ስለሚልዮን ሹሩቤ (በሰናይ ቸርነት)
የምሰራበትን የሚዲያ ተቋም ወክዬ በተለያዩ የፕሬስ መግለጫዎች ላይ እካፈል ነበር፡፡ በዚህም አጋጣሚ ከተለያዩ ነባርና አዳዲስ የሙያ አጋሮቼ ጋር የመተዋወቅ ዕድሉ አጋጥሞኛል፡፡ ከጋዜጠኛ ሚልዮን ሹርቤ (የማራኪ መጽሔት ባለቤት) ጋር ግን እንደሌሎቹ ተቀራርቤ ባልግባባውም በተገናኘኝ ቁጥር የአንገት ሠላምታ ከመስጠት አልቦዘንኩም፡፡
ከዕለታት በአንዱ ቀን ግን ሁለታችንንም የሚያቀራርበን፣ ከቅርርብም አልፎ ቁጭ ብለን የምጫወትበት አጋጣሚ ተፈጠረ፡፡ የፌደራል ጉዳዮች ሚንስትር ለሚዲያ ባለሙያዎች በአዳማ ባዘጋጀው የአራት ቀናት ሥልጠና ላይ ጋዜጠኛ ሚልዮን፣ ጋዜጠኛ ሲሳይ ጉዛይ እና ጋዜጠኛ ሲሳይ መንግስቴ፤ ጋዜጠኛ ወሰንሰገድ ገ/ኪዳን ተከራይቶት በነበረው ጊዜያዊ አልቤርጎ ቁጭ ብለን በሠፊው ተጫውተናል፡፡
በወቅቱም የፌደራል ጉዳዮች ሚንስትር እና የብሮድካስት ባለስልጣን ለጋዜጠኞች ባዘጋጁት ሠነድ ላይ ከጋዜጠኛ ወሰንሰገድ ሠፋ ያለ ማብራሪያና ትችት ሲቀርብ ሌሎቻችን በጥሞና እናዳምጥ ነበር፡፡ ይህም የመወያያ ጉዳይ ወደ ጎን ተደርጎ የድሮ የፕሬስ ታሪክና ጀብዱ በሠፊው በወሰን መተረኩን ቀጥሏል፡፡ ይሄ ሁሉ ጨዋታ ስንጨዋት ግን ሚሊ አቀርቅሮ ብዕሩን ከወረቀት እንዳገናኘ ነበር፡፡ በኋላ ላይ ዝምታው ቢብስብን ወደ እኛ ጨዋታ እንዲቀላቀል ጥያቄ አቀረብንለት፡፡ እሱ ግን የጀመረውን ጽሁፍ ሳያገባድድ እንደማያቆም ያንን ፍንጭት ጥርሱን እያሳያን ወደ ወረቀቱ አቀረቀረ፡፡ (አዎ! ሚሊ ላለፉት 12 ዓመታት በተለያዩ የፕሬስ ተቋማት ሰርቷል፤ ታግሏል ብል ይቀለኛል፡፡ በወቅቱ ለመንግስት የእግር እሳት በነበሩት እንደ አስኳልና ኢትኦጵ በመሳሰሉት አንጋፋ ጋዜጦች ላይ መስዋዕትነት ከፍሏል፡፡ በኋላም የራሱን “ማራኪ” የተሠኘች መጽሔት በማቋቋም የተቻለውን ሁሉ ደክሟል፡፡) በመጨረሻም እንደዛ አንገቱን አቀርቅሮ ሲሞነጫጭር የነበረውን ጽሁፍ እንድንሰማው አስፈቅዶ በሚያስገመግም ድምጹ ጮክ ብሎ አነበበልን፡፡ ሚሊ በሥልጠናው ላይ የብሮድካስቱ ኃላፊ አቶ ልዑል “ጥናት” ብሎ ባቀረበው ጽሁፍ ላይ ነጻውን ፕሬስ ክፉኛ መተቸቱ ስሜቱን እንደነካው ከጽሁፉ ለመረዳት ብዙም ጊዜ አልወሰደብኝም፡፡
ያ… ሁሉ አለፈና የፍትሕ ሚንስትር በነጻው ፕሬሶች ላይ ያቀረበውን ክስና በደሕንነቶች የሚደርስበትን ጫና መቋቋም ሲያቅተው የሚወዳትን ሀገሩንና ቤተሰቡን ጥሎ በወርሃ ነሐሴ ተሰደደ፡፡ በስደት ሕይወት ላይ እያለ ባደረበት ድንገተኛ ሕመም ጥቅምት 3/2007 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ፡፡
እግዚያብሔር ነፍሱን በገነት ያኑራት!!!



