እርካብና መንበር

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ዲራአዝ በሚል የብዕር ስም የጻፉት “ሰተቴ” የተሰኘው 3ኛው መጽሐፋቸው ሲሆን፣ አራተኛው “እርካብና መንበር” ይሰኛል። አምስተኛውና “መደመር” የተሰኘው መጽሐፋቸው በቅርቡ ገበያ ላይ እንደሚውል ተነግሯል።

ገ/ክርስቶስ ዓባይ

“እርካብና መንበር” በ'ዲራአዝ' የብዕር ስም የተጻፈች እጥር ምጥን ያለች መጽሐፍ ናት። መጽሐፏ እጅግ በሠፊው የተወራላት በመሆኗ በእጄ እንደገባች በጥንቃቄ እና በጥሞና ማንበቤን ቀጠልሁ። ጸሐፊው ያላቸውን ራዕይና የሞራል ጥንካሬ በሚገባ አይቼበታለሁ። ከልብ በመነጨ ስሜትና ጉጉትም እንደተጻፈ ለመገንዘብ ችያለሁ። ምናልባት ጸሐፊው የአስተዳደርን ጥበብ ለማወቅ፤ አንድም በተወሰነ ርዕስ ላይ በአተኮረ ጥናት መጻሕፍትን ሲበረብሩ፤ አልያም ስለአመራር የተለያዩ ሥልጠናዎችን የመካፈል ዕድል ያጋጠማቸው እንደነበር መገመት አይከብድም።

ምክንያቱም አንዳንድ አንቀጾች፤ ተደጋግመው ቢነበቡም እንኳ ለመረዳት የሚቸግሩ ከመሆናቸውም በላይ የአማርኛ ሰዋስው የዓረፍተ ነገር አጠቃቀምን የተከተሉ ባለመሆኑ ከሦስት አስከ አራት ዓረፍተ ነገር መሆን የሚገባው ሀተታ፤ በአንድ ዓረፍተ ነገር ብቻ ተጠቃሏል። ለዚህ ዋናው ምክንያት አንዳንድ ሐሳቦች በምንም ዐይነት ሳይሰለቁና ሳይደቁ በቀጥታ ትርጉም (literary translation) ብቻ የተስተናገዱ እንደሆኑ በግልጽ መረዳት ይቻላል። ለዚህ እሳቤ ትክክለኛነት ብቁ ተርጓሚ (Professional Translator) የሆነ ሁሉ የሚገነዘበው መሆኑን ለመጠቆም እወዳለሁ። በተጨማሪም በኒኮሎ ማኪያቬሊ የተጻፈው እርሳቸው መስፍኑ ብለው የሰየሙትን የ‘ልዑሉን’ በ(The Prince) የተባለውን መጽሐፍ፤ ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት ለማንበብ የቻልሁ ሲሆን፣ መጽሐፉ አሁንም በእጄ ይገኛል።

ከዚህ ውጭ ሥልጣንና ኃይል የሚለው ትንተና በአብዛኛው የመሪነት ብቃትን በተመለከተ የተለያዩ የፖለቲካ ምሁራን አስተያየትን በቀጥታ የሚያስተናግድ ሆኖ ይታያል። ይሁን እንጂ ጸሐፊው ይህንን ውጣ ውረድና መሰናክል ሁሉ በማለፍ ሐሳባቸውን ለማስተላለፍና ግባቸውን ለማሳካት በመብቃታቸው አሁንም ቢሆን አድናቆቴ ወሰን የለውም።

ለማንኛውም እስኪ በመጽሐፉ ውስጥ ከተጠቀሱት አንዳንድ አከራካሪ ነጥቦችን እየነቀስን እንመልከት። በትምህርተ ጥቅስ በጉልህ የቀረቡት ሐሳቦች ከመጽሐፉ የተጠቀሱት ሀተታዎች ሲሆኑ ሁሉም፤ አንባቢያን ስለመጽሐፉ ይዘት በቂ ግንዛቤ ያገኙ ዘንድ እንደወረደ በቀጥታ የተገለበጠ መሆኑን አሳስባለሁ።

ጸሐፊው መስፍኑ (Duke) እያሉ የተረጎሙት ስለ ልዑሉ መንታ ባህርይ በገጽ 36 ሁለተኛው አንቀጽ ላይ እንዲህ በማለት ይገልጹታል። “በመልካሙ ጊዜ ሕዝብን በፍቅር መያዝ አስፈላጊ ነው። ፍላጎታቸውን በመፈጸም የልብ ትርታቸውን ማዳማጥ፤ ደስ የሚያሰኛቸውን ነገር በማድረግ በሕዝብ ልብ ውስጥ ተደላድሎ መቀመጥ ይቻላል። ... ታዲያ አመጽና የመክዳት ምልክት የታየ ጊዜ፤ በሁለተኛውና በተለበጠው ማንነት መገለጥ ተገቢ ይሆናል። ተመጣጣኝ የሆነ ቅጣትን ተግባራዊ በማድረግ በፍቅር ጊዜ መልአክ በአመጽ ጊዜ ግን ሰይጣን ሊሆን እንደሚችል ማሳወቅ አለበት።”

በገጽ 37 አራተኛው አንቀጽ ላይ፣ ተቀናቃኞችን በሐሳብ መርታት እንደሚቻል ገልጸው ነገር ግን አንዳንዶቹ በመርታትም ሆነ በመረታት እንደማያምኑ ከገለጹ በኋላ ለእንደዚህ ዐይነቶቹ ተቀናቃኞች ሌላ ስትራተጂ መቀየስ እንደሚያስፈልግ ይጠቁማቅሉ፤ (እዚህ ላይ ማየት ያለብን እራሳቸውም በመረታት እንዳማያምኑ ልብ ይሏል) ።

በገጽ 38 አንደኛው አንቀጽ ላይ፣ “እንደውሻ በመጮህ ማምለጫን ማመቻቸት ዘላቂ መፍትሔ ባይሆንም ለጊዜው ይጠቅማል። ምክንያቱም እንዳይመለስ ሆኖ ያልተሸኘ ጠላት ጊዜ ጠብቆ ዳግም ለማጥቃት እንደሚመለስ ጥርጥር የለውም። ታዲያ ጊዜው ሲደርስ ልክ እንደ ነብር ኮቴን ሳያሰሙ ከጀርባ ቀብ ማድረግና ህልሙን በአንድ ጀንበር ማምከን መረሳት የለበትም። ሰዎች ራስ ወዳድ ናቸው፤ በጥቅም ሂድባቸው የሚፈልጉትን ነገር እያሳየህ ወደምትፈልገው ስፍራ ውሰዳቸውና ጣላቸው። ከዚያም ‘በሬ ሆይ! ሳሩን አይተህ ገደሉን ሳታይ’ የሚለውን ተረት ተርትባቸው።”

በገጽ 39 የመጀመሪያው አንቀጽ ላይ፣ “... ዕብሪተኛ ከመሆን ይልቅ ለሌሎች በጎ በመሆን የደነደነ ልብ ያላቸውን ተጠራጣሪዎች ለራስ ፈቃድ ማስገዛት ይቻላል። የበጎነትና ታማኝነት ስብዕና የተላበሱ ሰዎችን ለማዘናጋት፤ በቀላሉ ለመሸንገልና ለመደለል ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል።”

በገጽ 39 በሁለተኛው አንቀጽ ደግሞ፤ “የበላይነት ከምናረጋግጥባቸው መንገዶች መካከል አንዱና ዋነኛው ፕሬስ ሲሆን በቤተ እምነቶች፣ በቤተ መጻሕፍት፣ በትምህርት ቤቶች እና በማኅበራት ላይ አተኩሮ መሥራትም ሳይቀር ተጽዕኖ ማሳደሪያ ለዘብተኛ ኃይል ተደርገው ይወሰዳሉ። … በማንኛውም ጊዜ አብሮን የሚሆን አካል አለን፣ የሚለው ፅኑ እምነታቸውን ለማግኘትም ያበቃል። በተለይም ወዳጅና ጠላት የሚለየው በችግር ቀን ነው፣ ብሎ የሚያምነው ሕዝባችን ውስጥ ከነዕድፍ ተደላድሎ ለመቀመጥ በችግር ጊዜ መድረስን የመሰለ ጥሩ አጋጣሚ አይገኝም።”

እነዚህ ከላይ የተዘረዘሩት ሁሉም አገላለጾች፤ በእውነትና በሐቅ ላይ የተመሠረቱ የሕዝብ ወገንተኝነት መገለጫዎች ሳይሆኑ፤ ሕዝብን በማታለል በሥልጣን ላይ እንዴት መቆየት እንደሚቻል የሚጠቁም፤ መሠሪና ከሰብአዊነት ውጭ የሆነ የሠይጣን ተግባር መሆኑን ማጤን ያስፈልጋል። ዕድፍ በማለት የጠቀሱት ከሕግ ውጭ የተሠራ አረመኔያዊ ተግባር ማለታቸው እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል። በተለይ እንደኢትዮጵያ ያለች ፈሪሃ እግዚአብሔር ላላት አገር ፈጽሞ የሚመጥን አለመሆኑን መረዳት ይቻላል።

በገጽ 45 ሁለተኛ አንቀጽ ላይ እጅግ አደገኛ የሆነ አስተሳሰብ ሰፍሮ ይገኛል።

“ምንም እንኳን ሕገ መንግሥት፣ ሃይማኖትና መንግሥት የተለያዩ መሆናቸውን በግልጽ ቢያውጅም፤ ሕግ አውጪ፣ ሕግ ተርጓሚ እና ሕግ አስፈጻሚ የተለያዩና አንዱ ከአንዱ ነጻ ናቸው፤ ቢልም ... በጣም ዲሞክራሲያዊ ነኝ ቢልም፤ መንግሥትም ሆነ ሌላው አካል ሁሉም አካላት ከሕግ በታች ናቸው፤ ቢልም ... በቡድን ተደራጅቶ ፖለቲካዊ አስተሳሰባቸውን ያለምንም ተፅዕኖ የማራመድ መብት አላቸው፣ ብሎ ቢያስብም፤ እውነታው ግን የተገላቢጦሹ ሆኖ ይታያል። የእምነት ስፍራውም ሆነ የሕግ አስከባሪ አካላት መንግሥቶቼ ለሚሏቸው ኃይሎች የተለጎሙ ፈረሶች ሆነው ያገለግላሉ።”

አንባቢያን ሆይ ልብ በሉ! ይህ አገላለጽ ማንነታቸውን በግልጽ የምናይበትና እኒህ ሰው በዲሞክራሲ የማያምኑና ፍጹም አምባገነን መሆናቸውን የሚመሰክር አንቀጽ ሆኖ ይገኛል።

በገጽ 59 አንቀጽ ሦስት ላይ ደግሞ አለቃቸው የነበሩት ሟቹ መለስ ዜናዊ፤ በዳግማዊ አፄ ምኒልክና በቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ላይ የነበራቸውን ጥላቻ እንዴት አድርገው እንደገለጹት በትዝብት የምናስታውሰው ሲሆን፤ እኒህ ደግሞ ሆነ ብለው በአፄ ቴዎድሮስ ላይ ያላቸውን የጥላቻ ጥግ እንዲህ ሲሉ ገልጸውታል።

“በእርግጥ የዛሬዎቹ ከሊፋዎች እንደሚፈጽሙት ጭካኔ ሁሉ አፄ ቴዎድሮስም ከጠላት ጋር ያበሩ ዜጎች ምርኮኞቹን አርደዋል፣ በቢላ። የሰው ልጅን በመድፍ አፍ አድርገው ተኩሰዋል። ጆሮ ቆርጠዋል። ምላስ እጅና እግር በተመሳሳይ ቆርጠዋል። ቤት ዘግተው አቃጥለዋል። ገደል ጨምረዋል። ምናልባትም የአፄ ቴዎድሮስን ጭካኔ ከዛሬዎቹ ከሊፋዎች የሚለየውና ከባድም የሚያደርገው አፄ ቴዎድሮስ ሙሉ ቀን ሲገድሉ ውለው ቀኑ ስላልበቃቸው ቆጥረው አሳድረው፣ ሲነጋ ቆጥረው መግደላቸው ነው።” በማለት አስፍረዋል።

በገጽ 62 አንቀጽ 2 ላይ ደግሞ፤

“የሸዋውን ንጉሥ ሲንቁ ሲንቁ
የትግሬውን ንጉሥ ሲንቁ ሲንቁ
የጎጃሙን ንጉሥ ሲንቁ ሲንቁ
ወንድ ያለራስዎ ገድለውም አያውቁ!” እንዲል ባለቅኔ የራሳቸውን ሽጉጥ ጠጥተው (የታሪክ ክርክሩ እንዳለ ሆኖ) ሕይወታቸው ሊያልፍ ችሏል።”

በማለት ገልጸውታል። ይህም የንጉሡን የመጨረሻ የጀግንነት ቆራጥ ውሳኔ እውነት እንዳልሆነና በሌላ ኃይል እንደ ተገደሉ የሚያስመስል የታሪክ መዛባት ለመፈጸም ሞክረዋል።

በገጽ 64 በሦስተኛው አንቀጽ ላይ በአገሪቱ ባህል ሠርጾ የሚገኘውን የአንበሳነት (የጀግንነት) ገጸ ባህርይ ትክክል እንዳልሆነ አድርገው ከተቹ በኋላ ጀብዳዊ ጭካኔን ሲገልጹ የሚከተለውን አስፍረዋል።

“አንበሳ ከደከመ አይገዛም! ከደከምክ አትኖርም ትገደላለህ። በገዛ ወገንህ። ስለዚህ ላንተ አሳሳቢና ዘወትር አስፈላጊው ጉዳይ ኃይልን ማጠናከር ነው። መፈራትን መገንባት ነው። ከነዘርህ … ከነዘርማንዘርህ። አስከብሮ የሚያኖርህ በእንዲህ ዐይነቱ ምድር ፍቅር አይደለም - ጉልበት እንጂ። ለዚህ ደግሞ እንደ አንበሳ ሁሉ ማስፈራሪያ እንጂ ፍቅር አይሰጠውም - ያን ጉልበት በዲፕሎማሲ አስማምቶ ለመምራት አያውለውም ተቀናቃኜ ያለውን ጀርባ ለማድቀቅ እንጂ።”

የዚህ መልዕክት ሁሌም በኃይል እየረገጡና እየጨቆኑ ከመግዛት ውጭ ሌላ አማራጭ እንደሌለ አድርገው ይሰብካሉ። ነገር ግን ተቋማዊ የሕግ አሠራር ከተገነባ ማንም ሰው ከተራ ዜጋ እስከ ከፍተኛው ባለሥልጣን ድረስ የሕግ ከለላ በማግኘት በነፃነት መኖር እንደሚችሉ አያምኑም። ምክንያቱም የሕግ የበላይነትን አምባገነኖች አይቀበሉም። እራሳቸውን ከሕግ በላይ አድርገው ይቆጥራሉና! እንዲህ ያለው ፍርሃት ከየት መነጨ ብለን ብንጠይቅ ዲሞክራሲያዊ መርህን መሠረት በማድረግ በሚሰጠው የሕዝብ ውሳኔ ሥልጣንን ለመልቀቅ ፈቃደኛ ሆኖ አለመገኘትን ያመለክታል።

በዚሁ በገጽ 64 አራተኛው አንቀጽ ኮሎኔል መንግሥቱን እንዲህ ሲሉ ይነቅፏቸዋል።

“ኮሎኔሉም ጀብዳዊ ጨካኝ ናቸውና ሕዝቡ ይልስ ይቀምሰው አጥቶ ሲረግፍ እሳቸውም እንደ ኃይለ ሥላሴ ከደሃ ዜጋቸው አፍ ቀምተው ሠራዊታቸውን ቀልበውበታል። የጓሮ አትክልት መኮትኮቻና አፈር መዛቂያ የምታመርትበት የረባ የጎጆ ኢንዱስትሪ የሌላትን አገር የታላላቅ ወታደራዊ ኢንዱስትሪ መናኸሪያ ለማድረግ ጋፋት ላይ ጠመንጃ ማምረቻ ፈብሪካ አቋቁመዋል። ሆርማት ላይ ሞርታርና አዳፍኔ ማምረቻ ፋብሪካ ተክለዋል። ዲካ ላይ ፈንጂ ባሩድ ለማውጣት አስቆፍረዋል። በጦር ባይሸነፉ ኖሮ ሕዝቡ በረሃብ እየረገፈ እሳቸው እንደ ዘመናችን ኪም ጆንግ ኢል (ኪም ጆንግ ኡን ለማለት ይሆናል) ኢትዮጵያን ኒኩሌር ለማስታጠቅ የማይመለሱ ቆፍጣና ወታደር ነበሩ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም።”

‘እንትን ተገልቦ እራሥ ተከናንቦ’ እንዲሉ፤ ጸሐፊው የኢትዮጵያን መሠረታዊ ጠላቶች በሚገባ እንዳልተረዱ ያሳብቃል። ከግብጽ ጀምሮ እስከ ኦቶማን ቱርክ፣ እንግሊዝና ሶማሌን ጨምሮ ሌሎችም የዓረብ አገሮች ለኢትዮጵያ ያላቸው አመለካከት ላለፉት ብዙ ምዕተ ዓመታት በቅናት፣ በምቀኝነትና በተንኮል ላይ የተጠነጠነ ሆኖ እናገኘዋለን። በዚህም ምክንያት የዓለም የሥልጣኔ ፋና ወጊ የነበረችው አገራችን በየጊዜው በሚደርስባት ትንኮሳ ብዙውን ጊዜ ያሳለፈችው ዳር ድንበሯን ለማስከበር እንደነበረ ታሪክ ያስተምረናል።

ከዚህም የተነሳ ከውጭ የምታስገባው የጦር መሣሪያ የአገሪቱን ሀብት በየጊዜው ሲያሟጥጥ እንደቆየ የሚዘነጋ አይደለም። በተጨማሪም የጦር መሣሪያዎች በዐይነትና በጥራት በየጊዜው እየተለወጡ ስለሚመጡ ያንን የዕድገት ለውጥ ሚዛናዊ አድርጎ ለመራመድ የግድ ኢትዮጵያ የራሴ የምትለው ፋብሪካ ሊኖራት የሚገባ አንገብጋቢ ጥያቄ ስለነበር (አሁንም ነው)፤ በቅድሚያ ይህንን የተረዱት ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ሲሆኑ፣ የተወሰነ ሙከራ አድርገው እንደነበር ታሪክ ይነግረናል። ነገር ግን ‘የፈሩት ይደርሳል የጠሉት ይወርሳል’ እንዲሉ የተሻለ ትጥቅ በነበረው በእግሊዙ ጄኔራል ሮበርት ናፒር ወረራ ምክንያት ከፍተኛ ንዴትና ቁጭት ስለአደረባቸው፤ አንደኛ በፍርሃት ላለመሸሽ፤ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ እጃቸውን ለጠላት ላለመስጠት ሲሉ የገዛ ሽጉጣቸውን በጀግንነት ጠጥተው ለአገርና ለወገን ክብር ሆነው አልፈዋል።

ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማሪያምም የሚወቀሱበት ራሱን የቻለ ሌላ ጉዳይ ቢኖራቸውም፤ በዚህ ረገድ ግን ከከሐዲ የኢትዮጵያ ጠላቶች ወይም የጐጭ አስተሳሰብ ካላቸው የግንዛቤ ድኆች ካልሆነ በስተቀር፤ ከአገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን እንዲህ ዐይነቱ ትችት ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም።

ኢራንም ሆነ ደቡብ ኮሪያ ተፈርተውና ተከብረው የሚገኙት ሊጥ እያቦኩ እንዳልሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል። ማንም ኃይል ሊተነኩሳቸው ቢሞክር የአጸፋ ምላሽ መሥጠት የሚያስችል ብቃት እንዳለቸው ስለሚታወቅ ነው። እዚህ ላይ አንድ ግልጽ መደረግ ያለበት ነገር አለ። በጦርነት ማንም ኃይል አሸናፊ አይሆንም። ልዩነቱ አንዱ ከባድ ጉዳት ሲደርስበት ሌላው ደግሞ መጠነኛ ጉዳት ሊደርስበት ይችል ይሆናል። ነገር ግን ሁሉም የጦርነቱ ሰላባዎች መሆናቸው የሚያጠራጥር አይደለም።

በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ያለች ምንም የልብ ወዳጅ የሌላትና በጠላት የተከበበች አገር፤ ሌላውን ለመውረር ሳይሆን የራሷን ሉዓላዊነት ማስከበር እንድትችል ለማድረግ፤ ዘመናዊ የጦር መሣሪያ እንደሚያስፈልጋት ምንም ጥርጥር እንደሌለው ይታመናል። ማንኛውንም እድገት በልበ ሙሉነት ለማስቀጠል የመከላከያ አቅም ወሳኝ ነው። ሌላው ቀርቶ የሕዳሴውን ግድብ እንኳ ለማጓተት በግብጽ በኩል እየተደረገ ያለው የተቀነባበረ ሴራ ኢትዮጵያ አቅመ ቢስ መስላ በመታየቷ እንደሆነ በግልጽ መታወቅ አለበት።

ምናልባት ደራሲው በሚጽፉበት ወቅት አንድም በስሜት ውስጥ ሆነው፤ ወይም ደግሞ ኮሎኔል መንግሥቱን ከመጥላት ጽፈውት ሊሆን ይችላል። ምክንያቱም ‘ወጡ ሳይወጠወጥ ወስከምቢያው ቁጢጥ’ እንዲሉ፤ የባሕር በር ሳይኖር ባህር ኃይል የማቋቋም ፍላጎት እንዳላቸው መግለጻቸው ይታወሳል። እንግዲህ አንባቢ ፍርዱን ይስጥ፤ የትኛው ሐሳብ ነው ትክክለኛ? የኮሎኔል መንግሥቱ ኃ/ማርያም የጦር መሣሪያ ፋብሪካ ወይስ የዶ/ር ዓቢይ የባሕር ኃይል የማቋቋም ዕቅድ?

በገጽ 114 ሁለተኛው አንቀጽ ላይ ስለ ጋዜጠኝነት ሲተነትኑ “ኢትዮጵያ ዘመናዊ ጋዜጠኝነትን በሥራ ላይ ለማዋል አመቺ ማህበራዊና የባህል መሠረቶች በተጨባጭ የማይገኙበት ሀገራ ናት። … በዚህም አግባብ የአገሪቱን የጋዜጠኝነት ነፃ ፍላጎት ማራመድ ስንመለከት ‘የመታውን ይምታ፣ ያወደመውን ያውድም’ አካሔድ እንዳለው መረዳት ይቻላል።” በማለት ይገልጹታል።

ከዚህ መረዳት እንደሚቻለው ደራሲው የነፃ ጋዜጠኝነትን ጽንሰ ሐሳብ በእጅጉ እንዲፈሩ የሚያደርጋቸው ሁኔታ እንዳለ ግልጽ መሆኑን ነው። ምክንያቱም አምባገነን መሪዎች ለሥልጣናቸው ማራመጃ የሚፈጽሟቸውን ስውርና ሕገወጥ ተግባራት፤ ጋዜጠኞች ለሕዝብ በማጋለጥ ችግር ይፈጥራሉ የሚል ሥጋት እንዳላቸው የሚያሳብቅ ሆኖ እናገኘዋለን። የዚህም አካሄድ የአምባገነኖችን አፍቃሬ ውዳሴ ከንቱን ገጸ ባሕርይ፤ በእጅጉ የሚፃረር አቋም የሚይዝ እንደ መሆኑ መጠን እንደማይቀበሉት ለመረዳት አይከብድም።

በእርግጥም እንደ ጸሐፊው አመለካከት በመንግሥት ስውር ሴራ 20 ባንክ ሲዘረፍ እያዩ ጋዜጠኞች ዝም ማለት ነበረባቸው?! የኮንዶሚኒየም ዕጣ የወጣላቸው ሰዎች የደረሰባቸውን የፍርድ ጥሰት ሕዝብ እንዲያውቅ ማድረግ ተገቢ አልበነበረም?! የለገጣፎን ዘርን መሠረት ያደረገ መፈናቀል ጋዜጠኞች መዘገባቸው ሕዝብን ከሕዝብ ለማጣላት ነው እንጂ ዜና ለመዘገብ ብለው አልነበረም?! በቡራዩ የተከናወነውን የዘር ጭፍጨፋም ሰምተው እንዳልሰሙ፤ አይተው እንዳላዩ ሆነው ማለፍ ነበረባቸው?!

በጠ/ሚኒስትሩና በሕወሓት ጥምር ሴራ የአማራ መሪዎች በጅምላ መገደላቸውን መዘገባቸው የመንግሥትን ስም ለማጥፋት እንጂ እውነተኛውን ዜና ለሕዝብ ለማስተላለፍ ፈልገው አይደለም?! በቅርብ እንኳ ከአማራ ክልል ጤፍ ጭነው ወደ አዲስ አበባ 70 የጭነት መኪናዎች በእነ ታከለ ኡማ ትእዛዝ በሕገወጥ መንገድ መወረሱን ጋዜጠኞች መዘገብ አልነበረባቸውም?!

እጅግ በጣም የሚያስተዛዝብ ጉዳይ ነው። ለነገሩ በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ ሆነ ተብሎ ሥርዓት አልበኝነት እንዲሰፍን ተደርጓል። ለዚህም ዋናው ምክንያት ‘የገበያ ግርግር ለቀጣፊ ይመቻል’ እንዲሉ፤ ሥርዓቱ ሕዝብን እያወናበደና እያስፈራራ ጊዜ ለመግዛት እንደሚፈልግ በተግባር እየታየ ይገኛል።

በአንፃሩም ጋዜጠኞች መዘገብ ያለባቸው ጠ/ሚንስትሩ የከባቢ አየር ንብረት ሚዛንን ለመጠበቅና ኢትዮጵያን በተዋበ ደን ለመሸፈን ችግኝ ሲተክሉ ዋሉ፤ የተለያዩ የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናትን ሰብስበው በማወያየት ስለ አገራችን ፈጣን ዕድገት መመሪያ ሰጡ፤ ከ… መንግሥት መሪ ጋር የጋራ ስምምነት ተፈራረሙ፤ ወዘተ … የሚል አድር ባይ ልማታዊ ጋዜጠኛን ነው የሚፈልጉት። ይህ ዐይነት አሠራር ደግሞ አምባገነናዊ አስተሳሰብ የተላበሰ ውዳሴ ከንቱ እንጂ፤ ጋዜጠኝነት ሊሆን አይችልም።

ጋዜጠኝነት ሦስት ዋና ዋና መርኆች አሉት፤

ሀ) አሳዛኝም ይሁን አስደሳች እውነትን መዘገብ
ለ) ሁልጊዜም ለሐቅ (ለእውነት) መቆም
ሐ) ጥቃት ለደረሰበት፤ ለድምፅ አልባው ድምፅ መሆን ናቸው።

ከዚህ ዉጭ፤

በገጽ 115 ሁለተኛው አንቀጽ ላይ “ውስን ሀብታችን ውራጅ እና ራሣቸው ባለቤቶቹ ለጣሉት ዕሴት ሳይሆን ለላቀው ከፍታ መነሳሳት መዋል ይኖርበታል (ሐሳቡ ምን ለማስተላለፍ አስበው እንደጻፉት ግልጽ አይደለም)። በሙዚቃ ስም የቁሳቁስ ጩኸት፣ በስፖርት ስም እርግጫ፣ በመነቃቃት ስም ድባቴ ውስጥ የሚያስገቡን፤ እራሳችንን እንድናውቅ ሳይሆን እንድንረሳ ... የሚያደርጉን ከመሆን ይልቅ፤ የጋራ ዕሴቶቻችንን እንድናጎለብት መሆን ይኖርባቸዋል።”

ከዚህም መረዳት የሚቻለው የላይኛውን አስተሳሰብ የሚያጠናክር ሆኖ እናገኘዋለን። በዜማ ውስጥ የሚጠቀሱ ስንኞች፤ እምቅና ጠንካራ መልእክት የሚያስተላልፉ በመሆናቸው አምባገናኖች እንደዚህ ያሉ ቅኔያዊ ትርጉም ያላቸውን ውስጠ ወይራ አስተሳሰብ ከመፍራት የመነጨ እንደሆነ መገንዘብ ተገቢ ይሆናል።

ከገጽ115-117 ባሉት ገጾች ቤኔቶ ሞሶሎኒን እና ካርል ማርክስን ጨምሮ በጋዜጠኝነት ሙያ ተሠማርተው ሲሠሩ የነበሩ የተለያዩ መሪዎችን በመዘርዘር ስለተጫወቱት ሚና አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

ከዚያም ይህንኑ ሐሳባቸውን ሲያጠቃልሉ (በገጽ 117 አንቀጽ 3 ላይ)፤ “ወደ ብርሀን ለመሸጋገር የምናደርገው ጉዞ የሌሎችን ዱካና ፈለግ በመከተል የሚገኝ አይደለም። ራሳችን ጭለማ ውስጥ የጣልነውን መግቢያ ቁልፍ እዚያው ጨለማ ውስጥ በመሆን ለመራመድ የሚያግዙንንና ተፈጥሮ ያደለችንን ብርቅ የሆኑ ፀጋዎች ፈልገን በማግኘት ወደ ሁለንተናዊ እድገትና ልማት በሚያሸጋግር ሂደት እንዲታጀብ ማድረግ ይኖርብናል።” - (ምን ለማለት እንደፈለጉ ግልጽ አይደለም)።

ጸሐፊው እንደ ጋዜጠኛ የሚፈሩት ወይም የሚጠሉት ያለ አይመስልም ይህንኑ ሥጋታቸውን በሚቀጥለው መልኩ አጠናክረው ገልጸውታል (በገጽ 118 አንቀጽ 5 ላይ)፤ “… አንድ አዳኝ ገበሬ ስለ ውሻው ጉብዝና እንዲያደንቅለት የቅርብ ጓደኛውን ይዞት አካባቢያቸው ወደሚገኝ አንድ ባህር ይዞት ሄዶ ነበር፣ አሉ። ገበሬውም ውሻውን ባሰለጠነው መሰረት ዳክዬዎችን እንዲይዝ ያደርገውና ከጓደኛው ጋር ይመለከታሉ። በመጨረሻም ገበሬው ውሻው ያደናቸውን ዳክዬዎች ከውሃው ውስጥ ወደ ዳር ሲያወጣ፣ “አየህ!... የኔ ውሻ ምን ያህል ጎበዝ እንደሆነ?” በማለት እየተኩራራ መናገር ይጀምራል። ጓደኛው ግን ሲመለከት የነበረው እንዴት ያለ ጥበብ ይጠቀም እንደነበረ ሳይሆን እንዴት ይሳሳት እንደነበረ ስለሆነ ‘እንደዚህ አድርጎ መያዝ ሲችል አንድ ዳክዬ አምልጣዋለች፣ እንደዚህም ማድረግ አልነበረበትም ...’ እያለ የውሻውን ትንሽ ስህተት አጉልቶ ደግሞ ደጋግሞ በመናገር የውሻውን ጉብዝና ገደል ይከተዋል። … ልክ ወገቡ ድረስ ውሃ እንደተሞላው ብርጭቆ ... በውሃ ስለተሞላው የብርጭቆ ክፍል ሳይሆን ስለጎደለው የብርጭቆው ግማሽ አብዝቶ ይናገራል። የዘመናዊ ጋዜጠኝነትም ልክ እንደ ውሻው ጥቂት ስህተት አጉልቶ እንደሚያወራው ሰው ወይም የተሞላው የብርጭቆውን ክፍል ከመናገር ይልቅ ስለጎደለው አብዝቶ እንደሚያወራው ሰው ነው።”

ሲሉ ጥላቻቸውን አቅንጸባርቀዋል። ከዚህ የምንረዳው አምባገነኖች ስሕተታቸው እንዲደበቅና የሠሯት ትንሽ ነገር ተጋና እንድትነገር የሚሹ፤ ውዳሴ ከንቱ ናፋቂዎች መሆናቸውን በማያሻማ መልኩ አረጋግጠዋል።

በገጽ 135 አንቀጽ ሁለት ላይ እንዲህ የሚል ሐሳብ ይገኛል፤

“በግራና በቀኝ፣ በታችና በላይ ጉዟችንን የሚፈትን እውነታ መኖሩ በተረጋገጠበት ሂደት ውስጥ ከተጫነን የሥጋና የመንፈስ ባርነት ተላቀን ድህነትን ታሪክ የማድረግ ጉዟችንን ለማሳካት በስሜትና በደመነፍስ ሳይሆን በርጋታ፣ ስረ ነገርና ስረ መሠረትን ጨብጠን ሕግን ለዓላማ ሰብሮ፤ ሃሜትን በሚያስቀር ግልጽነት ተግባብቶ እንደሎጥ ሚስት በእንቅልፍ ልቦና ወደዚያ ተመልክተን ወደኋላ መመለስ ዕጣ ፈንታ፣ ዕድል ተርታ እንዳይነጥቀን እንደታማኙ እንስሳ ወደትፋታችን ላለመመለስ በመልካም አራሚ መሪዎች ስብስብ ይህችን ጥቁር ባሕር አቋርጠን የምታጓጓ ጥቁር ምድር ለመፍጠር ከላይ እስከታች እጅ ለእጅ ተያይዘን ዕድገታችን ሰውነታችንን መሠረት አድርጎ እንዲመጣ፣ የብዙዎችንን ተጠቃሚነት እንዲያረጋግጥ ሆኖ መቃኘት ያለበት ብቻ ሳይሆን እንደመንግሥት ሁሉ ምሁራንም በታላቅ ሆደ ሠፊነት መሥራት ይጠበቅባቸዋል።”

ከዐረፍተ ነገሩ መርዘም የተነሳ መልዕክቱ ምን እንደሆነ በግልጽ የማይታወቅ ለዛ የሌለው አሰልቺ ሆኗል።

በገጽ 139 በሁለተኛው አንቀጽ ላይ ስለፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም እንዲህ ሲሉ ይገልጻሉ። “የፖለቲካ ርእዮተ ዓለም፣ አገር ለመምራትና ለሀገሪቷ ሁለንተናዊ ዕድገት ለማምጣት የምንከተለው ሣይንሳዊ የፖለቲካ አመራር ንድፈ ሀሳብና ጥምረት ነው። ይህ ሣይንሳዊ የፖለቲካ አስተሳሰብ በአንድ ሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት ለማስመዝገብም ይሁን በዓለም ላይ ታላላቅ ዕድገቶች እንዲመዘገቡ ለማድረግ ዋናው አንቀሳቃሽ ሞተር ሆኖ ያገለግላል። በየትኛውም የዓለማችን ክፍሎች የመጡ ዕድገቶች መርህ እነሱን የሚመራው ርዮተ-ዓለም ነፀብራቆች ናቸው ተብሎ ይገመታል። ባለንበት ዘመን በዓለማችን አራት ዋና ዋና የርዮተ ዓለም አስተሳሰቦች ያሉ ሲሆን እነሱም፦ ሶሺያሊዝም፣ ሶሺያል ዴሞክራሲ፣ ኒዮ ሊበራሊዝም እና አብዮታዊ ዴሞክራሲ ናቸው።” በማለት ተሳስተው ሌላውንም ያሳስታሉ።

ከዚያም በአያንዳንዱ ዕርዮተ ዓለም መመሪያቸውን ያደረጉ ሀገራትን በምሳሌ ከገለጹ በኋላ ‘አብዮታዊ ዴሞክራሲን’ ግን በልማታዊ መንግሥት ስም ሲተነትኑት ይስተዋላል። በመሠረቱ አብዮታዊ ዴሞክራሲ የሚባል የተወናበደ ርዕዮተ ዓለም የለም፤ እንዲህ ዐይነቱ አስተሳሰብ የመነጨው በወያኔው መሪ መለስ ዜናዊ መሆኑ መታወቅ ይኖርበታል።

ሰውየው ሥልጣንን በማዕከል ጠቅልሎ በመያዝ የሚታዘዙትን ብቻ፤ መመሪያ ተቀብለው የሚፈጽሙ ታማኝ አገልጋዮችን መፈብረክ ሲሆን ይህም ዴሞክራሲ እንደሆነ አድርጎ ወስዶታል። ዋናው መሠረታዊ መገለጫውም አምባገነናዊ የዘረፋ ሥርዓትን ለማስፈን የተቀየሰ ነበር። ነገር ግን ጥያቄ የሚያቀርቡ፣ ወይም ደግሞ ‘ለምን?’ የሚል ማብራሪያ የሚጠይቁ ከሆነ ደግሞ፤ ማዕከላዊነትን አላከበርክም በሚል ተገምግመው እንደ ችግሩ ስፋትና ጥልቀት አብዮታዊ እርምጃ ይወሰድባቸዋል። ይህም ከሥራ መባረር፣ መታሠር ወይም እስከ መገደልም ሊደርስ ይችላል። ይህም በኢትዮጵያ ሲተገበር የቆየ ሐቅ ሲሆን፤ በሌላ አገር እንዲህ ያለ አምባገነናዊ የቡድን ዘረፋ ሥርዓት የተለመደ አይደለም። ጸሐፊው ከ15 ዓመታቸው ጀምሮ አብዮታዊ ዴሞክራሲን እንደ ሕፃን ልጅ ጡጦ እየመገመጉ ስላደጉ ርዕዮት ዓለም መስሏቸው ተሸውደዋል።

ለማንኛውም ግን የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም አስተሳሰቦች፤ አራት ብቻ ሳይሆኑ በርካታ ናቸው፤ ሌላው ቀርቶ ካፒታሊዝምን፣ ኮሙኒዝምን እና ኢትዮጵያ አሁን እየተመራችበት ያለውን አናርኪዝምን ብቻ መጥቀሱ ይበቃል፤ ሌሎቹን መግለጹ አስፈላጊ ሆኖ አላገኘኹትም።

በገጽ 146 በሁለተኛው አንቀጽ ላይ ስለኒዮ ሊበራሊዝም ያቀረቡት ትንተና ግን ተዓማኒነት ያለውና ትክክለኛውን ገጽታ አስቀምጠውታል። እዚህ ላይ ብዙም ትችት ማቅረብ አስፈላጊ ሆኖ አልታየኝም።

በገጽ 152 ስለ ልማታዊ መንግሥት የገለጹበት መንገድ የግንዛቤ እጥረት ያለበት መሆኑን መገንዘብ ይቻላል። ምክንያቱም እንደ ምሳሌ የጠቀሷቸው የእስያ ነብሮች (Asian Tigers) አገሮች ማለትም ሲንጋፖር፣ ደቡብ ኮሪያና ታይዋንን ሲሆን፤ እነዚህ አገሮች እንዴት በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲበለጽጉ ያስቻላቸውን ምክንያት ግን የተገነዘቡት አይመስልም። በአጭሩ ግን የተረጋጋ መንግሥት፣ በቂ የኃይል አቅርቦት፣ የሥራ ዲሲፕሊን ያለው ሕዝብ መገንባትና የእድገት ማነቆ የሆኑትን የቢሮክራሲ አሠራሮችን ቀልጣፋ ማድረግ መሆናቸውን አልጠቆሙም።

በገጽ 153 ላይ ይህንኑ ሲያብራሩ እንዲህ ያለው ስኬት ላይ ሊደርሱ የቻሉት በሁለት መሠረታዊ ነገሮች ማለትም የሥልጣን መሠረታዊ አውታሮች ብለው የተረጎሙት (Infrastructural Powers) የመሠረታዊ ልማት ኃይሎች አቅርቦትና የፖለቲካ ቁርጠኝነት (Political Commitment) ላይ የሚያጠነጥን ነው በማለት ይገልጹታል። ይሁን እንጂ ቻይናን ጨምሮ የእነዚህ አገሮች እድገት ከጀርባው ከዚህም በላይ የጠለቀና የመጠቀ መሠሪ አስተሳሰብ የተላበሰ መሆኑ ይታመናል።

ይኸውም በማኦ ሴቱንግና በቹ ኦንላይ ስትመራ የነበረው ቻይና እንዴት አድርጋ የኢምፔሪያሊዝም ጥማት የነበራትን አሜሪካ በፕሬዝዳንት ኒክሰን ጊዜ ርካሽ የሰው ጉልበት በማሳየት፣ በመቃጥን እንደሚጠመድ ዓሣ ምዕራባዊያን ያላቸውን የማምረቻ ጥበብ ለመዝረፍ ችለዋል። በመሠረቱ ፕሬዝዳንት ኒክሰንም በወቅቱ ታላቅ ተግባር የሠሩ መስሏቸው ነበር። የእርሳቸው አስተሳሰብ አየር በካይ የሆኑትን ታላላቅ ኢንዱስትሪዎች ወደ ቻይና በማዛወር የአሜሪካ ሕዝብ ንጹሕና ያልተበከለ አየር እንዲተነፍስ ለማድረግ አቅደው ነበር። ይሁን እንጂ ለዘመናት የተገነባው የቻይናዎች ዲሲፕሊንና የተረጋጋው የመንግሥት አስተዳደር፤ የኢንዱስትሪ ባለሀብት የሆኑት ኮርፖሬሽኖች የሚያገኙትን ትርፍ በማስላት ፋብሪካቸውን እየነቀሉ ወደ ቻይና፣ ታይዋን፣ ደቡብ ኮሪያና ሲንጋፖር በመውሰድ ሲተክሉ ኖረዋል። ቬትናም እንኳ ሳይቀር በጦርነት ከደቀቀ ኢኮኖሚዋ አገግማ በከፍተኛ የእድገት ጎዳና እየገሰገሰች ትገኛለች።

በአጠቃላይ ግን "እርካብና መንበር" ቀደም ብላ ለኅትመት በመብቃቷ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ማንነት ለማወቅ አስችሎናል። እጅግ በጣም የሚገርመው ነገር የሁላችንም የኢትዮጵያውያን አስተሳሰብ ቀናነት ነው። ምክንያቱም በደርግ ጊዜ ‘ደርግ በሔደ እንጂ መቼም ቢሆን ከደርግ የከፋ አስተዳደር አይመጣም’ በማለት ተዘናግተን እንደነበር የሚረሳ አይሆንም። ቀጥሎም ወያኔ መጥቶ ከደርግ በባሰ መልኩ ሕዝብን ሲያስመርር እንደቆየ ግልጽ ነው። በዚያን ጊዜም ‘ወያኔ ይሂድ እንጂ ከሕወሓት የከፋ አስተዳደር በዚች አገር ላይ ከእንግዲህ አይኖርም’ በማለት ስንጮህ ቆይተን፤ ዶ/ር ዓቢይ ሥልጣኑን ሲይዙ፤ ያደረጉትን የመጀመሪያ ዲስኩር በመስማት ብቻ ሁላችንም ሆ! ብለን ከአጥናፍ እስከ አጥናፍ ደገፍናቸው። ነገር ግን ቀስ በቀስ የጭቃ ጅራፉ መውጣት ጀምሮ፤ በእርሳቸው የሥልጣን ዘመን ንጹሐን እየተሳደዱ ይፈናቅሉ፣ ይታሰሩና ይገደሉ ጀመር። የዘረፋውማ ጉዳይ የማይታየውን ገንዘብ ብቻ ሳይሆን፤ አገር ያወቀውን ፀሐይ የሞቀውን ሕንፃና መሬት ‘ምን ታመጣላችሁ?’ በሚል ዕብሪት እየተዘረፈ ይገኛል።

አገራችን የነበሯትን ታላላቅ መሪዎች ያለአግባብ በስሜታዊነት በማስወገዷ ሌላ የምትከፍለው ዕዳ ያለባት ይመስላል። ለማንኛውም ግን ኢትዮጵያ ጥሩ መሪ ለማግኘት አልታደልሽምና እርምሽን አውጪ!

--//--

ከአዘጋጁ፤

“ዲራአዝ” የሚለው ስም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ሦስት ሴቶች ልጆች ዲቦራ፣ ራሔልና አሜን፤ እንዲሁም ከባለቤታቸው ዝናሽ ከሚለው ስሞቻቸው የመጀመሪያዎቹን ፊደላት በመውሰድ የተፈጠር እንደኾነ ይነገራል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ