ላይ የጨረቃ ግማሽ ሥዕልና የቱርክ እስላም መንግሥት ምልክት “ላኢላህ ኢላላህ መሐመድ ረሱል አላህ” ተብሎ ሲያጽፉበት ይህ የእስልምና ክፉ ምልክት አይደለምን።

 

ልጅ ኢያሱ ይህን ሁሉ ጥፋት የሚሠሩት፣ ልብ ነሥቷቸው አዕምሮ ጐድሏቸው አይደለም። የሰውን ምክር ባለመስማት፣ ምን አለብኝ በማለት ወደው፣ ለምደው ያደረጉት ሥራ ነው እንጂ፤ አብደው እንደ ናቡከደነፆር ልብ አጥተው፣ የልብ ማጣት ቢሆንስ ያሳዝነን፣ ያስለቅሰን ነበር እንጂ ባልፈረድንባቸውም ነበር። ይልቁንም አስረን በስውር ቦታ አኑረን፣ ስለጤናቸው መድኃኒት እንፈልግላቸው ብዙም እንደክምላቸው ዘንድ ይገባን ነበረ። ነገር ግን አበዱ ብሎ የማያስሩዋቸው፣ ጨመቱ ብሎ የማያከብሩዋቸው ሆነው አጉል ሥራ እየሠሩ፣ እዚህ ሁሉ ነገር በገዛ እጃቸው ደረሱ። እኛንም በማይገባ ክፉ ሥራቸው ለኹከት አንቀሳቀሱን።

 

አሁንም ጃንሆይ ያሽከሮቻቸውን ደም አፍስሰው ያቀኑት ሀገር፣ የእስላም ሰንደቅ ዓላማ ሲሰቀልበት፣ ክርስቲያኖችም የሠሩዋቸው አብያተክርስቲያናት የእስላም መስገጃ ሊሆኑ ነውና ኃይማኖት መፍረሱን፣ መንግሥት መጥፋቱን አስበን፣ እንቻልህ፣ እንታገሥህ ብንለው የማይቻለን ሆነ።

 

ስለዚህ ከአውሮጳ በፊት በወንጌል ተሰብኮ፣ በክርስትና ፀንቶ፣ እስካሁን ድረስ የኖረውን መንግሥት፣ አሁን የእስላሞች ዋና ገዥ የቱርክ መንግሥት ሊወድቅ በደረሰበት ሰዓት ወደ እስላምነት ሲመለስና የክርስቲያን ደም ብዙ ጊዜ ከእስላም ጋር በመዋጋት እንደ ጎርፍ የፈሰሰበት ሀገር ኢትዮጵያ፣ የእስላም ሰንደቅ ዓላማ ሲሰቀልበት ከማየት አስቀድሞ የኃይማኖት አምላክ ይርዳን ብለን ለኃይማኖትና ለመንግሥት ደማችንን ለማፍሰስ ቆርጠናል።

 

እንግዲህ መንግሥት ያለ ኃይማኖት፣ ኃይማኖትም ያለ መንግሥት እንዳይፀና የታወቀ ነውና ለዚሁም ኃይማኖትና መንግሥት፣ ጃንሆይ አልጋ ላይ ከዋሉ ጀምረው እስካሁን የደከሙበት አባታችን ነዎ። ኃይማኖት ይጥና፣ መንግሥታችን ይርጋ ያሉ እንደሆነ የማርቆስ ኃይማኖት፣ አምላክ ለዳዊት ዕርዳታ ያወረደ፣ መንፈስ ቅዱስ አይለያችሁ ብለው አባታችን መስቀልዎን እፊታችን ይዘው ኃይማኖታችንን ያጥኑልን፣ በፀሎትዎም ይባርኩን።

 

እስላም ጀሃድ ካለ በኋላ የሰደድ (የቋያ) እሳት ከተቃጠለ፣ ለማጥፋት እንዲያስቸግር እንደዚሁ ያስቸግራልና በቶሎ ካልነቃንበትና ካላጠፋነው፣ ስር ከሰደደ በኋላ ይልቁንም የክርስቲያን ደም ብዙ ይፈስብናል።

 

ይህም የተነሣንበት ሁሉ በሹመት፣ በሽረት፣ በማግኘት፣ በማጣት አይደለም። ለኃይማኖታችንና ለመንግሥታችን፣ ለሀገራችንና ለህዝባችንም ስንል ነው እንጂ። ምክንያቱ ይህ እንደሆነ፣ ሌላ ነገር እንዳይደለ የኢትዮጵያ አምላክ ይመስክርብን።

 

መስከረም 17 ቀን 1909 ዓ.ም. አዲስ አበባ ከተማ ተጻፈ

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ