አማረ አረጋዊ ጩቤ ጨበጠ!
ተስፋዬ ገብረአብ
አማረ አረጋዊ ከልብ የሚያደርሱ ቃላትን በመጠቀም ኢህአዴግን የሚገለባብጥበት ጊዜ አለው። የረቡእ ርዕሰ አንቀፅ የዚህ ምሳሌ ነው። ኢህአዴግን በሁለት ከፍሎ ያየዋል። ሙሰኛ ያልሆኑ፣ ለአገር አሳቢ የሚላቸው አሉት። እንዲህ ማለቱ ሚዛን ለመጠበቅ ይሆናል። ርግጥ ነው፣ እኔ ጨምቄ ያቀረብኩት የርእሰ አንቀፁን ቁንፅል አሳብ ነው። አማረ በርዕሰ አንቀፁ ኢህአዴግ በመጪው ጉባኤ ራሱን እንዲያፀዳ መክሮአል። የአማረ ምክሮችና የኢህአዴግ ጠንካራ ጎን ሆነው የቀረቡት አጃቢዎች ገለል ሲሉ የኢህአዴግን እውነተኛ ምስል የሚገልፀው ክፍል የሚከተለውን ይመስላል።
• (የኢህአዴግ አመራር አባላት) … ከሕዝባዊ መስመር እየራቁና እየሸሹ ለግል ገንዘብ፣ ንብረት፣ ክብርና ኔትዎርክ የሚሯሯጡ፣ በጉቦ የተጨማለቁና በሙስና የተነከሩ አሉ። እነዚህ በውስጥ ትግል፣ በደፋርና በቆራጥ ትግል ካልተገለሉና ድርጅቱ ካልፀዳ ድርጅቱን እያበሰበሱ የሚገድሉት ናቸው።
• (ባለስልጣናትን) … በብቃት መመደብ እየቀረ፣ ‘ደጋፊ እስከሆነ ችግር የለም’ እየተባለ የተሾመው ሁሉ የድርጅቱን ዓላማ ማራመድ አልቻለም። ሕዝቡንም ማገልገል አልቻለም። ባለአቅም እየጠፋ ባለምላስ በዛ። ተንዛዛ በጣም በዙ። ሕዝብ ይህንን እያየና እያስተዋለ ‘ምንድን ነው ነገሩ?’ እያለ ነው። አይወስኑም፣ ቢሮ አይገቡም፣ አያሳምኑም። አንዳንዶቹም ይህን እያወቁ ሀቅን ከመጋፈጥ ይልቅ ሽሽትና ድብብቆሽ እየመረጡ ናቸው። ሕዝብ በድርጅቱ ላይ አመኔታ እንዲያጣ እያደረጉ ናቸው።
• (የኢህአዴግ አመራር አባላት) …. ራሳችንን አናታልል፤ የዓለም ሁኔታ ከሚጠይቀው አንድነትና መጠናከር ከሚጠይቀው መመዘኛ አንፃር ሲታይ ያለው አንድነት ጠንካራ አይደለም። ተደፋፍሮ መገማገም፣ ቆራጥና ደፋር ትግል አካሂዶ አንድነትን እውን የማድረግ ሁኔታ በአጠቃላይ በኢሕአዴግ፣ በተናጠልም በእያንዳንዱ ድርጅት እየታየ አይደለም።
• ጠንካራ አንድነት በሕወሓት ውስጥ አይታይም፣ ጠንካራ አንድነት በብአዴን ውስጥ አይታይም፣ ጠንካራ አንድነት በኦሕዴድ ውስጥ አይታይም። ጠንካራ አንድነት በደኢሕዴን ውስጥም አይታይም። እርስ በርስም ጠንካራ አንድነት እየታየ አይደለም። (ይህ ወደ አማርኛ ሲተረጎም - ሕወሓት ውስጥ መካፋፈል አለ። ብአዴን ጎራ ለይቶአል። ኦህዴድ በቡድን ተለያይቶአል። ደኢህዴን ሲዳማና ወላይታ ብሎ እየተናቆረ ነው። በጥቅሉ የኢህአዴግ ጃንጥላ ተቀዶአል።)
• ልማት እየቆመ ነው። የፍትሕ ሥርዓት እየተደረመሰ ነው። መንግሥት በቂ ገንዘብ ማሰባሰብ እያቃተው ነው። በብዙ ቦታዎች ንብረትና ገንዘብ እየባከነ ነው። የሕዝብ ጉጉትና ምኞት በተፈለገው ፍጥነት እውን እየሆነ አይደለም።
• ሕዝብ መንግሥትን ለመደገፍ ጨዋነቱንና ኢትዮጵያዊነቱን ለማሳየትና ለማረጋገጥ በእጅጉ ዝግጁ ነው። በሐዘን ጊዜም በጋራ እንደ አንድ ሰው አልቅሷል፤ አዝኗል። ጨዋነቱንና ኢትዮጵያዊነቱን በግልጽ ለዓለም አሳይቷል። በእግር ኳስ ደስታም ማንነቱን በየጎዳናው አሳይቷል። ያኮራል፣ እውነትም ወርቅ ሕዝብ። ግን … ነገር ግን እንደ ኢትዮጵያዊያን ተንቀሳቀሱና ማንነታቸውን አሳዩ ማለት ከመሪው ፓርቲ ጋር ያላቸውን ግንኙነት በአዎንታ አንፀባረቁ ማለት አይደለም። ፍትሕ ሲጠፋ አቤት የምንልበት ጠፋ። ወደ ሕዝብ ቀርቦ፣ ወደ ሕዝብ ወርዶ የሚያነጋግረን ሹም ጠፋ እያሉ ነው። ይህ ማለት ሕዝቡ የሚፈልገውን ግንኙነትና ትስስር እያገኘ አይደለም።
ተስፋዬ ገብረአብ
This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.



