ኤፍሬም እሸቴ (www.adebabay.com)

በሕይወቴ ኢትዮጵያ መሪ ሲሞትባት አላየኹም። ቀዳማዊ አጼ ኃ/ሥላሴ ሲወርዱ የሕልም ያህል ትዝ ይለኛል። ሞታቸውም እንደ ሕልም አለፈ። ከዚያ በኋላ የወታደራዊው መንግሥት ዘመን ብዙ ባለሥልጣናት ሲሞቱ መሪው ግን ምንም ሳይነኩ ቆዩ። ከዚያም የእርስበርስ ጦርነቱ መንግሥታቸውን ጠራርጎ ሲገነድሰው እሳቸው ወደ ዚምባብዌ ገቡ። አልሞቱም ዛሬም ድረስ። ከዚያ በኋላ ኢትዮጵያን የመሩት አቶ መለስ ዜናዊ፣ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ እና ፕሬዚደንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ ናቸው። ከእነርሱ መካከል በሞት በመለየት አቶ መለስ ቀደሙ ማለት ነው። ነፍሳቸውን ይማር።

 

ሞታቸውን የሰማኹት ልተኛ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩኝ ነበር። ኢቲቪ ኦንላይን ብከፍተው እምቢ አለ። ትዊተር ውስጥ ስገባ መሞታቸውን ብዙዎች ከአዲስ አበባ እየዘገቡ ነው። ከዚያ ኢቲቪውም ሠራ። ከዚያ ቢቢሲ ረዥም ዝግጅቱን ማቅረብ ቀጠለ። በእርግጥም አቶ መለስ ሞተዋል።

 

ስለ ኢትዮጵያውያን ስሜት በጥቂቱ የምረዳው ከማኅበራዊ ድረ ገጾች ነውና ሁሉንም ጓዳ ጎድጓዳ መፈተሽ ያዝኩ። ብዙው ሰው “ዕረፍተ ነፍስ ይስጥዎት” የምትለዋን የእንግሊዝኛ አሕጽሮት “R.I.P/ Rest in Peace” ደርድሮታል። በተለምዶ ስለ እርሳቸው ጠንካራ ትችቶች የሚያቀርቡ ሰዎች ሳይቀሩ “ዕረፍተ ነፍስ” እንዲሰጣቸው በመመኘቱ በኩል የተለየ ስሜት አላሳዩም። ባህሉም ከዚህ ውጪ አይፈቅድም። “ሙት አይወቀስ” እንዲል።

 

ከዚህ አልፎ ግን በቅርብ ዘመናት የአገር መሪ ሲሞት በቅጡ አስተናግዳ የማታውቀው ኢትዮጵያ አሁን እንዴት ባለ ስሜት እንደምትቀበለው ማወቁ በራሱ አንድ ታሪክ ነው። አገር የሚፈርስ ስሜት ግን መሰማቱ አይቀርም። መሪ ማለት አባትም፣ የሁሉ ጠባቂ ነው የሚለው ገሚስ ታሪካዊ ገሚስ ሃይማኖት መሰል ሚቶሎጂያዊ ሐሳብ ሥር የሰደደ ነው። የአገሪቱ እስትንፋስ በአንድ ሰው መዳፍ ውስጥ “እንደ ኒኩሊየር ቁልፍ” እንደሌለች እየተረዳን እንኳን ነገር ግን “ሞቱ” ሲባል ክው፣ ድንግጥ፣ ርብሽ እንላለን።

 

አጼ ምኒሊክ ከሞቱም በኋላ ስንት ዘመን ነበር ሞታቸው የተደበቀው? ስድስት ዓመት? ንግሥት ዘውዲቱ ከሞቱ በኋላ ከሕዝቡ ሙሉ ፍቅር እና አክብሮት በክብር ተቀብረዋል። ልጅ ኢያሱ ያንን ዕድል አላገኙም። ተፈሪ መኮንን አስረዋቸው በዚያው እንዳረፉ ይታወቃል። ራሳቸው ተፈሪ መኮንን (አጼ ኃ/ሥላሴ) አረጋዊነታቸው እና ሽበታቸው ሳይከበር ከተራ ሰው ሞትም ያነሰ ሞት ሞቱ። አስከሬናቸው በድብቅ ተቀመጠ። መንግሥቱ ኃ/ማርያም አሉ።

 

እንግዲህ ኢትዮጵያ መንግሥታዊ የቀብር ሥርዓት ያደረገችለት የቅርብ ዘመን መሪ የላትም ማለት ነው። መለስ በዚህ በኩል ዕድለኛ ናቸው። በጦርነት ሥልጣን ቢይዙም በሰላም ከመንበራቸው ያውም በማይቀረው ጥሪ በሞት መውረዳቸው ሌሎቹ መሪዎች “ያዩትን” እንዳያዩ ያደርጋቸዋል። መንግሥታቸው ሳይነቃነቅ፣ ጦራቸው ሳይፈታ፣ ዙፋናቸው እንደተከበረ፣ ከደጃፍ ቆሞ የሚያንኳኳ ተቀናቃኝ ሳይገጥማቸው ወደላዩ ቤት ሔደዋል።

 

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ዕረፍት ከቅዱስነታቸው ጋር “ኋላና ፊት” መሆኑም በራሱ “የተለየ” ያደርገዋል። ከፖለቲከኛው እስከ ሃይማኖት ሰዉ ድረስ ሁሉም የየራሱን ትርጉም ይሰጠዋል። ይህንን ጽሑፍ የምጽፈው ዕረፍታቸው ከተሰማ ከጥቂት ጊዜ በኋላ አስተያየቶቹን በሙሉ ለመገምገም ጊዜ ባላገኝም ከሁለት ወር ላላነሰ ጊዜ “አርፈዋል” ሲል ከነበረው ተቀናቃኛቸው ጀምሮ በተለይም በዋልድባ እና በሙስሊሞች ጉዳይ እስከማይቀበላቸው ድረስ አንድምታው ሰፊ ሐተታ የሚፈልግ ይሆናል። ለሐተታው ደግሞ እንደርስበታለን።

 

ለጊዜው እንደ ባህላችን ለቤተሰባቸው፣ ወዳጅ ዘመዳቸው በሙሉ መጽናናትን ይስጥልን ማለት ይገባል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ