ዮፍታሔ

Belay Zeleke
በላይ ዘለቀ

የዘንድሮው የአርበኞች ቀን የስመ ጥሩው አርበኛ በላይ ዘለቀ ስም ጎልቶ እይታሰበ የተከበረበት መሆኑ ተጠቅሷል - ይልቁንም በአማራ ክልል።

ይህንን ተከትሎ ደግሞ ዶክተር ሽብሩ ተድላ “ከጉሬዛ ማርያም እስከ አዲስ አበባ የሕይወት ጉዞዬ እና ትዝታዬ” በሚል ርዕስ ያሳተሙትን መጽሐፍ በመጥቀስ ከዚህ በታች የሚታየው የበላይ ዘለቀ ፎቶ የርሱ እንዳልሆነ የሚገልጹ ጽሑፎች ወጥተው እያነበብን ነው።

ይህ ፎቶ የበላይ ዘለቀ ያለመሆኑን ለማስረዳት የቀረቡት ማስረጃዎች ደግሞ በላይ ዘለቀ ጽጉሩን አጎፍሮ እንደማያውቅ የሚገልጹ ናቸው። በማስረጃነት በላይ ዘለቀ ያስቀድስ በነበረበት ቤተክርስቲያን ያገለግሉ የነበሩ ዲያቆናት፣ በላይ ዘለቀ የአባቱን ተዝካር ሲያወጣ አንድ ቀን ያዩት ሰውና የአንድ ሌላም ደጃዝማች ምስክርነት ተጠቅሰዋል።

ነገር ግን ይህ በዶ/ር ሽብሩ መጽሐፍ የተጠቀሰው መረጃ ሚዛን የሚደፋ መሆኑን ለማረጋገጥ በሌሎች ሰዎች የቀረቡትን ምስክርነቶች ማቅረብም ይጠቅማል።

በመጀመሪያ ስብሀት ገ/እግዚአብሔር በየካቲት መጽሔት 3ኛ አመት ቁጥር 7 ሀምሌ 1972 ዓ.ም. ያወጣውን ጽሑፍ እንመልከት። ስብሐት ገ/እግዚአብሔር ይህን ጽሑፍ ያወጣው ለበላይ ዘለቀ በጣም ቅርብ የነበሩትንና፣ በአርበኝነት ዘመኑም ያልተለዩትን የሚከተሉትን ሰዎች ምስክርነት ቃል በቃል (የአካባቢው መለያ ከሆነው የአነጋገር ዘይቤ ጋር) በማስፈር ነው።

ሰዎቹም፦

  1. ፊታውራሪ ተሻለ ዓለሙ - ከበላይ ዘለቀ ጋር የወንድማማች ልጆች የሆኑ፣ ከበላይ ዘለቀ ጋር አርበኝነቱን ከተቀላቀሉ የመጀመሪያ ሃምሳው የበላይ ዘለቀ ቤተሰቦች አንዱና በላይ ዘለቀን (በእስር ቤት ካልሆነ በቀር) እስከ ዕለተ ሞቱ ያልተለዩት፣ በዕድሜ በላይ ዘለቀን 4 ዓመት የሚበልጡት መሆናቸውን የገለጹና በቃለ ምልልሱ ጊዜ የ74 ዓመት አዛውንት።
  1. ፊታውራሪ ተሰማ ላቀው - የበላይ ዘለቀ የአባቱ ትንሽ ወንድምና በቃለምልልሱ ጊዜ 67 ዓመታቸው የነበረ።
  1. ፊታውራሪ ቀለመወርቅ መዝጊያ - የበላይ ዘለቀ ዋና ጸሐፊ የነበሩና በቃለምልልሱ ጊዜ ዕድሜያቸው 62 ዓመት የነበረ።

እነዚህ ሦስቱም አዛውንት ስለ በላይ ዘለቀ አርበኝነት፣ ባሕሪ፣ ስለጠላቶቹ፣ ስለእሥሩ፣ ፍርዱና አገዳደሉ ልቅም አድርገው ሁሉንም ገልጸውታል።

ከዚህ ሁሉ በላይ ግን ለተነሣሁበት ርዕስ ጠቃሚ የሆነው ፊታውራሪ ተሻለ ዓለሙ የበላይ ዘለቀን መልክ የገለጹበት መንገድ ስለሆነ ወደዚያ እንለፍ። ፊታውራሪ ተሻለ የበላይ ዘለቀን ገጽታና አካላዊ መለያዎቹን ሲገልጹ እንዲህ ይላሉ፦

"አፍንጫው ሰተት ብሎ ወርዶ ቅጠሉ ነፋ ነፋ ይላል። ከንፈሩ ከበድ ይላል። ጠጉሩ ክርክም ጎፈሬ ጺሙ ሙሉ ለስላሳ። ረጅም ጣቱ መልካም ወተት የተነከረ ነው የሚመስለው ጣቱ። እግረ ቀጭን።"

እውነቱ ይህ ከሆነ ዘንዳ በላይ ዘለቀ ጎፈሬ ያልነበረው መሆኑን በመግለጽ ይህንን ፎቶግራፍ የርሱ አይደለም ከማለት በፊት ዶ/ር ሽብሩ ተድላ ሌሎችን መረጃዎች አገላብጠው ነበርን? በማለት መጠየቅ እፈልጋለሁ።

በፊታውራሪ ተሻለ ገለጻ መሠረት የበላይ ዘለቀን “ክርክም ጎፈሬ” እንጂ በዶ/ር ሽብሩ መጽሐፍ ተጠቅሷል የተባለውን “ላሽ ያስቸግረው ስለነበረ ሁልጊዜ ፀጉሩን ይላጭ” የነበረውን በላይ አንመለከትም። ይህም ብቻ አይደለም በፊታውራሪ ተሻለ ዓለሙ የተገለጹትን የአፍንጫ፣ የከንፈርና፣ የጸጉር አካላዊ መለያዎች ላነበበ ሰው ይህ ፎቶግራፍ የበላይ ያለመሆኑን እንዲጠራጠር ከሚያደርገው ይልቅ ፊታውራሪ ተሻለ በቃል የገለጹትን የሚያረጋግጥና ፎቶውን እንዲቀበል የሚያደርግ ነው።

የመረጃዎቹ ምንጭ መሆናቸው የተጠቀሱት ሰዎች ለበላይ ዘለቀ የነበራቸው ቅርበትና የእውቀት ደረጃ ደግሞ በዶ/ር ሽብሩ በመረጃ ምንጭነት ተጠቅሰዋል ከተባሉት ሰዎች ጋር ተነጻጽረው መታየት ይኖርባቸዋል። ጽሑፎቹ የቀረቡበት ዘመንም ግምት ውስጥ መግባት ይኖርበታል።

ሌላም አለ። ይህም በ2004 ዓ.ም. የበላይ ዘለቀ መቶኛ ዓመት በአ.አ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ምርምር ተቋም አማካኝነት በተከበረበት ጊዜ ከቤተሰቦቹ የተገኘ ፎቶ መሆኑ ተገልጾ በማኅበራዊ መገናኛዎች ሲዘዋወር የነበረ የበላይ ዘለቀ ፎቶግራፍ ነው።

Belay Zeleke
በላይ ዘለቀ በአንድ ዛፍ ሥር ሆኖ አርበኞችን በሩቅ ሲያስተኩስ

በዚህ ፎቶግራፍ በላይ ዘለቀ በአንድ ዛፍ ሥር ሆኖ አርበኞችን በሩቅ ሲያስተኩስ ይታያል። ይህ ፎቶግራፍ ፊታውራሪ ተሻለ በቃል የገለጹትን የበላይ ዘለቀ ገጽታ (በተለይም ጎፈሬ) የሚመጥን ከመሆኑም በላይ ከሌላው የበላይ ዘለቀ ምስል ጋር የሚመሳሰል መሆኑ አያሻማም። በዚህ ፎቶግራፍ ላይ በላይ ዘለቀ በእጁ ወደፊት ሲጠቁም ስለሚታይ የተሻለ ጥራት ያለውን የፎቶውን ኮፒ ማግኘት ቢቻል ፊታውራሪ ተሻለ ስለ በላይ ዘለቀ እጅ የጠቀሱትንም ለማረጋገጥ ይቻል ይሆናል የሚል ተስፋ አለኝ።

አንድ ልጨምር። ከዚህ በታች በእጅ ተሥሎ የሚታየው ምስል የሚገኘው በበላይ ዘለቀ ትውልድ ቦታ አካባቢ በእነሴ ወረዳ በምትገኘው የቅድስት ድንግል ማርያም ቤ/ክርስቲያን ውስጥ ነው። በሥዕሉ ላይ በላይ ዘለቀ (ከመካከል) ፊታውራሪ ተሻለ ዓለሙ ከጠቀሱት “ክርክም ጎፈሬ” እና “ሙሉ ለስላሳ ጺም” ጋር በግልጽ ይታያል (ጺሙ ከሌሎች በሥዕሉ ላይ ከሚታዩት ሰዎች የተለየ መሆኑን ልብ ማለት ያስፈልጋል)። ከዚህም በተጨማሪ በሥዕሉ ላይ የሚታየው በላይ ዘለቀ በፎቶግራፉ ከሚታየው ጋር ተመሳሳይ ነው። ሥዕሉ የተሣለበት ጊዜም 1934 ዓ.ም. እንደሆነ ሰፍሯል። ይህ ወቅት ጣሊያን ከኢትዮጵያ ከተባረረ በኋላ በላይ ዘለቀ በደጃዝማችነት ማዕረግ ቢቸና ላይ በተሾመበት አካባቢና ከመሞቱ ደግሞ አራት ዓመታት በፊት መሆኑ ነው። ይህ ሥዕል የተሣለበት ምክንያትም “የታመኑ አርበኛ ለእመቤታችን የ ፯ ብር ቀለም መጋረጃ ስለሰጡን” ስለሚል በላይ ዘለቀ ለቤተክርስቲያኑ ባስገባው መባ መነሻ መሆኑን የሚያመለክት ነው። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሥርዓት መሠረት በዚህ መልክ ለመታሲቢያነት የሚሣሉ ሥዕሎች በምን ዓይነት ጥንቃቄ እንደሚዘጋጁ ለሚረዳ ሁሉ የዚህ ሥዕል ዋጋ ግልጽ ይሆንለታል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።

የበላይ ዘለቀ በእጅ የተሳለ ምስል፣ Belay Zeleke
በበላይ ዘለቀ ትውልድ ቦታ አካባቢ በእነሴ ወረዳ በምትገኘው የቅድስት ድንግል ማርያም ቤ/ክርስቲያን ውስጥ የተሳለው የበላይ ዘለቅ ምስል።

በመጨረሻም የበላይ ዘለቀ መቶኛ ዓመት በአ.አ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ምርምር ተቋም ሲከበር የበላይ ዘለቀ ቤተሰቦች መገኘታቸውና የበላይ ዘለቀን ፋውንዴሽን ለማቋቋምም የነበራቸውን ዓላማ ሲገልጹ ስለሚታይ እነዚህ የበላይ ዘለቀ ቤተሰቦች በጉዳዩ ላይ ያላቸውን ሐሳብ ያካፍላሉ ብዬ ተስፋ በማድረግ ጽሑፌን እቋጫለሁ።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ